የማህበረሰባዊ ሞራል ዝቅጠትና የዘረኝነት ማገንገን?! | (በአፊላስ አእላፍ)
የዛሬ አንድ ዓመት ከመንፈቅ አካባቢ 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ በሃዋሳ ሲከፈት የግንባሩ ሊቀ መንበር እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ካደረጉት ንግግር ላይ መሃል ”ዝርፊያና ሌብነት፤ ጥላቻና ቂመኝነት፤ ዘረኝነትና ስግበግብነት ምንጫቸው የሞራልና የግብረ ገብ ደረጃ መዝቀጥ መሆኑ አያጠያይቅም።” ብለው ነበር፡፡
ስለማህበረሰባዊ ሞራል ምንነት ከተሰጡ ብያኔዎች ውስጥ፡- “ሁሉን አቃፊ፤ ሁሉን በእኩል የሚያይና መከባበርን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ” የሚል ሲሆን ”የሞራል እሳቤዎች ስንልም ለምሳሌ ያህል አቃፊነት፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ከሌሎች ጋር አብሮ መኖር፣ ሌሎችን መርዳት ወ.ዘ.ተ የሚሉ የማህበራዊ እሴት ብይኖችን እናገኛለን፡፡
እንግዲህ እንዲህ አይነት የሞራል ልዕልና ላይ የደረሰ ማህበረሰብ የሚመራው፤ በህግና ህግ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። በማህበረሰቡ ውስጥም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባትም አያስቸግርም። በተቃራኒው ግን የሞራል ዝቅጠት ሲያጋጥም ግዴለሽ የሆነ ማህበረሰብ ይፈጠራል።
ሞራልና ግብረ ገብ የሌለው ማህበረሰብ፤ ከራስ አልፎ ሃገርንም ጭምር ፈተና ውስጥ የሚከት ይሆናል።”የማህበረሰባዊ ሞራል መዝቀጥ ወይም መውደቅ ከየት ይጀምራል ቢባል ከአንድ ግለሰብ ይጀምራል እላለሁ። የሞራል ልዕልና የሌለው ግለሰብ ለራሱና ለአካባቢው ማህበረሰብ ከብር አይሰጥም፤ ለሃገር አድገት ህልውና ብዙም ደንታ የለውም፤ ስለዚህ ደንታ ቢስ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ ይሄዳል፤ ደንታ ቢስ በሆነ ትውልድ የሚሞላ ሃገር ደግሞ እንደ ሃገር መኖርና መቀጠል በራሱ የከፋ ችግር ይሆናል፡፡
ዛሬ እንደ ሃገር ኢትዮጵያን እየተፈታተናት የሚገኘውም ከዚህ ህሳቤ የሚቀዳ ነው። ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ይሻል፤ ይጠይቃልም። ሆኖም ስርዓቱን ለመገንባት የሚያስችለው ማህበረሰባዊ የሞራል ልዕልና እያደር መቀጨጩ ግን ለብዙዎቻችን አሳሳቢ ሆኖ አልታየም!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሃዋሳው ንግግራቸው አስረግጠው የተናገሩትም ይህንኑ ይመስላል። ”የስራ ፍቅርን፣ የሰው ክቡርነትን፣ ፍትህን ፣ዴሞክራሲያዊ አመለካከትን፣ የሃሳብ ልዕልናን እንዲሁም ሰላምና እኩልነትን የማስረፅ እና የማረጋገጥ ሂደት በሞራልና በግብረ ገብ ደረጃው በወደቀ ማህበረሰብ ውስጥ የሚታሰብ አይደለም።”
እንደኔ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልክ ብለዋል፡፡
በስነ-ማህበራዊ ጥናት የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የኢኮኖሚ፣ የቤተሰብና የትምህርት ተቋማት የሚባሉ አምስት ማህበራዊ ተቋማት አሉ። እነዚህ ተቋማት ተያያዥና ተደጋጋፊ ናቸው። አንዱ ላይ የተበላሸ ስርዓት ወደ ሌሎቹም ተዛምቶ እንደሚያጠለሽ ይታወቃል። እኒህ ማህበራዊ ተቋማት ሞራላዊ ስርዓትም ሆነ ስነ ምግባር ያለው ዜጋ በመፍጠር ረገድ ያላቸው አስተዋፅኦ እጅጉን የላቀ ነው።
በግልጽ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው አክራሪ ብሄርተኝነት የሚመነጨው ከፖለቲካ ተቋማት ብልሽት የሚመነጭ ነው። ብሄርተኝነትና ዘረኝነት ጫፍ የረገጡ ሁነዋል። ብሄር እየለዩ በየአካባቢው የታዩት መፈናቀሎችና ግድያዎች ለዚህ የሞራል ዝቅጠት፤ ፍንትው ያለ ማሳያ ሊሆኑ ይችላል።
ለዚህም ነው ሃገራዊ ልዕልና እየተሸረሸረ መጥቶ፤ ክልላዊ ልዕልና እየነገሰ መጥቷል የምንለው!
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዜጎች የሚለኩት፤ በሰውነታቸው ሳይሆን በብሄራቸው እየሆነ መጥቷል፡፡ ሌላው ይቅርና የግለሰቦች ፀብ እንኳ ብሄር ተኮር የመሆኑ ምክንያት ከዚሁ ከማህበራዊ የሞራል እሴት ማሽቆልቆል ጋር ይገናኛል፡፡
ሰውን በሰውነቱ ብቻ ካላየንና የሚገባውን ሽልማት ሆነ ቅጣት፤ ነፃና ገለልተኛ ሁነን መስጠትና መመዘን ካልቻልን አይደለም ዴሞክራሲ ተፈጥሯዊ ህልውናችንን እናጣለን! ብሄርተኝነትና ዘረኝነት ባየለበት ሃገር ውስጥ ደግሞ የህግ ተጠያቂነትም ስለሚላላ፤ ግለሰቦች ብሄራቸውን ሽፋን አደርገው ህዝብን ለመዝረፍ፣ለማፈናቀልና ለመግደል ምክንያት መሆናቸው አይቀርም።
ታዲያ ሁነኛ መፍትሔው ምንድ ነው?!
እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች ድምዳሜ ከሆነ መጀመሪያ መቅደም ያለበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ቤተሰባዊና የትምህርት ተቋማት ራሳቸውን ማፅዳት ሲችሉ ነው።
”ትምህርት ቤቶች የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ከሆኑ፤ ሃይማኖት ተቋማቱም የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ መንዣ ከሆኑ፤ኢኮኖሚውም እንደዛ ከሆነ መጨረሻችን ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ነው። ስለዚህ ተቋማት በቅድሚያ ራሳቸውን ማፅዳት አለባቸው። ራሳቸውን ካፀዱ በኋላ ሲቀጥል ማህበረሰባዊ ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ።” ይሉናል ምሁራኑ።
አዎን ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች፤ በድምር ሁላችን፤ ማህበረሰባዊ የሞራል እሴቶችን ማነፅ ከቻልን፤ ያኔ በሃገሩ የሚኮራ፣ የሞራል ልዕልናው ከፍ ያለ፣ መልካም ምግባር ያለው ኢትዮጵያዊ፤ በኢትዮጵያ ምድር መፍጠር እንችላለን እልሃለሁ።
እስከዚያው ግን?!…