Connect with us

ተጓዦች ስለ ሸዋ ምን ይላሉ?

ተጓዦች ስለ ሸዋ ምን ይላሉ?

ባህልና ታሪክ

ተጓዦች ስለ ሸዋ ምን ይላሉ?

“አካባቢው በውሸት ትርክት ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል”
አቶ ታደሰ ፈቅ ይበሉ፤ የአንኮበር ወረዳ ም/አስተዳዳሪ
ከአፄ ምኒልክ የጦር ግምጃ ቤቶች አንዱ

ቦታው በሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር ወረዳ ይባላል፡፡ የዘመናዊ መንግስት መፈጠሪያ ነው:: አፄ ምኒልክ ከ1857 እስከ 1881 ዓ.ም የሸዋ ንጉስ ሆነው የቆዩበት ሲሆን ከዚያም አዲስ አበባ በመሄድ ማዕከላዊ መንግስት መስርተው አገርን አንድ አድርገው የመሩበት አካባቢ ነው፡፡ ይሄ ወረዳ ከ110 ሺህ ሕዝብ በላይ የሚኖርበት፣ 19 የገጠርና 4 የከተማ ቀበሌዎች የተዋቀሩበት አካባቢ ነው፡፡ ታሪኩም ገድሉም ትልቅ ወረዳ ነው፡፡ ከታሪኩ ግዝፈትና ትልቅነት አንፃር መንገዱንም ከተማውንም ብታይው፣ ጥንት እነ አፄ ምንሊክ እንዳስቀመጡት ነው፡፡ አካባቢው ከአሁኑ ይልቅ በዚያን ዘመን ብዙ ስልጣኔና ብዙ እድገት ነበረው፡፡ እርግጥ ወደፊት ብዙ ተስፋ አለ፡፡ ከአዲስ አበባም ሆነ ከዞኑ ዋና ከተማ ደብረ ብርሃን በቅርብ ርቀት ላይ ቢገኝም አስፓልት ቀርቶ ደህና የጠጠር መንገድ እንኳን የለውም፡፡

የአፄ ምኒልክን ያልተፃፈና ያልተደረገ ነገር እያራገቡ እሳቸው ላይ የፈጠሩት ጥላቻ፣ እስከ ዛሬ አካባቢው የልማት ብርሃን ሳያገኝ ሰውም ማደግ ያለበትን ያህል ሳያድግ በድህነት ሲማቅቅ ኖሯል፡፡ ሆኖም አሁን ከደብረ ብርሃን አንኮበር – አዋሽ አስፋልት መንገድ እየተሰራ ነው:: ያ መንገድ ሲጠናቀቅ አካባቢው ታላቅነቱን የሚመልስበትና ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ የሚሆንበት ሰፊ እድል አለው፡፡ ባለሀብቶችም በአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ሰፊ እድል ይኖራቸዋል፡፡

አካባቢው ከታሪኩ ግዝፈት አንፃር፣ መሰረተ ልማት ባልተሟላበት፣ በቂ ማረፊያ በሌለበትና እኛም የማስተዋወቅ ስራ ባልሰራንበት ሁኔታ እንኳን ቱሪስቶች ከየትኛውም የዓለም ጥግ እየመጡ፣ ጐብኝተው ተደንቀው ይሄዳሉ፡፡ መሰረተ ልማት አሟልተን አስተዋውቀን ሲሆን ደግሞ የሚፈጠረውን መገመት አያዳግትም:: አሁን አፄ ምኒልክ፣ ከአባታቸው ከሀይለ መለኮትና ከአያታቸው ንጉስ ሳህለ ስላሴ ዘመን ጀምሮ ጥንታዊ ቅርሶች በነሱ ዘመን በተመሰረቱ በዚህ ቤተ መንግሥት ዙሪያ ባሉ አምስት አብያተ ክርስቲያናት እንደነገሩ ተቀምጠው ነበር፡፡ አሁን እንደምታይው በቤተ መንግስቱ በምስራቅ በኩል ማዶ ላይ ትልቅ ሙዚየም ገንብተናል:: እየተጠናቀቀ ነው፡፡ ያን ጊዜ በምቹ ስፍራና ሁኔታ ቅርሶቹን አስቀምጠን ለማስጐብኘት ያስችለናል፡፡ ባለፈው በውሸት ታሪክ ወረዳው ተጐድቶ መቆየቱ ቢያስቆጨንም፣ አሁን ያለው ተስፋ ይበልጣልና አካባቢውን ለመለወጥ እንደ አመራርነታችንም እንደ ተወላጅነታችንም ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡ አንኮበር ቤተ መንግስትም ሆነ የአካባቢው ብዙ መስህቦች ሊጐበኙ ይገባቸዋል፡፡ በተለይ የአገራችን ሰዎች እየመጡ አገራቸውን፣ ማንነታቸውን የኋላ ታሪካቸውን እንዲጐበኙና የአሸናፊነት ስነ ልቦና እንዲላበሱ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

“በአፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመን ኪነጥበብ ያበበበት
ቦታ ሸዋ ነው”
(አበረ አዳሙ፤ የኢትዮትጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት)

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሸዋን ለመጐብኘት ይህን መርሃ ግብር ያዘጋጀበት ምክንያት ያው እንደሚታወቀው፣ ሸዋ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው ቦታ ነው፡፡ በርካታ ነገስታት፣ የታሪክ ተዋንያን፣ በስነ ጽሑፍም ሆነ በኪነጥበብ ዘርፍ አንቱ የተባሉ ሰዎች የፈለቁበትም ጭምር ነው ሸዋ፡፡ በአፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግስት፣ ስነ ጽሑፍ ያበበበትና ጣሪያ ላይ የደረሰውም በዚሁ በሸዋ ነው፡፡ ያንን የጥንት ስነ ጽሑፍ ያሳበበውን አካል ወይም የነበረበትን ቦታ እንዲሁም ነገስታት ከዚህ እየተነሱ ነበር አንዲት ጠንካራ አገር የመሩበት ታሪክ የሚፈልቀው ከዚሁ ከሸዋ ነው፡፡ በዘመነ መሳፍንትና በሌሎች ምክንያቶች ተበጣጥሳ የነበረችውን ኢትዮጵያን መልሰው ሰፍተው አንድ ያደረጉት መንግስታት መነሻ ሸዋ ነው፡፡ እንዴት ነው ያንን የተበጣጠሰ አገር አንድ ያደረጉት? ይህንን ያደረጉበት ዘዴስ ምንድነው? አሁን ላለንበት በየመንደሩ የተደራጀ የመንደር ጐረምሳ ለሚያምሳት አገር ምን ትምህርት ይሰጣል? የሚለውም መታየት አለበት፡፡ በአጠቃላይ አካባቢው መጐብኘት አለበት የሚል አላማ ይዘን ነው ጉብኝቱን ወደ ሸዋ ያደረግነው፡፡

አሁን እንደምናየው አገሪቱ የምትመራው በመንግስት ሳይሆን በየመንደሩ በተደራጁ ጐረምሶች ነው፡፡ አባቶቻችን ያኔ ጥንት፣ የምትከበር የምትፈራ ግርማ ሞገስ ያላት፣ በነጭ ያልተወረረች፣ አድርገው ያስረከቡን እንዴት ነው? የሚለውን ለማወቅ ወደዚህ ስፍራ መምጣትና ማጥናት ተገቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ማህበራችን “ብሌን የሰላም ኪነጥበብ ምሽት” በየወሩ ስላለን ለዚያም ግብአት ይሆነናል፡፡ ምንም እንኳን በዚያን ወቅት አገሪቱ ላይ በየአካባቢው የተለያዩ መንግስታት ቢኖሯቸውም፣ ለምሳሌ ጐጃም፣ ጐንደር፣ ወሎ የየራሳቸው ንጉስ ነበራቸው ደቡብም ብትሄድ ከፋ ወላይታም የራሳቸው ንጉስ ነበሯቸው ነገር ግን እነዚያን ወደ አንድ ያመጡበት ፍቅር ምንድነው የሚለው አስደናቂ ነው፡፡ እርግጥ ታሪኩን በመጽሐፍ ስናነብ ኖረናል፤ ነገር ግን ቦታው ላይ በአካል ተገኝቶ የመመልከትና የመረዳትን ያህል አይሆንም፡፡ ለዚህ ነው ጉብኝቱ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘነው፡፡

አንኮበር ስመጣ
የመጀመያ ጊዜዬ ነው
(አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ)

አንኮበር ስመጣ የመጀመያ ጊዜዬ ነው፡፡ ይህ ቦታ ለማየትና ለመጐብኘት ከምጓጓላቸው ቦታዎች አንዱ ነበር፡፡ ለአዲስ አበባም ቅርብ ነው፡፡ የሚገርምሽ ወደ ደብረ ብርሃን ለስራም ለተለያዩ ጉዳዮችም ብዙ ጊዜ እመጣለሁ:: አንኮበርን የማየት እድል አልነበረኝም:: በዚህም ሁሌ ራሴን እወቅሳለሁኝ፡፡ ዛሬ ይህ ዕድል ገጥሞኝ መጥቼ ሳየው፣ መደነቄን እንዴት እንደምገልጽ አላውቅም፡፡ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ቁጭ ብለሽ እምዬ ምኒልክን ስታስቢያቸው ገና የመልክአምድሩ ሁኔታ የሚነግርሽ ነገር አለ፡፡ ቤተ መንግስቱንና ዙሪያ ገባውን ስታቃኚ፣ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡ የትኛውንም ቦታ ከጠላት ለመጠበቅና ለመቆጣጠር የሚመች፣ እውነትም ንጉስ አለበት የሚያሰኝ ግርማ ሞገስና ክብርን የተሞላ ቦታ ነው፡፡ ይህን ስታስቢ አፄ ምኒልክ ምን አይነት ሰው ነበሩ ወደሚለው ትመጫለሽ:: እናም እዚህ ቦታ ላይ ቤተ መንግስታቸውን ማድረጋቸው ለህዝቡ ተደራሽ ያደርጋቸዋል፡፡ ምክንያቱም በዚህ በኩል አፋር ቅርብ መሆኑን ስትሰሚ፣ በሌላው አቅጣጫ አዋሽ ቅርብ መሆኑን ስታውቂና ለደሴም ቅርብ ነው ሲሉሽ ቦታውን እንዴት እንደመረጡት ምን ያህል በሳል ንጉስ እንደነበሩ ትረጂያለሽ፡፡ ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ በአጠቃላይ አራት አይና እውቀት የታደሉ መሪ እንደሆኑ፣ ትገነዘቢያለሽ፡፡

ሁላችንም የተለያየ ሙያ ይዘን ወደዚህ ቦታ ስንመጣ ዝም ብሎ ለመምጣት ብቻ አይደለም:: ይሄን ቦታ ስትጐበኚ ወደ እውነተኛ ማንነትሽ ነው የሚመልስሽ፡፡ ሌሎች አለማትን ስትጐበኚ ተረት ተረታቸውን ነው የሚያስጐበኙሽ፡፡ ያ ትንሽ ሀብት ነው እያልኩሽ አይደለም፡፡

እነሱ በአፈ ታሪክ የወረሱትን ታሪክ ቁስ አድርገው፣ ሃሳቡን የሚታይ የሚዳሰስ ያደርጉና የተረቱን መጀመሪያ አውርተውልሽ፣ ከዚያ መጽሐፉን ሰጥተው ቦታውን ያስጐበኙሻል:: ይህን ያህል ራሳቸውን የመሸጥ አቅም ይፈጥራሉ፡፡ እኛ ደግሞ በዓለም ትልቁን ገፀ በረከት ነፃነትን ያወጁና ያጐናፀፉ፣ በተለይ ለጥቁር ህዝብ ምልክትና ባንዲራ የሆኑት ደጉ ንጉስ ቤተ መንግስታቸው መሃላችን ሆኖ አለመጐብኘት ራስን መውቀስ ነው፡፡ እኔ ራሴን ወቅሻለሁ፡፡ የእኛ ታሪኮች በእውን የተከሰቱ፣ የሚዳሰሱ የሚጨበጡ ናቸው፡፡ እንደ ቴአትር ባለሙያነቴና የቴአትር ባለሙያዎች ማህበርን ወክዬ እንደመምጣቴ የተሰማኝን ቁጭት ማጋራት ዋናው ተግባር ይሆናል፡፡

የደራሲያን ማህበር የሚሰራው ስራ በዕውነት መታደል ነው፡፡ ከአንድ የኪነጥበብ ሰዎች ሰብስብም የሚጠበቅ ነው፡፡ እንደነገርኩሽ እኔም የቴአትር ባለሙያዎችን ማህበር ወክዬ ነው የመጣሁት፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ደጋፊ አካላት ማህበሩንና ዓላማውን መደገፍ አለባቸው፡፡ ለዚህ ጉዞም ላገኘሁት እድል ማህበሩንና አመራሮቹን አመሰግናለሁ፡፡ እኔ ባልሳተፍም ጓደኞቼ የነገረኝ የፍቅር እስከ መቃብር፣ የፍቅረማርቆስ ደስታ ሀገር የሀመር ጉዞ እጅግ የሚደንቁና የሚያስቆጩ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፡፡ ማህበሩ ይህንን ትልቅ ስራውን ለመስራት አጋዥ ያስፈልገዋል፤ ሊታገዝ ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ምንጭ:- አዲስ አድማስ

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top