Connect with us

የሁለት መንግሥታት አገር-ኢትዮጵያ

Photo: Facebook

ፓለቲካ

የሁለት መንግሥታት አገር-ኢትዮጵያ

የሁለት መንግሥታት አገር-ኢትዮጵያ | በኃይሉ ሚዴቅሳ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‹የውጭ አገር ፓስፖርት ይዛችሁ የምትበጠብጡን ሰዎች አገራችሁን ለቃችሁ ውጡ፤ አለያ ተውን›› የሚል ይዘት ያለው ንግግር ካሰሙ በኋላ፣ አቶ ጃዋር መሐመድ ‹‹እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል›› የምትለዋን የአይጥ ተረት በመተረት ለመፋለም መዘጋጀቱን በገደምዳሜ ገለፀ፡፡

ይህ ከሆነ በኋላ ምሽት ላይ በኤልቴቪ ቀርቦ ጠቅላይሚኒስትሩን፣ መንግሥታቸውንና ድርጅታቸውን በተደጋጋሚ ‹ውሸታም› እያለ ተቸ፡፡‹‹ይህንን የለውጥ ኃይል ደግፉት እያልኩ ለማሳመን የጣርሁትን ጥረት ሳስበው አሁን ይቆጨኛል-ዓይነት ንግግርም ተናገረ፡፡በዚህ በጃዋር ንግግር ጠቅላይሚኒስትሩ እንደሚበሳጩ እሙን ነው፡፡

የሁለቱ ሰዎች ቁርሾ ውስጥውስጡን ሲወራ ቢሰነብትም ይህንን ያህል ጎልቶ ይወጣል ተብሎ አልተጠበቀም ነበር፡፡ይሁን እንጂ ጠቅላይሚኒስትሩ ኢሕአዴግን ለማዋኸድ ደፋ ቀና እያሉ ባሉበት ሰዓት ‹‹ኢሕአዴግ የሚዋኸደው አሀዳዊ ሥርዓትን ሊያመጣ ነው›› ብሎ ጠቅላይሚኒስትሩን ተቸ፡፡

በዚህም ሳያበቃ ‹‹መደመር የተባለው ነገር ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንም አይለይም›› ብሎ አዲስ ነገር የሌለው ነገር እንደሆነ አብራራ፡፡በዚህ ሁሉ ንግግር ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ እንደማይደሰቱ የታወቀ ነው፡፡ እናም በእኩለ ሌሊት ወደ አቶ ጃዋር መኖሪያ ቤት አካባቢ ሠራዊት ሄደ፡፡ ይህንንም ጥቃት ሊደርስበት እንደሚችል አድርጎ ቀሰቀሰበት፡፡ ወጣቶችም አዲስ አበባን ከበቧት፡፡

ይህ የዚህ 24 ሰዓት ሂደት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ነገሩ ፈር መያዝ የነበረበት ድሮ ነበር፡፡‹‹እዚህ አገር ላይ ያለው መንግሥት ሁለት ነው፡፡አንዱ የዐቢይ፣ሌላው የቄሮ ነው›› ተባለ፡ ፡ ‹‹የመደመርን ካልኩሌተር የሠራነው እኛ ነን›› ሲልም ተደመጠ፡፡ ከዚያ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሁለተኛ ሰው ደመቀ መኮንን ‹‹ቄሮ የለውጥ ሞተር›› ሲሉ አደናነቁ፡፡

በሕቡዕና ሕጋዊ ባልሆነ አደረጃጀት ውስጥ ያለን ኃይል እንደ ለውጥ አቀጣጣይና የለውጥ ባለቤት አድርገው ያቀረበው እራሱ መንግሥት ነበር፡፡

ከዚያም ረዘም ላሉ ወራት ይህንን እንደ ቅቡል አጀንዳ የወሰደው አቶ ጃዋር፣ በቄሮ የተረሳ መሰለው፡፡ስለዚህ ከወጣቶቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመፈተሸ፣ የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየምን አጀንዳ አደረገ፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቆጥበው ያሠሩትን ኮንዶሚኒየም፣እንዳይተላለፉ ለማድረግ እነዚህኑ ወጣቶች ጠራ፡፡ ከዚያም አትርሱኝ አልረሳሁዋችሁም ተባብለው ተለያዩ፡፡

እነሆ በድጋሚ ይህ ጋርዮሽ የሚገናኝበት አጋጣሚ ተገኘ፡፡ ጃዋር ተወርሬያለሁ የሚል ይዘት ያለው ጽሁፍ ከፖስተ በኋላ ወጣቶቹ ቤቱ ድረስ ዱላቸውን ይዘው መጡ፤የአዲስ አበባ መንገዶችንም ዘጉ፡፡መንግሥትም ለጃዋር መሐመድ ጠባቂ ኃይል መመደቡን ቀጠለበት፡፡

አሁን ጥያቄው ያለው አንድና ግልጽ ነው፡፡ነገርዮው ሕግ ማስከበር ከሆነ፣ የሕግ ጉዳይ መከበር የነበረበት ዱሮ ነበር፡፡በአንድ በኩል ለአንድ በትርፍ ለተቋቋመ ድርጅት ባለቤት (ለዚያውም ለውጭ ዜጋ) በድሃ ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ የተቋቋመን ሠራዊት ጠባቂ አድርጎ መመደብ ስህተት ነበር፡፡ሲቀጥል ይህንን ጠባቂ ኃይል ለማንሳት በሌሊት መሄድ ስህተት ነው፡፡ከዚያ በፊትም መንገድ ተዘግቶ፣ኮንዶሚኒየም ሲቀማ ዝም መባል አልነበረበትም፡፡

አሁን ግን ከጃዋር ጋር መንግሥት (በተለይም ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ) እልህ ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡ጠቅላይሚኒስትሩን እንደ ውሸታምና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አድርጎ መናገሩ ሳይበቃው፣መደመር የሚለው ነገር በተለይ በኦሮሚያ ፖለቲካ ኃይሎች ውስጥ ተቀባይነት እንዳይኖረው ታትሯል፡፡ ዛሬ መደመር የተሰኘው መጽሐፍ ሲቃጠል የዋለውም ለዚያ ይመስላል፡፡ በነዚህ ሁለት መንግሥታት ፀብ ውስጥ ግን ንፁሀን ይራባሉ፤ይሞታሉ፤ ሥራቸውን ያጣሉ! ፈጣሪ ሆይ ኢትዮጵያን አስባት!

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top