ዛሬም “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” | (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
በቀድሞው አጠራር ወሎ እና ትግራይ ይባሉ የነበሩት ክፍለ ሀገሮች ኩታ ገጠም መልክዐ-ምድራዊ ቁርኝት፣ ስነ-ልቦናዊ ቀረቤታ፣ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ያላቸው ጎረቤታሞች በመሆናቸው፤ የትግራይ ሰዎች ወደ ወሎ፣ ወሎዬዎች ወደ ትግራይ መሄዳቸው የተለመደ ነበር፡፡ መሄድ ብቻ ሳይሆን የሄዱት ሰዎች በሄዱበት ስፍራ ያገኙትን/ያገኟትን፣ ልባቸው የፈቀደውን/የፈቀዳትን ያገቡና ቤተሰብ ይመሰርታሉ፡፡ ልጅ ይወልዳሉ፣ ይከብዳሉ፣ ይድራሉ፣ ይኩላሉ፡፡ የብዙዎቻችን “ወሎየዎች” እና “ትግሬዎች” ማንነት ቢገለጥ በዚህ መልኩ የተዋቀረ ሆኖ ይገኛል፡፡
ይህንን ያነሳሁት አንድ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ጋብቻ የመሰረቱ የወሎ ሴቶች ባሎቻቸው ወደ ትግራይ ዘመድ ጥየቃ ሄደው ዋል፣ አደር፣ ዘግየት ሲሉባቸው “ኧረ ባሌ ቀረ አንቺዬ? ምን ሆኖ ይሆን?” ማለት ያበዛሉ፡፡ በዚህ ጊዜ “ያገሯን ልጅ” ያገባች ወሎዬ “ነግሬሽ ነበረ ተይ ብዬ ተይ ብዬ፤ …… ውሽማ እንጂ ባል አይሆንም ብዬ” በማለት በነገር ነካ ታደርጋታለች አሉ፡፡
ይህንን ሁሉ ያነሳሁት ላለፉት 26 ዓመታት “ተው” ስንላቸው የነበሩት ህወሓት እና አዴፓ/ብአዴን (ትናንት የሰሩት ስህተት አላንስ ብሎ) ዛሬም ከስህተታቸው ሊማሩ አለመቻላቸው ገርሞኝ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን የቀድሞው ብአዴን እና ህወሃት “የፖለቲካ ጋብቻቸውን” ሲያፈርሱ የቀድሞ ቁስላቸውን ጭምር እያደሙ በመግለጫ ሲጠዛጠዙ ሰማንና “ዱሮም ጋብቻው ትክክል አለመሆኑን ነግረናችሁ ነበር፡፡ ሁለታችሁም ዋጋችሁ ነው፡፡ ብቻ የምትወረውሩት ነገር ህዝብ ላይ እንዳያርፍ ተጠንቀቁ” ብለን አለፍናቸው፡፡
ሰሞኑን ደግሞ የትግራይ ክልል “600 የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል አልክም” ማለቱን ሰማን፡፡ (የአማራ ክልል የሚሰጠውን መልስ እየጠበቅን ነው) ወንድሜ አንሙት አብርሃም #Anmut_Abrham እንዳለው ይህንን ሁሉ ጣጣ ያመጣው ህወሓት “ራሱ አቡክቶ በጋገረው ፖለቲካ አገርን ለስንቱ ማፈሪያ ያስረከበ ድርጅት፣ [የዘር] ፖለቲካህ አገር ያፈርሳል ሲባል [ጆሮውን በጥጥ የደፈነ] ድርጅት ዛሬ አገር ሲመሳቀል ማፈር” ሲገባው እንዲህ ያለ ኃላፊነት የጎደለው፣ በዘረኛነት የታጀለ፣ በጠባብነት የተሸፈነ፣ “ጎጠኛ” ውሳኔ ማሳለፍ ከጤነኛ አእምሮ የሚመነጭ ሆኖ አይታይም፡፡
የሚገርመው ነገር በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ትግራዋይ ዛሬም በአማራ ክልል እንደሚኖሩ እንኳ ግምት ውስጥ አለማስገባቸው ነው። ከ600 እና ከ100 ሺዎች የቱ ይበልጣል? የትግራይ መሪዎች የጤና መቃወሱ እየጠናባቸው ሲሄድ “ጓዛችሁን ሸክፋችሁ ወደ ትግራይ ተመለሱ” የሚል ጥሪ ማድረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ሰው ጤናው ሲቃወስ ወደ ጤና ጣቢያ ይወሰዳል፡፡ መንግስት ሲታመም የት ይታከማል?
ዛሬ ደግሞ ምን ገጠመኝ መሰላችሁ፡፡ ለዓመታት የማውቀውና የማከብረው፣ መሀል አገር የተወለደ አንድ “ትግራዋይ” የፌስቡክ ወዳጄ “እኔ በማላምንበት፣ ህወሓት ትፈርሳለች በሚል ፖስት ላይ ታግ አታድርገኝ” አይለኝ መሰላችሁ! ይሄ ወንድሜ ከዓመታት በፊት ዌብ ሳይት ከፍቶ፣ ኢህአዴግን ሲያወግዝና ስለሊበራል ዲሞክራሲ ሲሰብክ የነበረ ሰው ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ግልብጥ ብሎ “ህወሓትን የነካ የማሪያም ጠላት” እያለ ነው፡፡ ይሄን አቋሙን አከብራለሁ፡፡
እሱ ግን ምንም ነገር ከእኔ መስማት አልፈለገም፡፡ “ዴሞክራሲ ማለት የማያምኑበትን የሌሎችን ሃሳብ መስማት ነው” ብዬ ለዚህ ወንድሜ መንገር ልጅ ለእናቷ ምጥ ማስተማር ይሆንብኛል፡፡ ለማንኛውም “ታግ አታድርገኝ” የሚለውን አባባል (“ከፋብሪካ እንደወጣ ሳሙና”) ሰሞኑን እናንተም ከአንዳንድ የፌስቡክ ወዳጆቻችሁ ልትሰሙት ትችላላችሁ ብየ አስባለሁ – እንዳይገርማችሁ!
ጀግናው፣ ኩሩው፣ አስተዋዩ፣ ጨዋው፣ ደጉ፣ ቻዩ፣… የትግራይ ህዝብ እንዲህ ያሉ “የታሪክ አተላዎችን” ተሸክሞ፤ “ምእንቲ ዛ ምጎጎ እታ አንጭዋ ትህልፍ” (ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ) እያለ ነው እየኖረ ያለው! “ጣት ገማ ተብሎ ተቆርጦ አይጣልም” እንዲል አማራ!
ከ40 ዓመታት በላይ ሀገሪቱንና ህዝቧን በጭቆና ስር ያማቀቀው የአጤ ኃ/ስላሴ ዘውዳዊ ስርዓት ተወግዷል፡፡ ጨፍጫፊው ደርግ ወድቋል፡፡ “በህወሃት የበላይነት” ስንሰቃይበት የነበረው የ27 ዓመታት ዘመነ ፍዳ “በመንጋ” ማዕበል ተጠርጓል፡፡
አሁን ያልጠራ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው… ከ4 ኪሎ ቤተ መንግስት ተጠርገው የሄዱት የ“ዘመነ ፍዳ” ባለሟሎች ለመመለስ ላይ ታች ይላሉ፡፡ “ፌዴራላዊ ስርዓቱን እናድን” እያሉ ዳግም ሊያጃጅሉን ከኛው ላይ ቀምተው የወሰዱትን ገንዘብ ይረጫሉ፡፡ ኮርቻው ላይ የተፈናጠጡት “ፈረሰኞች” ከፊሎቹ በ“ተረኛነት” መንፈስ ሊግጡን ይከጅላሉ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ “ፈረሱ ላይ መውጣት የሚችለው አንድ ሰው ነው፡፡ ሌሎቻችን ፈረሰኛውን አጅበን አብረን እንሂድ፡፡ ከተወሰነ ርቀት በኋላ ሌላ ፈረሰኛ ይተካል…” የሚል የለዘበ ሃሳብ ይናገራሉ፡፡
ይህንን ማመን ከብዶን ተቸግረናል፡፡ ምን እናድርግ የመጣንበት የታሪክ ጎዳና ይህንን እንድናምን አይፈቅድልንም… በማመንና ባለማመን መሀል ቆመን ስንወዛገብና እርስ በርሳችን እየተናከስን ስንጯጯህ ለድንገተኛ፣ “ደመ-ቀዝቃዛ” ፈረሰኛ እየተመቻቸን መሆኑን ማስተዋል ተስኖናል…
ለማንኛውም ይሄም ቀን ያልፋል፡፡ እኔ የፈራሁት ይሄ ቀን የማያልፍ መስሎን አንዳችን በሌላው ላይ የምናደርሰው በደል ከልክ በላይ እንዳይበዛና እንዳያስተዛዝበን ነው…
ዛሬም ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ!
–
(ይህ ፅሁፍ የፀሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም)