Connect with us

መደመር – ትርጉምና እሳቤው

በዚህ ሳምንት ለንባብ የሚበቃው "መደመር" መፅሃፍ ውስጥ ለቅምሻ ያህል እነሆ...
Photo: Facebook

ፓለቲካ

መደመር – ትርጉምና እሳቤው

መደመር ስንል ከቂም ከበቀልና ከጥላቻ፣ ለዘመናት ሲያባላን ከነበረው፣ ሲከፋፍልን ከኖረው ክፋት፣ ተንኮልና ምቀኝነት እንላቀቅ ማለታችን ነው።

መደመር – ትርጉምና እሳቤው

“መላዉ የሀገራችን ሕዝብ ነፃነት፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት የሰፈነባት ጠንካራ ኢትዮጵያን እዉን ለማድረግ ታላቅ ትግል አካሂዷል። በዚህም ሳቢያ አዲሱ የለውጥ እመርታ ከሀገራችን ሰማይ ላይ ድንግዝግዙን ገፍፎ ጸዳሉ ከአጥናፍ እስከአጥናፍ እየታየ ነው። የጀመርነው የለውጥ እመርታ ከድንግዝግዝ ወደ ብርሃን፣ ከጭቆና ወደ ነጻነት፣ ከመከፋፈል ወደ አንድነት፣ ከድህነት ወደ ብልጽግና ሊመራን ይገባል። ይህ የለውጥ እርምጃ በወሳኝ የሽግግር ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

በጉዞዉ ሂደት ላይ ጋሬጣ፣ ዕንቅፋትና ተቃርኖ በሞላበት ከባድ አቀበታዊ ጎዳና ላይ ደርሰናል። መንገዱ እልህ አስጨራሽ ቢሆንም አቀበቱን ፈጥኖ መውጣት፣ ወደምንመኘዉ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የማለፊያው ሁነኛ ዘዴ ነው። ትግላችን ወደ ኋላ እንዳይመለስ ጠንካራ የአንድነት ክንድ ያስፈልገናል። የመደመር ጽንሰ ሐሳብ የአዲሱ እመርታዊ ለውጥ ቁልፍ መለያ መርሕ የሆነውም በዚህ ምክንያትም ነው። ለአንድነት አንድ ዓይነትነት አይጠበቅብንም። ሆኖም ከመነጣጠል ድካምና አደጋ የምንድነውም ሆነ የችግራችን መፍትሔ ያለው በአብሮነት ባሕላችን ውስጥ ነው። አብረን ከሆንን አንሰበርም፣ የማንፈታው ችግር አይኖርም። የዕድገትና የብልጽግናችን መሠረትና ዋስትና፣ አብረን ተዋደን እና ተከባብረን መኖራችን ነው። የዛሬ ኃላፊነታችንን በመሸሽ በትናንት ታሪክ ውስጥ ዕድሜ ዘላለማችንን ተኝተን ማሳለፍ አንችልም። ታሪክ ለመማሪያ እንጂ ለመተኛ መዋል የለበትም። ይልቁንም ይህ ትውልድ ከትናንት ታሪካችን ትምህርት ወስዶ ከገባንበት የቀውስ አዙሪት መውጣትን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባዋል። ሀገራችን ወደ ላቀ የልማትና የዴሞክራሲ ጎዳና መግባት የሚያስችላትን የቁጭት ስንቅ ልንሰንቅ ያስፈልጋል። ለተሳካና ውጤታማ ማኅበራዊ እመርታ ምሥጢሩ ከአንድ በላይ የሆኑ ወገኖች የፍቅር አንድነታዊ ጥምረትና መደመር ነው።

የመደመርን ተግባራዊ ፋይዳና ወቅታዊ የሆነ ሀገራዊ ብሎም አህጉራዊ መፍትሄነት ለመረዳት ቃሉን ከቃልነት ባሻገር በቃሉ ውስጥ ታጭቆና ተሰድሮ ያለውን ጥልቅ ጽንሰ ሀሳብ መመርመርና መረዳት ይጠይቃል። የመደመር ሀሳብ ምሁራንና የሀሳብ መሪዎች እየተመራመሩ ቢጠበቡበት፣ የእምነት መሪዎችና የሀገር ሽማግሎች የሞራል ልዕልናቸውንና የማህበረሰብ አድባርነታችውን ተጠቅመው የግልና የጋራ ህሊናችንን ቢሞግቱበት የቃሉ ሙሉ ትርጉምና ክብደት ይበልጥ ሊገባን ይችላል። የኪነ-ጥበብ ሰዎችና ከያኒያን ስሜታችንና ነፍሳችን ልትረዳው በምትችለው ውብ ቃላት፣ ቀለማትና ትርእይት ከሽነው ቢያሳዩን፣ በሀገራችን ያሉ ወጣቶች ከዳር እስከዳር ቀፎው እንደተካበት ንብ በሰላምና እርስ በእርስ በፍቅር በመፈላለግ በትኩስ ጉልበታቸው የተስፋና የአንድነት ጮኸታቸውን ቢያሰሙበት መደመር ምን እንደሆነ ያለ አስተማሪ ልንረዳው እንችላለን። በዳይ የበደሉ ክብደትና የፈጠረው ስቃይ ገብቶት ለበደሉ ሙሉ ኃላፊነትን ወስዶ ይቅርታ ቢጠይቅና ከጥፋቱ ቢታረም፣ ተበዳይም ከቂምና ከበቀል ይልቅ በሰፊ ልብና በንጹህ ህሊና ለበዳይ ይቅርታ በማድረግ ያለፈውን ይቅር ለፈጣሪ ብሎ አዲስ ወንድማማችነትን ለመፈጠር ቢፈቅድ መደመር በመካከላችን ቆሞ የሚሄድ ለራሱ የሚናገር የነጻነትና የብልጽግና አጋራችን ይሆናል።

➕ መደመር ስንል ከቂም ከበቀልና ከጥላቻ፣ ለዘመናት ሲያባላን ከነበረው፣ ሲከፋፍልን ከኖረው ክፋት፣ ተንኮልና ምቀኝነት እንላቀቅ ማለታችን ነው። መደመር በዚህ ጊዜ መቀባበልን መላበስ ይሆናል።
➕ መደመር ስንል ትናንት በታሪካችን ውስጥ በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ከኖሩት ኋላቀር አስተሳሰቦች፣ መናቆሮች፣ የጅምላና የተናጠል ጥላቻዎች መውጣት ማለት ነው። መደመር በዚህ ጊዜ በሀሳብ ልዕልና ማመንና ምክንያታዊ እመርታን መላበስ ይሆናል።
➕ መደመር ስንል ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን በማስወገድ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ለክብሩና ለነጻነቱ መከበር ዘብ መቆም ማለት ነው።መደመር በዚህ ጊዜ ግለሰባዊ ነጻነትና ማኅበረሰባዊ ደኅንነት መላበስ ይሆናል። መደመር ስንል ከዜሮ ድምር ጨዋታ ወጥተን፣ በአንድነትና በአብሮነት መንጎድ፣ ባለን በጎ እሴት ላይ በመጨመር ወደ ከፍታው መዝለቅ ማለት ነው።በዚህ ጊዜ መደመር የሥልጣኔን ጸዳልና የብልጽግናን ጮራና መላበስ ይሆናል።
➕ መደመር ስንል ‹ሁላችንም እናስፈልጋለን፤ከመካከላችን የማያስፈልግ የለም› ማለታችን ነው።በዚህ ጊዜ መደመር የእኩልነትን መጎናጸፊያ ላይ የሰብአዊነትን ካባ እንደ መደረብ ይሆናል።
➕ መደመር ስንል እያንዳንዱ ብሔርና ብሔረሰብ አንዱ ከሌላው ጋር እየሆነ፣ ያለውን ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ጥበባዊና ኢኮኖሚያዊ ጸጋ እየደመረ፤ የሁሉንም የያዘችና በሁሉም የምታጌጥ አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያን መፍጠር ነው።
➕ መደመር ስንል የተከፋፈለና የተበታተነ አቋማችንን ሰብስበን የጋራ አቅጣጫን በመያዝ፣ ሁላችንም በየፊናችን በግልና በቡድን አቁረን የያዝነውን አቅም በአንድ ላይ አዋህደን ለሁላችንም የሚበቃ ሰፊ የእኩልነት፣ የነጻነትና የብልጽግና ሜዳ የምንፈጥርበት የእመርታዊ ለውጥ ስሌት ነው።

መደመር ከክስተትነቱ ይልቅ ሂደትነቱ ያመዘነ፣ ከንግግር ይልቅ ተግባር ላይ ያተኮረ፣ ከእኔነት ይልቅ እኛነት ላይ የተመሰረተ ጽነሰ ሀሳብ ነው። ከመደመር የምንጠብቀው ብዙ መልካም ፍሬ እንዳለ ሁሉ የሚያስከፍለንም ዋጋ ቀላል ላይሆን ይችላል። መደመር በግፊት ያለፈቃዳችን የሚጫንበን ቀንበር ሳይሆን በፈቃደኝነትና በደስታ የምንወስደው የኃላፊነት ሸክም ነው። የመደመርን ጽንሰ ሀሳብ በትክክል ለመረዳትና ለመተግበር በመጀመሪያ ትክክለኛ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ተገቢውን መልስ ልናገኝ ይገባል። አለበለዚያ ጭፍን ተደማሪዎች ወይም ድፍን ተቃዋሚዎች ከመሆን ውጪ አማራጭ አይኖረንም። በሁለቱ መካከል ደግሞ እምብዛም ልዩነት ሊኖር አይችልም። መደመርን ከሥር መሰረቱ በመረዳት ቀላል የአተገባበር አቅጣጫን ለማያዝ ከሚረዱን ጥያቀዎች መካከል የሚከተሉት መሰረታዊ ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል።

1️⃣ #በምን_እንደመር (Possibilities) – መደመር በዋናነት የጭማሪ ስሌት ነው። ይህም ምኔን እምኑ ላይ ልደምር የሚለውን ሀሳብ ያጭራል። የመደመር አስተሳሰብ የመጀመሪያው እሳቤ ሁሉም ሰው ለሌላው ሊሰጥና ሊያበረክት የሚችለው ነገር አለው የሚል ነው። ሰው ከበጎ ፈቃዱ፣ በመልካም ቃሉና በሰናይ ግብሩ ሊደመር ይችላል። በጎ ፈቃዱ ካለን መናገርና ማድረግ በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንኳ ቢያንስ አሉታዊና አፍራሽ ነገሮችን ላለመናገር፣ ላለማድረግና ላለመተባበበር መወሰን እንችላለን። ይህ የመደመር ጽንሰ መነሻ መሰረት ነው። የአቋም ድማሮ ባለበት የአቅም መደመርን መፍጠር አያዳግትም። የያዝነው የመደመር እመርታዊ ለውጥ ሁነኛ መገለጫዎችና መሳሪያዎች ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር ናቸው። እነዚህን ሶስት ተያያዥ ሀሳቦች – (ሠ)ላም – (ይ)ቅርታ እና (ፍ)ቅር በጥምረት ‘የመደመር ሠይፍ’ ልንላቸው እንችላለን። መደመር የሚያነሳው ሰይፍ የጥላቻ፣ የጥፋትና የመግደል ስላይደለ ከሁሉም የበረታና በውጤቱም አስተማማኝ ነው። በመደመር ጦርነትና ጠብ ሳይሆን ሰላምን እንሻለን። በመደመር ቂምና በቀል ሳይሆን ይቅርታና እርቅን እናውጃለን፤ እናደርጋለን። በመደመር ጥላቻና ፍርሃትን ሳይሆን ፍቅርንና አንድነትን እናራምዳለን፤ እንመሰርታለን። ስለዚህም በምን ልደመር ለሚል ሰው ይቅርታ በማድረግና በመስጠት፣ ሠላም በመፈጠርና የእርቅ ወኪል በመሆን፣ እንዲሁም ሌሎች በሰላምና ያለስጋት እንዲኖሩ እንፈቅዳለን፤ ያለፈውን ትውልድ በማክበር ለሚቀጥለው ትውልድ ችግር ሳይሆን ጥሪት ለመተው በመታተር እንኖራለን።

2️⃣ #እንዴት_እንደመር (Process) – መደመር አንድም የከፋፈለንንና ያራራቀንን ያለፈ ሰንኮፍ አውጦቶ ለመጣልየሚደረግ ትግል ነው፤ ደግሞም የወደፊቱን ህልውናችንንና ማንነታችንን ወደ ተሻለ ቦታ ለማድረስ አብሮነታችንን መኮትኮትና በግለሰቦች ነጻነትና የሰብእና ልቀት ላይ የተመሰረተን ህብሩን ያለቀቅ ጽኑ
ማህበረሰባዊ አንድነትን ለመፍጠር የሚደረግ የእመርታ ሂደት ነው። ስለዚህ የራሳችንን የተሻለ ማንነታት በመገንባት ወደ ሌሎች መድረስና መጣመርን ይጠይቃል። ዋጋ በመክፈል ከሌሎች ጋር የአቋምና የአመለካከት መጣጣም ለማምጣት መስራት ነው። ያለንን ከሌሎች ጋር በመካፈልና በማጣመር ወደ ተሻለ ብልጽግናና አብረን የምናሸንፍበት የሕይወት ደረጃ መድረስ ነው። የጀመርነውን እመርታዊ ለውጥ ዐበይት እሴቶች – ማለትም ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅርን የግልና የማህበረሰባችን መግባቢያ ቋንቋ በማድረግ ግባችን ወደሆኑት እኩልነት፣ ነጻነት አንድነትና ብልጽግና ለመድረስ ተገቢውን ሁሉ ማድረግና ከዚህ የሚያዘገዩንና የሚያፋልሱንን እክሎች ጸንቶ መቃወም ነው። ያለፈ ክፉ ፋይሎቻችንን ለአንዴኛ ለመጨረሻ ጊዜ ዘግተን ወደ ሥልጣኔ ከፍታ በእመርታ ለመውጣት የሚረዱንን ተግባሮች ከራስ ወደ ቤተሰብ፣ ከአካባቢ ወደ ሀገር በማስፋፋት፣ ከአህጉራችን ተርፈን ለአለም ህዝቦች የምናበረክተውን ስጦታ ወደ ማፍራት በመገስገስ ነው።

3️⃣ #ለምን_እንደመር (Purpose) – የመደመር ግብና ፍሬው ብዙ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ባለመደመር ጦስ ከሚመጣ መከፋፈልና ለመጠፋፋት መነሳት፣ ከበቀልና ማለቂያ ከሌለው ግጭት የምንድነው በመደመር ነው። በመደመራችን ትልልቅ ችግሮቻችን ይፈረካከሳሉ፣ ተግዳሮቶቻችን ወደ እድል ይቀየራሉ። በመደመር
የናቁንና ለውድቀታችን የሰሩ ኃይሎች ሊያከብሩንና እንደ እኩያ ባልንጀራ ሊያዩን ይጀምራሉ። በመደመር ለየብቻ ሆነን ልንሆንና ልንሰራ ያልቻልናቸውን ነገሮች ባጭር ጊዜና በተሻለ ፍጥነት እንሰራቸዋለን። ብንደመር ሁላችንም እንደተረት ስንሰማት የነበረችውንና የሁላችንም ሕልም የሆነችውን አንዲት የታፈረችና የተከበረች ሰላማዊ ኢትዮጵያ እንገነባለን። ብንደመር ለአፍሪካ የለውጥ ብርሃን ለዓለም ደግሞ የለውጥ ፈርጥና ምሳሌ እንሆናለን። ብንደመር ስደተኞች ሳይሆን እንግዳ ተቀባዮች፣ በድህናትና በጉስቁልና የምንታወቅ ሳይሆን በብልጽግናና በለጋስነታችን እንዘከራለን። ብንደመር የጥንት ስልጣኔያችንና ከወደ ፊት የታላቅነት ህልማችን ጋር የምናገናኝ ታልቁ ትውልድ የሀገር መሠረት ጣዮች እንባለለን። በዓለም ላይ ያልተደመረ ታላቅ ሕዝብና ስልጣኔ ኖሮ አያውቅም ወደ ፊትም ሊኖር አይችልም።

4️⃣ #ማን_ይደመር (Person) – መደመር ማንንም የሚያገልል ማንንም የሚያስገድድ ሂደት አይደለም። እርቅና ሰላምን የመረጠ፣ ፍቅርና አንድነትን የወደደ ብሎም ለነጻነትና እኩልነት፣ ለብልጽግናና ሰብዐዊነት የቆመና የቆረጠ ሁሉ ተደማሪ ሊሆን ይችላል። የመደመር ሜዳው ሰፊ፣ እድሉ ብዙ መንገዱም ልዩ ልዩ ነው። ስለዚህም አልፈልግም አሻፈረኝ ከሚልና ለግል ጥቅሙና አላማው ማስፈጸሚያ ፈልጎ ልደመር ከሚል በቀር የመደመር በር ለሁሉ ክፍት ነው። ህጻናንት በፍቅራቸው፣ ወጣቶች በብርታታቸው፣ ጎልማሶች በልምዳቸው አዛውንቶችም በጥበባቸው ሊደመሩ ይችላሉ። ነጋዴ በገንዘቡ፣ መምህር በእውቀቱ፣ ገበሬ በምርቱ፣ ዳኛ በፍትሁ፣ ከያኒ በጥበቡ ሊደመር ይችላል። አፋሩ ከጋንቤላው ጋር፣ ቤንሻንጉሉ ከሶማሌ፣ አማራው ከአደሬው፣ ትግራዋዩ ከሀድያ፣ ኦሮሞውም ከጉራጌው ቢደመር ተጠቃሚው ሁላችንም ደግሞም የምወዳት ሀገራችን ናት። ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከመበጣጠስ ቢጣመሩ፣ የደርግና የኢህአዴግ ባለስልጣናት በይቅርታና በአርቅ በአንድ ማዕድ ቢቀመጡ፣ ቤተ እምነቶች ልዩነታቸውን አክብረው በሀገር፣ በግበረገብና በዜጎቻችን ጉዳይ ላይ እጅ ለእጅ ቢያያዙ የማይደመር ላይኖር ነው። መደመር አግላይነትና ሌላውን ጥላሸት ከመቀባት የራቀ ነው።

5️⃣ #መቼ_እንደመር (Program) – የመደመር ሀሳብ በክስተትነቱ ያስደመመንን ያህል ተግባራዊነቱ ሂደትና አንዳንዴም እልህ አስጨራሽ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ፈጥኖ በመደመር ስሌት ውስጥ በጭፍን ከመቀላቀል ተረድቶና ሁለንተናን ሰጥቶ ጊዜን ወስዶ መደመር የተሻለ ውጤት ሊኖረው ይችላል። የተደመሩ ሲበዙ መደመሩ እየቀለለ ይመጣል። መደመርን የግዴታ ፖለቲካ ሳይሆን የውዴታ እንቅስቃሴ ብናደርገው ተደማሪዎች በፍጥነትም በቁጥርም ሊበዙ ይችላሉ። ከላይ በመሪዎች ደረጃ፣ ከታችም በማህበረሰብ ደረጃ የመደመር ጽንሰ ሀሳብና ተግባራዊ መንገዶቹ እየተብራሩ ሲመጡ መደመር ሁሉንም የሚስብ ማግኔት ይሆናል። ዛሬ ያለው የመደመር ጅረቶች ተዋህደው ትልቁን ወንዝ የሚፈጥሩበት ጊዜ እስኪመጣ ግን ትዕግስትና የማያቋርጥ ጥረት ይጠይቃል።

6️⃣ #የት_እንደመር (Platform) – በመደመር የእመርታዊ ለውጥ ሀሳብ ውስጥ አንዱ የተደማሪዎች ፈተናና መደናገር ሊሆን የሚችለው ምኑ ላይ ወይም ከማን ጋር ነው የምደመረው የሚለው ሊሆን ይችላል። እራስን አጽድቆና አትልቆ ሌላውን ደግሞ አኮስሶና አዋድቆ የማየት ችግር ስላለብን ነው። ለራሳችን ካለን በጎነትና መልካም እይታ ቀንሰን ለሌሎች በመስጠት፣ በሌሎች ላይ ካለን አብጥልጥሎና አብጠርጥሮ የመፈተሽ ልምድ ደግሞ ቀንሰን በራሳችን ላይ ብንተገብረውከማንም ጋር ለመደመር ዝግ አንሆንም ነበር። ከሌብነትና ከዘቀጠ ሥራ ጋር መደመር መቀነስ ነው። ከጥላቻና ከጥፋት ጋር መደመር መውረድ ነው። ይቅርታና እርቅ፣ ሰላምና አንድነት፣ በጎነትና ቅንነት፣ መልካም ሥራና ልማት፣ ፍቅርና እኩልነት መግባቢያ ቋንቋና የመደመር ልኬቶች በሆኑበት ቦታ ሁሉ መደመር ያስፈልጋል። በሀገራችን የተፈጠሩትን የመከፋፈል ሰው ሰራሽ ድንበሮች ለማፍረስ፣ በቡድን አስተሳሰብና በስማ በለው የተፈጠሩ የጀማ ጥላቻና ፍረጃን ለማስቀረት በተጀመሩ እንቅስቃሴዎችና ጅማሮዎች ሁሉ መተባበር ትክክለኛው የመደመር ቦታ ነው። የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የሥራ ፈጠራ ተግባራትን መደገፍም ሆነ መሳተፍ ትክክለኛው የመደመር ቦታ ነው። መጪውን ትውልድ አንድ ጥልቅ አገራዊ ፍቅር እንዲኖረውና የሰውን ሁሉ እኩልነትና የሰብዕና ልዕልና ማስተማርና ማቀራረብ ባለበት ቦታ ድርሻን መወጣት ትክክለኛው የመደምር ቦታ ነው። ያለንን የሥራ ባህል ለመለወጥ፣ የንጽህናና አካባቢን የመንከባከብ ልምድ ለማዳበር በሚደረጉ ተግባራት መሳተፍና የበኩልን እገዛ ማድረግ የመደመር ከፍታ ነው።

7️⃣ #ባንደመርስ (Problems) – መደመር የግልም ሆነ የቡድን ምርጫችን መሆኑ እሙን ነው። ሌላው አማራጭ ደግሞ አለመደመር ሲሆን ያለመደምርን ዳፋና ሰቆቃ በመፍረስ አፋፍ ላይ ሆነን ስላየነው መደመርን አማራጭ የሌለው ምርጫ አድርገን ማየቱ ተገቢ ነው። ከይቅርታ ይልቅ ቂም፣ ከእርቅ ይልቅ በቀል፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻና ፍርሃት፣ ከሰላምም ይልቅ ጠብ፣ ግጭትና ጦርነት በመደመርና ባለመደመር መሀል ያለውን ልዩነት የሚያሳዩ የምርጫዎቻችን መንገዶች ናቸው። ውጤታችውም እንደመንገዱ ሁሉ ብርሃን ከጨለማ እንደሚለይ የተለያዩ ናቸው። ይህም ያለመደመር ውጤቶች ከነጻነት ይልቅ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የፍርሃት ኑሮና ሽሽት፣ ከብልጽግና ይልቅ ድህነትና ጉስቁልና፣ ከእኩልነት ይልቅ ኢፍትሃዊነት፣ አድልዎና ቡድንተኝነት ይሆናል። ይህም ወደማያቋጥ መከፋፈልና መፈራረስ የሚያመጣ ጎዳና ሊሆን ይችላል። የመምረጥን ነጻነትና መብትን ባለመደመር ለመግለጽ መሞከር ሌላውን ሳይሆን ራስንም ወደ ጥፋት የሚወስድ አፍራሽ ጎዳና ነው። ይህንን የመደመር ጽንሰ ሀሳብ ከግለሰብ እሰከማህበረሰብ፣ ከቤተሰብ እስከሀገር ብሎም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አውድና ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በመበታተን አፋፍ ላይ ሆና ሕዝቦቿም በዘርና በሀይማኖት፣
በመደብና በፖለቲካ አንጃ ለመቧጨቅ በሚያስፈራ ሁኔታ ላይ ደርሰው ነበር። ይህንን ጥልቅ የመገፋትና የግፍ፣ የቂምና የበቀል፣ የቁጣና የእሮሮ ሀይል ሙሉ ለሙሉ አጥፍተን አዲስ ጅማሬ ከፈለግን ከመደመር ሌላ ምን አማራጭ አለን? ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲመጣ፣ መንግስት ወርዶ መንግስት ሲወጣ ሀገርና ህዝብ ግን ይሄው ሁሉን እያሳለፈ ዛሬም አለ። የዚህ ትውልድ ታላቁ ጥሪ የመበተንና በሌላው ላይ የመሰልጠን፣ ባለፈ ታሪክ ላይ ሙጭጭ ብሎ ወደፊቱን በሚያጨልም ግብግብ ውስጥ መግባት ሳይሆን እጁን ለሥራ ልቡን ለፍቅር አጠንክሮ የመደመርን ጠመዝማዛና ረጅም ጉዞ በጥንካሬ መቀጠል ነው። በአገራችን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ውስጥ ተገቢውን ቦታ እያጣ የመጣው አንዱ የዘመናዊነት መገለጫ ወንድማማችነት ነው። ወንድማማችነት ማለት ከአካባቢያዊ ወይም ከራስ ቡድን ወጥቶ ለማንኛውም የሰው ልጅ በጎ ምልከታ ማሳዬትና በወንድምነት መመልከት ነው። በአገራችን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ውስጥ እኩልነትና ነፃነት የተቀነቀኑትን ያክል ወንድማማችነትም ቢቀነቀን ኖሮ አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ የተለዬ በሆነ ነበር። የዘመናዊነት መንገድ እንኳንስ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ይቅርና ከየትኛውም የዓለም ክፍል የሆነ ሰው ስለሌላኛው የዓለም ክፍል ችግርና መከራ የሚጨነቅበት እንደበፊቱ የሞራል ድንበር አበጅቶ መገዳደል የሌለበት የቅርብ ዘመናት የሰው ልጅ ትሩፋት ነው።

በአገራችን የብሔሮችን የዕኩልነት ጥያቄ ለማስተናገድ የተጓዝንበት መንገድ ከትብብር ታሪካችን ይልቅ የፉክክር ታሪካችን ጎልቶ እንዲወጣ ስላደረገው የወንድማማችነት ጉዟችን ላይ ጥላ አጥልቶበታል። የእኩልነትን ጉዳይ ከወንድማማችነት ጋር አስተሳስረን ከሰራንበት ኢትዮጵያ ለሁላችን ትበቃለች። ሌላው በአገራችን በብሄርተኝነት መክረር ምክንያት እየተሸረሸረ የመጣው አንዱ ነገር አርበኝነት ነው። ብሔርተኝነት በብሔር ደረጃም ይሁን በአገር ደረጃ ከሌሎች ጋር የማፎካከር ባህርይ ሲኖረው አርበኝነት ግን ራስን በመገንባትና ራስን በመከላከል ላይ ያተኮረ የአገር ወዳድነት ባህሪ ነው። ባለፉት አመታት በአገራችን የዜጎች የአርበኝነት ባህሪ እያሽቆለቆለ መጥቷል። ሃገራቸውን ትተው በገፍ የሚሰደዱ ዜጎች፣ የገዛ አገራቸውን ተደራጅተው የሚዘርፉ ቡድኖች፣ የአገሪቱን ቁልቁለት ተቀምጠው የሚመለከቱ ይባስ ብለውም ቁልቁለቱን ለማባባስ የሚዶልቱ ልሂቃን ወዘተ የአርበኝነት መላላት ማሳያዎች ናቸው። ስለዚህም አገራችን በልማትና በዴሞክራሲ እንድትሻገር ካስፈለገ የህዝቦችን አገር ወዳድነት በመጨመር በአገራቸው ዕድገትና ህልውና ላይ የማይደራደሩ አርበኞች ማድረግ ያስፈልጋል።

አሁን በእጃችን ያለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ታላቅ መሥዕዋትነት የተከፈለባት የጋራ ትግላችን ውጤት ናት። አስጎምጂ ጅማሮ በጨለማ ተውጦ እንዳይበላሽ ግን ሆደ ሰፊነት፣መቀባበልንና የተሻለ የመደማመጥ የፖለቲካ ባሕልን በሀገሪቱ ሕዝቦች ልብ ውስጥ መዝራትና ማለም ለምን ይጠይቃል። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ያልተቀናጀና ያልተደራጀ፣ ያልተባበረና ያልተሳሰበ ሕዝብ፣ የውስጥ ችግሮቹን መፍታትም ሆነ የውጭ ጥቃትን በብቃትና በንቃት መመከት ፈጽሞ አይቻለውም። ማረጋገጥ የምንፈልገውን ፈጣን ልማት በተናጠል ጉዞና ከአንድ አቅጣጫ ብቻ በሚመጣ መፍትሔ ሊረጋገጥ አይችልም። ስለዚህም

▪️ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓታችንን ወደ ሙሉ ቁመናው እና መገለጫው በቶሎ ማሸጋገር የሚያስችል ሰፊ የፖለቲካ ምኅዳር ማስፈንና
▪️የሲቪል ማኅበረሰብና የምሁራን ተሳትፎን የሚያጠናክሩ አሠራሮችንና ዕድሎችን መዘርጋት ይኖርብናል።

ይህም በመጀመሪያ በዴሞክራሲ ትግበራችን ሂደት ውስጥ ያሉ እንከኖችን በጋራ የማረም እና የማከም ኃላፊነትን መውሰድ ይጠይቃል። አስቀድሞ ግንሥልጣን፣ ታሪካዊ ኃላፊነትና የባለቤትነት መብት ሁሉ የአንድየፖለቲካድርጅት ብቻ ንብረት ከሆነበት ጠባብ አዙሪት መላቀቅን ይጠይቃል። ሁሉም አካል የዜግነት ኃላፊነቱን የድርሻውን ያህል በመወጣት ወቅቱ ለጋረጠብን በሽታዎች ሁለንተናዊ ፈውስ ለማግኘት መረባረብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ አመራር ቀዳሚ ጉዳይ ሊሆን ይገባል። ብንወድም ብንጠላ ኢትዮጵያዊነት ተፈትሎ የተሸመነበት ድርና ማግ ባለአንድ ቀለም ነጠላ ሳይሆን በኅብረ ቀለማት ያሸበረቀ ደርዘ ብዙ ረቂቅ ጥበብ ነው። ለዚህ ነው አንድነታችን ኅብራዊ አንድነት ነው የምንለው። የተለያዩ ቀለማት ሸምነውት የተሠራ ባለ ብዙ ቀለም ረቂቅ ጥበብ ነው። የዘር ማንነት ይለያየዋል ያልነውን ሕዝብ በእምነት ድልድይ ተሻግሮ ሲዛመድ እናገኘዋለን። የእምነት አጥር ቅጥር ገንብቶ እዚያና እዚህ ተራራቀ ስንል በጋብቻና ኑሮ ተዛምዶና ተጎራብቶ፣ ተቀራርቦና ተቀላቅሎ መኖሩን እናያለን።

ለዚህም ነው፣ ኢትዮጵያችን ከመደመር ውጭ፣ ከአብሮነት፣ ከአንድነትና ከኅብረት ውጭ ሌላ አማራጭ የላትም የምንለው። ብዙ ነን፤ ነገር ግን አንድ ሆነንእንነሣ። ልዩነታችን ያፈጠጠ ቢመስልም የአንድነትና የኅብር ድምጻችንን እናሰማ። ልዩ ልዩ ባሕሎቻችንን፣ እምነቶቻችንን፣ ታሪኮቻችንን፣ ቋንቋዎቻችንን፣ ማንነቶቻችንን እንደምርና ለሁላችንም የምትሆን አንዲት ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያን እንገንባ። ኢትዮጵያ የየብሔረሰቡ የሙዚቃ መሣሪያ በአንድ መድረክ ለአንድ ዜማ እንደምታቀርብ ኦርኬስትራ ናት።እያንዳንዳቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች የየራሳቸው ታሪክና ድምጽ አላቸው። ሁላችንም የምናዳምጠውን ውሁድ ውብ ሙዚቃ የሚያወጡት ግን በአንድ ቅንብር ተስማምተው ለአንድ ዓላማ ሲያዜሙ ነው። ያኔ እንኳን እኛ የምናውቃቸው ባለቤቶቹ፣ የማያውቋቸው የባዕድ ሀገር ሕዝቦችም በተመስጦና በአርምሞያዳምጧቸዋል።

በፖለቲካ ሰነዶቻችን ላይተደጋግሞ እንደተገለጸው ድርጅታዊ ዐቋማችን ለሕዝቦች መናቆር ሳይሆን በእኩልነትና በመብት መከበር ላይ ለተመሠረተ አንድነትና ለአዲስ ኢትዮጵያዊነት ጸንቶ ይቆማል። ሕዝቦች እኩልነታቸውና መብታቸው ተከብሮ፣ ሰላም ልማትና ብልጽግና የሚያገኙት፣ አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ ሲገነቡ ብቻ እንደሆነ ያምናል። ይህችን የጋራ ቤታችንን በጋራ ስንገነባ ብቻ ነው የእያንዳንዱ ብሔር ጭቁን ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚከበረው የሚል ጥልቅ የጋራ ግንዛቤም አለን። ለአካባቢያዊ ማንነትና ተያያዥ መብቶች የምናከናውናቸው ነገሮች የጋራ ጎጇችንን የሚንድ፣ የሚሸረሽርና የሚያዳክም እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግን በመነሻነት ይወስዳል፤ ያምናልም። ስለሆነም ለብሔሮች መብትና እኩልነት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ከዚህ የጋራ ቤት ግንባታ ሳይነጠል የሚፈጸምና የሚከናወን እንጂ የእያንዳንዱን ብሔርና ጭቁን ሕዝብ መብትና ጥቅም በተናጠል ለማሳካትና ለማራመድ በሚደረግ ሙከራ እንደማይሆን በጥብቅ ያምናል። ይልቁንም የእያንዳንዱን ብሔር ጭቁን ሕዝብ መብትና ጥቅም በተናጠል ለማራመድ የሚካሄድ ሙከራ ዞሮ ዞሮ የሁሉም ሕዝቦች መብትና ጥቅም የሚከበርበት ብቸኛ አማራጭ የሆነውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ይንዳል። ይህ ደግሞ ሁሉም ብሔሮችና ጭቁን ሕዝቦች ለእልቂት፣ ለዴሞክራሲ ክሥረትና ለከፋ
ድህነት እንዲጋለጡ ያደርጋል።

መደመር እንደ ድርጅት ከሌሎች የሚለየንን መተዋወቅን እና ልምምድን መሠረት ያደረገ ኅብረትና መብትን በዐመፃ ሳይሆን በፍቅር መቀዳጀት ነው።የመደመር መንገድ በሰላም ትታጀባለች እንጂ ሁከት አይዳበላትም። ድሉም የአንድ ወገን ማግኘትና የሌላኛው ወገን ማጣት ሳይሆን የሁላችንም ማሸነፍ፣ ማግኘትና በጸጋ የመሞላት አቅጣጫ ነው። በጋራ ነጻ የምንወጣበት የፍቅርና የዕውቀት መንገድ ነው። ስንደመር ከተበታተነና ከሚጋጭ የዐቋም ግጭት ወጥተን በአንድነት ለአንድ ዓላማ መትመም ይቻላል። ስንደመር በየግል ከወረድንበት የዐቅም ማነስና ደካማነት ተላቀን በጋራ በፈጠርነው የላቀ በርታት ያሸነፉንን ችግሮች ሁሉ በቀላሉ እናሸንፋቸዋልን። በመደመር ክፉንና ጎጂውን ነገር ቀንሰን፣ በጎውንና ጠቃሚውን ተካፍለን ወደላቀ የብዜት ስሌትና ፈጣን ስኬት ለመግባት እንችላለን። የወደፊቱን የዕድልና የብልጽግና በር መክፈት የሚቻለውም በዚህና በዚህ አካሄድ ብቻ ይሆናል።

መደመር የኢህአዴግ እሴቶችና ባህሎች የሚያጠናክር ፍልስፍና ነው፡፡ነባር የኢህአዴግ እሴቶችተራማጅነት፣ ዲሞክራሲያዊ አንድነት፣ ህዝባዊነት፣ ልማታዊነት ሲሆኑ የድርጅቱ ባህሎች ደግሞ የዳበረ የሂስና ግለሂስ ልምድና ተሞክሮ፣ ሐሳብን በነፃነት የማንሳትና የመተጋገል ባህል፣ ከምንም ነገር በላይ በድክመቶቹ ላይ የሚያነጣጥር ድርጅት፣ ከየተግባር ምዕራፉ እየተማረ ለቀጣይ ድል የሚተጋ ድርጅት፣ በስኬቶች የማይኩራራ በመሰናክሎች የማይደናገጥ ድርጅት፣ ከሕዝብ ጋር ተቀራርቦ የመስራት እምነትና ልምድ ያለው ድርጅት፣ በየምዕራፉ ውስጣዊ ጥንካሬን በግምገማ ራሱን በራሱ እያረመ የመሄድ ባህል ያለው ድርጅት መሆኑ ነው፡፡ የኢህአዴግ ወቅታዊ ችግር ደግሞ የኔትዎርክና አለአግባብ መጠቃቀምና መጠቃቃት መበራከት፣ የውሸት ሪፖርት መበራከት፣ ውጤታማ ያልሆኑ ስብሰባዎች መብዛትና ረጅም ጊዜ መውሰድ በእህት ድርጅቶች መካከል መጠራጠር መጀመር፣ የአመራሩ ህዝባዊ ወገንተኝነት እና ተራማጅነት መሸርሸር ናቸው፡፡ ስለዚህ የመደመር ፍልስፍና ለዘመናት ድርጅቱ ያዳበራቸው ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የመሸርሸር አደጋ ውስጥ የገቡትን እሴቶችን (ህዝባዊነት፣ተራማጅነት፣ዲሞክረሲያዊ አንድነት…ወዘተ) የመላበስ፣ በመርሆች የመገዛትና ባህሎችን በዕለት-ተ-ለት እንቅስቀሴ ውስጥ ተዋህዶ የመኖርና የመስራት ሁኔታ ነው፡፡ በመሆኑም መደመር በአዲስ የፖለቲካ ትርክት አደጋ ላይ የወደቁትን ነባር የኢህአዴግ እሴቶች፣መርሆችና ባህሎች መልሶ እንዲያገግሙ የማድረክ እንጂ የተኪነት ሚና የለውም፡፡”
—//—
(ምንጭ :-THE FINFINNE INTERCEPT)

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top