ከማድሪድ እስከ ወንጪ፤ ከ174 መንደሮች ጋር የተወዳደረው ወንጪ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር ተብሎ ተሸለመ፡፡
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬቲዩብ)
በሀገረ ስፔን ማድሪድ ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ያለው 24ኛው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደርን አሸናፊ ይፋ አድርጓል፡፡ 75 ሀገራት እኛም ምርጥ የቱሪዝም መንደር አለን በሚል ካቀረቧቸው 174 መንደሮች አንዱ ወንጪ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወንጪን ምርጥ የቱሪዝም መንደር ናት ብላ አቅርባ ግን አላፈረችም፡፡ ወንጪ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር ተብላ ተሸልማለች፡፡
ማድሪድ ጉባኤው ላይ ከኢ.ፊ.ዲ.ሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ጋር አብረው የታደሙት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሌሊሲ ዱጋ ታድመው ሽልማቱን አብረው ተቀብለዋል፡፡ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በወንጪና በአካባቢው ሰፊ የማስተዋወቅ ስራ በመስራት የወንጪን የጎብኚ ማዕከልነት ለማጉላት እየሰራ ቆይቷል፡፡
የዓለም ቱሪዝም ድርጅት እነኚህ የቱሪዝም ምርጥ መንደሮች በዚህ ክብርና ስም ራሳቸውን አስተዋውቀው ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማሰብ የሚያጎናጽፋቸው ስም ነው፡፡
የወንጪን በዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደርነት ማሸነፍ አስመልክቶ ዛሬ በወንጪ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት እንደ ማድሪድ ሁሉ ኢትዮጵያዊቷ መንደር የአሸናፊነቷን ዋንጫ ስለማንሳቷ በተለያዩ ኩነቶች አዲሱን ስያሜዋን አብስራለች፡፡ ሚኒስትሮች፣ የክልል አመራሮች፣ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ፣ የዞን አመራሮችና የአካባቢው ማኅበረሰብ የተገኙበት ይኽ የማብሰሪያ ኩነት ከማድሪድ ወዲህ የተከናወነ የወንጪ ዳርቻ መርሃ ግብር ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ካካተታቸው አካባቢዎች አንዷ የሆነችው ወንጪ በርካታ ጸጋዎች ያሏት ለአዲስ አበባ በቅርበት የምትገኝ መዳረሻ ናት፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የኢኮ ቱሪዝም ማኅበሩ ከሚሰራቸው ሥራዎች አንዱ የኾነው ንብ ማነብ ፍሬ አፍርቶ ወደ ጣሊያን ሀገር ማር መላክ መጀመራቸውን ለታዳሚው ገልፀዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሊሴ ጫሊ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፍት መልዕክት ሽልማቱ በሀገራችን ለሚገኙ የማኅበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻዎች መነቃቃት የሚፈጥርና የጀመርነው ማኅበረሰብ ተኮር የቱሪዝም ልማት ለውጤት እንደሚያበቃ ገልፀዋል። ሚኒስትሯ “አካባቢው ለሽልማት ያበቃውን እሴት ጠብቆ እንዲያስቀጥል አደራ እላለሁ” ብለዋል።
ሽልማቱን በማድሪድ ተገኝተው የተቀበሉት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሌሲሴ ዱጋ ከስፍራው ባስተላለፍት መልዕክት “በምድር ላይ ከምወዳቸው ቦታዎች አንዱ የሚገባውን እውቅና በማግኘቱ ምን ያህል ደስተኛ እንደሆንኩ መናገር እፈልጋለሁ” ሲሉ ባሳለፍነው መስከረም የሚመሩት ተቋም ምርጥ መዳረሻ ብሎ የሸለመውን ወንጪ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ መመረጥ ለአባል ሀገራቱ ምስጋና በማቅረብ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ልምድ በመነሳት በቀጣይም በርካታ መንደሮቿን ከዓለም ጋር አገናኝታ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም ከተማነቷን የምታረጋግጥበት ቀን ቅርብ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ወንጪን እንዲህ ላለው ክብር ለማብቃት የውድድሩን ማመልከቻ ከመሙላትና አስፈላጊውን ሰነድ ከመላክ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን የሰሩ ሀገር ወዳዶች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ በድጋሚ ለዚያ ደግ እንግዳ ተቀባይ የወንጪ ሰው እንኳን ደስ ያለህ ብያለሁ፡፡