አፍሪካ ፓርክስ በኦሞና ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርኮች፤
ይህ ታላቅ የምሥራች ነው!
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
ትናንት መልካም የምሥራች ሰማሁ፡፡ አፍሪካን ፓርክስ በጋምቤላና ኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች መሥራት የሚችልበትን የስምምነት ሰነድ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ተፈራርሟል፡፡
አፍሪካን ፓርክስ ለኢትዮጵያ እንግዳ አየደለም፤ ለውጥ አሳይቶ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋምን የመስጋት አልፎም የመጥላት መንፈስ በትሩን ያሳረፈበት ነው፡፡ የምንቀናባቸው የጎረቤት ሀገር ፓርኮች ብዙ ተጠቅመዋል፡፡ እኛም አብሮ በነበረን የቀደመ ቆይታችን ብዙ ቱሩፋቶችን አግኝተናል፡፡
የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ ብዙ ገንዘብ ብቻ አይደለም የሚፈልገው እውቀት ያሻዋል፤ ልምድና ጥበብ ለውጤታማነቱ አስፈላጊ ናቸው፡፡
እነኚህ አሁን ስምምነት የተደረገባቸው ሁለት ፓርኮች ሀገር መቀለብ የሚያስችል ትልቅ አቅም ያላቸው የኢትዮጵያ የባለጸጋነት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ግን ተደብቀዋል፡፡
ትናንት ጥቅምት ሲገባ በመጀመሪያው ቀን ግን ደስ የሚል ዜና ሰማን፡፡ ሁለቱ ተቋማት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ በባለስልጣኑ አዳራሽ የተከናወነው ይህ የጋራ ስምምነት በዋናነት በጋምቤላና ኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች መልሶ ማቋቋምና አስተዳደር ያካትታል፡፡
በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራና በአፍሪካ ፓርክ ኔትወርክስ ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ፒተር ዊትኒ መካከል የተፈረመው አብሮ የመስራት ስምምነት አፍሪካ ፓርክስ ያለውን ልምድ መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች በኢትዮጵያ አንጋፋዎቹ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ ይተገበራል፡፡
እነኚህ ብሔራዊ ፓርኮች በዱር እንስሳት ብዛትና ስብጥር በቆዳ ስፋትና ቢሰራባቸው ከዓይነተ ብዙ የቱሪዝም ምርቶች ጋር ባላቸው ትስስር የመጪው ዘመን የኢትዮጵያ ማዕድን ናቸው፡፡
አፍሪካ ፓርክስ ኦሞና ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ከጥበቃና ቁጥጥር ስራ ባሻገር መሠረተ ልማታቸው ጥሩ የሆነ ማኅበረሰብን ያሳተፈ የተፈጥሮ ጥበቃ ሥርዓት የሚተገበርባቸውና የቱሪዝም ልማት ላይ ስኬታማ የሆኑ ፓርኮች እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡
ብሔራዊ ፓርኮች አሁን በኢትዮጵያ መንግስት ከሚመደብላቸው ዓመታዊ በጀት በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ኢንቨስትመንት በየዓመቱ ይመደብላቸዋል፡፡ ምናልባት ይሄ ብሔራዊ ፓርኮቹን ለሚያውቅና ሲቆጭ ለኖረው ቤተሰብ ታላቅ የምስራች ሲሆን በሌላ በኩል ነገ ከነገ ወዲያ ውጤቱን ለሚሰማውና በቱሩፋቱ ለሚጠቀመው ሀገር ደግሞ ታላቅ ተስፋ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡
አፍሪካ ፓርክ ለትርፍ ያልተቋቋመ የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት ሲሆን ከመንግስትና ከጥበቃ ቦታዎች ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር ጥበቃ የሚደረግላቸውን አካባቢዎች መልሶ የማቋቋም እና የረዥም ጊዜ አስተዳደር ሥር በቀጥታ የሚወስድ ድርጅት ነው፡፡ እስከአሁንም አንጎላ፣ ቤኒን፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ሩዋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌን ጨምሮ ከ11 በላይ በሚሆኑ አገሮች ውስጥ ከ19 የሚበልጡ ብሔራዊ ፓርኮችን ጠብቆ አስተዳድሮና አልምቶ ለዓለም ውለታ የዋለ ተቋም ነው፡፡