Connect with us

ህውሓት እስካለ ድረስ በግልባጭ የምንቀበለው እቅድ እንጂ የምንጽፈው አገራዊ እቅድ አይኖረንም!

ህውሓት እስካለ ድረስ በግልባጭ የምንቀበለው እቅድ እንጂ የምንጽፈው አገራዊ እቅድ አይኖረንም!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ህውሓት እስካለ ድረስ በግልባጭ የምንቀበለው እቅድ እንጂ የምንጽፈው አገራዊ እቅድ አይኖረንም!

ህውሓት እስካለ ድረስ በግልባጭ የምንቀበለው እቅድ እንጂ የምንጽፈው አገራዊ እቅድ አይኖረንም!

(አሳዬ ደርቤ ~ድሬ ቲዩብ)

የሥልጣን ሽግግር ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ያሉትን ጊዜያት መለስ ብለን ስናስባቸው ከመንግሥት ይልቅ በህውሓት ፕሮግራም መሠረት እየተመሩ ማለፋቸውን እንረዳለን፡፡ በተለይ ደግሞ ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ጦርነት ከተከሰተበት ጊዜ ወዲህ የነበረውን አንድ ዓመት ስናስበው ሙሉ በሙሉ ከእኛ እቅድ ውጭ ሆኖ ማለፉን እንገነዘባለን፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአንዲት አገር ውስጥ ሁለት መንግሥታት ተፈጥረው ህወሓት ሲተናኮል መንግሥት ደግሞ ሲከላከል መክረሙ ነው፡፡ 

ዓመቱ መጀመሪያ ላይም መንግሥት በአረንጓዴ ብዕር ልምላሜ ተኮር እቅዶችን ሲያቅድ፣ ህወሓት ደግሞ በቀይ እስኪብርቶ የጦርነት እቅድን አቀደ፡፡ ከዚያም  ‹‹አሸናፊነት›› እና አራት ኪሎ መግባት›› የሚሉ ተጨማሪ እቅዶችን ጽፎ ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ፈጸመ፡፡ 

ከጥቃቱ በኋላም መንግሥት የእራሱን እቅድ ወርውሮ የህወሓትን የጦርነት እቅድ ሳይወድ በግዱ በመቀበል ‹‹አሸናፊነት›› እና ‹‹አራት ኪሎ መግባት›› የሚለውን የህወሓት እቅድ አከሸፈ፡፡ ለፕሮጀክት የመደበውን በጀትም ወደ ጦርነት በማዛወር ከመቶ ቢሊዮን ብር ወጪ ጋር መቀሌ ከተማ ከረመ፡፡ አራት ኪሎ የመግባት እቅድ የነበረው ህወሓት ደግሞ ባቀደው ፈንታ ያላቀደውን ክንውን ከፌደራል መንግሥቱ እጅ ተረክቦ ስምንት ወር ሙሉ በቆላ ተንቤን ዋሻዎች ውስጥ ከዝንጀሮ ጋር እየተጋፋ አሳለፈ፡፡ 

በመሆኑም መንግሥትና ህወሓት ከምርጫ እቅድ ውጭ በእራሳቸው አቅደው፤ በእራሳቸው የጊዜ ሰሌዳ የፈጸሙት እቅድ ነበረ ማለት ይቸግራል፡፡ በተለይ ደግሞ ከማጥቃት ይልቅ የተከላካይነት ሚናን የወሰደው የፌደራል መንግሥት በርካታ የህወሓት እቅዶችን እየወሰደ ለህወሓት በማይጥም መልኩ ሲፈጽም ነው የከረመው፡፡ የጦርነት ግብዣውን ተቀብሎ አገር የማፍረስ ሕልሙን በማክሸፍ ነው ዓመቱን የጨረሰው፡፡

ስለሆነም በዚህ ዓመትም በአዲስ መልክ በመደራጀት ላይ የሚገኘው መንግሥት ዓመታዊ እቅዱን ‹‹እንቅፋትን ማስወገድ›› በሚል እቅድ ካልጀመረ ከአምናው የባሰ ችግር እንጂ ከአምና የተሻለ አገር መጠበቅ አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ህውሓት እስካለ ድረስ የሚመዘገብ ስኬት ቀርቶ የሚታሰብ ምኞት ይኖራል ተብሎ አይገምትም፡፡ 

ምክንያቱም አንገቱን ሲያዝ ‹‹ተወረርኩ›› እና ‹‹ተራብኩ›› እያለ የሚወነጅል፣ ስትለቀው ደግሞ ወረራ ፈጽሞ በድል ሙዚቃ የሚከተል… እኩይ ቡድን ተሸክሞ ሕዝብን ማስጠቀም ይቅርና ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻል አይደለም፡፡

በመሆኑም ሰላም ማረጋገጥ ስታስብ ብጥብጥ፣ ልማት ስታቅድ ጦርነትና ውድመት ጭኖብህ ይመጣል፡፡ አጋር የሚሆን ባልንጀራ ለማፍራት ስትንቀሳቀስ አገር የሚያተራምስ ውጫዊ ባላንጋራ ያደራጅብኻል፡፡ የኢትዮጵያን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ጤነኛ ፖለቲካ ማራመድ ስትሻ፣ አገርን ለፍርሰት የሚዳርግ ዘረኛ ፖለቲካን አንግቦ ይታገልኻል፡፡ 

ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው ትርፍ ምርት ማምረት የሚገባቸውን ገበሬዎች ተፈናቃዮች ያደርግብኻል፡፡ ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል ስታስብ፣ ‹‹አንዲት ቃል መቀነስ አትችልም›› እያለ ጦሩን ይሰብቅብኻል፡፡ ‹‹ከዓባይ ግድብ ሃይል ለማመንጨት ስታቅድ ችግር አፍልቆ ግድቡ በሚያመነጨው መብራት ፈንታ የግድቡን ጠላቶች እንዲትጠብቅ ያደርግኻል፡፡ እንዳጠቃላይ የትኛውንም እቅድ ለማከናወን ስትሻ እንቅፋቱን ይዞ እየመጣ እቅድህን መሬት በማስነካት ፈንታ ወረቀት ላይ የሚቀር ያደርግብኻል፡፡ 

ስለዚህ ከመንግሥት በቀዳሚነት የሚጠበቀው እቅድ ህወሓትን እና ቢጤዎቹን ታሪክ በማድረግ የትኛውንም እቅድ ለማከናወን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን አገራችን የህወሓትን የትርምስ እቅድ በግልባጭ መቀበል እንጂ የእራሷን እቅድ አርቅቃ መፈጸም የሚቻላት አይመስለኝም፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top