የትግራይ ህዝብንና አገሬን ይቅርታ እጠይቃለሁ!
(ነብዩ ስሁል ሚካኤል)
ህዝብና አገር ማገልገል ከጀመርኩባቸው አንድ ደርዘን አመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ግለት የታየባቸው የፖለቲካ የትግል አመታት የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መፈጠርና መታነጽ ባበረከተው ቁልፍ አስተዋጽኦና ለዴሞክራሲና ለእኩልነት በከፈለው ከባድ መስዋእት ልክ አገራዊ አንድነቱ፣ ብሔራዊ ነጻነቱ፣ ራስን-በራስ የማስተዳደር መብቱ፣ ልማታዊ ተጠቃሚነቱና የዴሞክራሲ ጥማቱ ለማርካት እኔን ከሚመስሉ ጥቂት ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር አብሬ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡
በሂደቱ መደበኛ የመንግስት ሃላፊነት በመሸከም ህዝብና አገር የማገልገልና አገር የማነጽ ማእከል በሆነው የዩኒቨርሲቲ አስተማሪነት ሞያ 10 አመት ያገለገልኩ ሲሆን ከዚህ ጎንለጎን የተለያዩ መጽሃፍቶች በመድረስ ታሪኩና ማንነቱ የሚያውቅ፣ ጠያቂና ብሔራዊ ክብሩ የተጎናጸፈ ትውልድ እንዲፈጠር እንዲሁም ፍትህ፣ ዴሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት አገር እውን እንድትሆን የበኩሌን አስተዋጽኦ እያበረከትኩ ቆይቻለሁ፡፡
በለውጡ አመታትም የለውጥ እድሎች ለማቀብና የህዝብ ደህንትና የአገር አንድነት ለመጠበቅ የተለያዩ የማንቃትና የልማት ስራዎች ላይ ስሳተፍ ቆይቻለሁ፡፡ በስተመጨረሻም ጽንፈኛው የህወሓት ቡዱን የትግራይ ህዝብ በእጅጉ የሚጎዳና አገር የሚያፈርስ ተግባር ላይ በሰፊው እየተሰማራ በመሄዱ ወደ መደበኛ የፖለቲካ ትግል በመቀላቀል የተደራጀ ትግል እያካሄድኩ እገኛለሁ፡፡
ወደ ብልጽግና ስቀላቀል ጽንፈኛው የህወሓት ቡዱን እየፈጠረው የነበረው የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች የመነጠል፣ ከጉያው ውስጥ የመሸ-ሸግና የጦርነት አደጋ ውስጥ እንዲማቅቅ የማድረግ እኩይ አላማው በመቀልበስ አስከፊ የእርስበርስ ጦርነት ጨምሮ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አደጋዎች መከላከልና ማስቀረት፣ የለውጡ ግለት መጠበቅ፣ በህዝቦች መካከል መተማመንን ማጠናከር፣ አገራዊ አንድነት ማጽናትና ብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ምልአት እንዲላበስ መተባበር ያለመ ልዩ ተልእኮ/specialty mission እንደነበር ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡
ይህ ሁሉ ታቅዶና ጥረት ተደርጎ ግን ለማስቀረት የወጠንኩትና ለመገንባት ያለምኩት ህዝባዊና አገራዊ አጀንዳ ማሳካት ሳልችል ቀርቻለሁ፤ በዚህም እጅግ በጣም አዝኛለሁ!!
በደማቅ ታሪኩና በከባድ መስዋእቱ ልክ የተሻለ ኑሮና ስርዓት ይገባዋል ብየ የተጨነቅኩለትና የራሴንና የቤተሰቤ ህይወት ጭምር አደጋ ላይ ጥየ በቅድምያ የታገልኩለት የትግራይ ህዝብም ከነበረበት በብዙ እጥፍ በባሰ ደረጃ በሁለንተናዊ ችግርና በጦርነት አዙሪት ውስጥ እየዳከረ ይገኛል፡፡ አገራችንም ብትሆን ከልማት አጀንዳዋ ጎድላና የህልዉናና የአንድነት አደጋ ተጋርጦባት ትገኛለች፤ ይህም በራሱ እጅግ አሳዛኝ ክስተት መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡
በመሆኑ እንደ አንድ የትግራይ ህዝብ ልጅና እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከዚህ የተሻለ ጥረትና ትግል ማካሄድ እንዲሁም ከፍ ያለ መስዋእት መክፈል እንደነበረብኝ በማሰብ የጥፋተኝነት ስሜት እየተሰማኝ ይገኛል፡፡
ለግዜው አሁን ካለሁበት የትግል ምእራፍ የተሻለ ብየ የደረስኩበት የጥረትና የትግል አይነትና የመካሻ መላ ባለመኖሩም ቢያንስ ቅድምያ ህዝቤንና አገሬን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብኝ ወስኛለሁ፤ ይቅርታየም እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡-
ህዝቤንና አገሬን ከጦርነት አዙሪትና ከአሰቃቂ ጥፋት መታደግ ባለመቻሌ፤ የልማትና የዴሞክራሲ እድሎች እንዳይስተጓጎሉ የተሻለ ጥረትና ትግል ባለማካሄዴ እንዲሁም ከፍ ያለ መስዋእት ባለመክፈሌ በግሌ እንደ አንድ የትግራይ ህዝብ ልጅና እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከልብ ከመነጨ ስሜት ህዝቤንና አገሬን ይቅርታ እጠይቃለሁ!!