የተኩስ አቁም ጣጣ
(አሳዬ ደርቤ – ድሬ ቲዩብ)
ወርሐ ነሃሴን ያሳለፍኩት ከኮሮና ቫይረስ ጋር ግብግብ በመግጠም ሲሆን ሕመሙ ሲጀማምረኝ አካባቢ ጉንፋን መስሎኝ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በሽታውን በመድሃኒትም ሆነ በነጭ ሽንኩርት በመዋጋት ፈንታ የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጌ ነበር፡፡
እየቆየ ሲመጣ ግን ህወሓት የሚተኩሳቸው ሮኬቶች የንጹሐንን ቤት እየሳቱ የእኔን ጭንቅላት የሚደበድቡ እስኪመስለኝ ድረስ ከባድ እራስ ምታት ይወቅረኝ ጀመር፡፡ ከጭንቅላቴም አልፎ መላ ሰውነቴን እንደ ሰሜን ወሎ ዞን በመውረር ያወድመኝ ያዘ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ምግብ ከማጣጥምበት ምላሴ በተጨማሪ እሜቴን የምጎበኝበት ሕዋሴ ላይ ጥቃት በመፈጸም ሁሉንም ነገር ጣዕም አልባ አድርጎብኝ አረፈ፡፡
ቫይረሱ በምላሴ ላይ ጉዳት ማድረሱን ከማወቄ በፊትም፤ ውዷ ባለቤቴ ሾርባ አምጥታ ስትሰጠኝ ‹‹ጁንታ ይመስል እንዴት ሊጥ ትሰጪኛለሽ?›› እያልኩ የረሐብ አድማ ስመታ ነበር፡፡ ሕመሜ እየተባባሰ ሲመጣ ግን የኮሮና ምርመራ ማድረግ እንደሚኖርብኝ አምኜ ወደ ጤና ጣቢያ ሳመራ ካርድ ለማውጣት የተደረደሩ እልፍ አእላፍ ታማሚዎች ተደርድረው አገኘሁ፡፡
ከእነዚህም ታካሚዎች ፊት ተገትሬ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቅላጼ ‹‹የተከበራችሁ የጉንፋን ተጠቂዎች፣ የተከበራችሁ የታይፎይድና ታይፈስ ታማሚዎች፣ የተከበራችሁ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ ተጠቃሚዎች፣ እንዲሁም የካርድ ክፍል ሠራተኞች…. ከፊታችሁ ቁሜ የምታዩኝ ግለሰብ የኮቪድ 19 ተጠቂ ስለሆንኩ ቀድሜያችሁ ካርድ አወጣ ዘንድ እንድትፈቅዱልኝ እማጸናለሁ›› የሚል ተማጽኖዬን ሳቀርብላቸው ‹‹እኛም በትኩሳትና በሳል እየተቃጠልን እዚህ የተቀመጥነው የኮሮና ምርመራ ለማድረግ ስለሆነ አርፈህ ወረፋህን ጠብቅ›› በማለት ተንጫጩብኝ፡፡
እናም ርቀቴን ጠብቄ ከኋላቸው ከተቀመጥኩ በኋላ ባነጠስኩ ቁጥር ‹‹ይማርህ›› የሚሉኝን ሰዎች፣ ባስነጠሱ ቁጥር ‹‹ይማራችሁ›› እያልኩ ውለታቸውን እመልስ ጀመር፡፡
ከብዙ ጥበቃ በኋላም፣ ወረፋዬ ደርሶ ካርድ ካወጣሁ በኋላ ወደ ምርመራ ክፍል ሳመራ ‹‹ከኮቪድ ይልቅ በማስክ ታፍኜ ልሙት›› የሚል ውሳኔ ያስተላለፈች አንዲት ዶክተር ሦስት ማስክ ደርባ ጠበቀችኝ፡፡ በአምስት ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ወንበር ላይ ካስቀመጠችኝ በኋላም ‹‹እንዴት ነው የሚያደርግህ?›› ስትለኝ ‹‹እንደ ታዲዮስ ታንቶ አፍኖ ሊወስደኝ ይዳዳዋል›› አልኳት፡፡
‹‹ሌላስ?››
‹‹የምበላው ምግብ ምንም አይነት ጣዕም የለውም››
‹‹የምትበላው ምግብ ዘይትና ቅቤ አለው?››
‹‹የለውም››
‹‹ታዲያ ዘይትና ቅቤ የሌለው ምግብ ምን ጣዕም አለውና ነው የምታጣጥመው?›› ብላ የሳቅ ድምጽ ካሰማች በኋላም ‹‹ሌላስ?›› በማለት ጠየቀች፡፡
‹‹ከሦስት ብርድ ልብስ ስር የተኛች ሚስቴ ‘ወበቅ ገደለኝ’ ስትለኝ በብርድ ከመሞቴ በፊት ሌላ ብርድ ልብስ ፈልገሽ ደርቢልኝ እያልኩ እለምናታለሁ››
ይሄንንም መልሴን ስትሰማ ‹‹ባለቤትህም መመርመር አለባት›› ከሚል ትዕዛዝ ጋር ወደ ላብራቶሪ ክፍል ላከችኝ፡፡ ከሰላሳ ደቂቃ ጥበቃ በኋላም የላብራቶሪ ውጤቴ ደርሶ ወደ ምርመራ ክፍል ተመልሼ ስገባ ‹‹ቫይረሱ ተገኝቶብኻል›› አለችኝ፡፡
‹‹ኮቪድ 19 ነው ወይስ ዴልታ?›› ብዬ ስጠይቃትም ‹‹ልዩነት የላቸውም እኮ! ትሕነግና ኦነግ እንደማለት ነው›› የሚል መልስ ከሰጠችኝ በኋላ ‹‹እነዚህን መድሃኒቶች ገዝተህ ውሰድ›› ብላ የሆነ ወረቀት አቀበለችኝ፡፡
እናም ድሮን ይመስል ቱርክ አገር ከተመረተ ክኒን ጋር ሌሎች ተጨማሪ መድሃኒቶችን ገዝቼ ወደ ቤቴ ከተመለስኩ በኋላ ‹‹የያዘኝ ሕመም ኮሮና ሆነ እኮ›› በማለት ለእሜቴ ስነግራት፣ ‹‹እስከ እለተ ሞትህ ድረስ አብሬህ ለመኖር ቃል እገባለሁ›› ብላ የተጋባን ቀን ቃል የገባችልኝ ውዷ ባለቤቴ ‹‹እስክትድን ድረስ ደጀን ፍለጋ ወደ እናቴ ጋር ልሄድ ስለሆነ ነጭ ሽንኩርትና ዝንጅብል እያፈላህ ጠጣበት›› ብላኝ ስልታዊ ማፈግፈግ በማድረግ ባሏን ጥላ ስትወጣ፣ ቫይረሱን አንጠልጥላ ወደ እናቷ ዘንድ አመራች፡፡
የታዘዘልኝን የቱርክ ክኒን እና የራሺያ ቪታሚን ባግባቡ በመጠቀም እንደ ‘ንፋስ መውጫ’ ከተማ የአየር ማስገቢያና መስወጫ ጉሮሮዬን የዘጋኝን ተሕዋስ በአፋርና በወልቃይት አካባቢ ወረራ ሊፈጽም ሲል መሽኮ እንደቀረው የግንቦት ሃያ ቫይረስ መፈናፈኛ አሳጥቼ እደመስሰው ጀመር፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ግን፣ ከኮሮና ሙሉ በሙሉ ነጻ እስክሆን ድረስ ትግሌን በማጠናከር ፈንታ ጭንቅላቴን የሚደበድበኝ፣ ደረቴን የሚያፍነኝ እና ጀርባዬን የሚደበድበኝ ሕመም ጋብ ባለልኝ ቅጽበት የምወስደውን መድሃኒት እንደ ሰሞኑን ጦርነት አቋርጬው አረፍኩ፡፡
ይሄንንም መልካም አጋጣሚ ያገኘው ቫይረስ አዲስ የኮሮና ሠራዊት ሲመለምልና ሲያሠለጥን ውሎ ካደረ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ያስለቀቅኩትን ሳንባዬን እንደ ሰቆጣና ላሊበላ ድጋሜ ተቆጣጥሮ ወደ ኤካ ሆስፒታል አፈናቅሎኝ አረፈ፡፡
ሞራል ኦፍ ዘ ስቶሪ፡-
‘አገገምኩ’ ብሎ በሃኪም የታዘዘን መድሃኒት ሳይጨርሱ መተው፤ ‘አዳከምኩ’ ያሉትን አሸባሪ ሳይደመስሱ እንደመተው ዋጋ ያስከፍላል!!