“የገዳዮች ወንድማማችነት”
ሰዎች በተለያየ ርዕሰ ነገር ወይም አላማ ይወዳጃሉ:: የወዳጅነቱ አይነት የትየለሌ በመሆኑ ቆጥሬ አልዘልቀውም:: በጥቅሉ ግን ማህበራዊ ፋይዳው መልካም የሆነ ህብረት ሲሆን ያ ጓድ የለውጥ ሰራዊት/ሐዋርያት “pioners of change” የሚል ታሪካዊ ቅጽል ያገኛል::
እንደሰንደቅ የሚውለበለብ ድል ባያቀዳጅም ዘወትራዊ ሕይወትን በድል የሚያሻግር መደበኛ ወንድማማችነትም ክብር ይገባዋል:: አላማው በጉልህ የማይታየው የፈንጠዝያ ውድጅትም ቢሆን የሚለካው አግኝቶ “ቢሰፍሩት” ዋጋው ከፍ ሳይል አይቀርም:: ዝንጋኤ እስካላስከተለ ድረስ አብሮነት ደግ ነው::
እኔን ግርም የሚለኝ የነፍሰ ገዳዮች “ወንድማማችነት” (Fraternity of Assasins) ነው:: ይህ ውድጅት በተለያየ ምክንያት ይመሰረታል:: አንዳንዱ እጅግ እውቀታዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ እና ፍልስፍናዊ መሠረት ያለው ይመስላል:: ይሁንና የዚህን ህብረት መሠረት ቢያናጉት ከሆድ ወይም ከግላዊ ጥቅም የዘለለ ጉዳይ አታገኙበትም::
ይህ ቡድን ለስሙ መጠርያ ተጨናቂ፣ ለቀለሙ ማማር ተብረቅራቂ፣ የሆዱን ጩኸት “በሕዝብ አለኝታነት” ደባቂ ነው:: ይህን መልከ ቀናነት ለመቀዳጀት የታቀደ “እውነት”የሚመስል ቅደም ተከተላዊና ፈር ያለው ስልት ያዘወትራል:: ይህ ውድጅት በነገረ ፆታ፣ በነገረ ወሲብ፣ በሐይማኖት፣ በብሔር፣ በፖለቲካዊ አቋም፣ በሙያ፣ በመሳሰለው ታላላቅ ስብዓዊ ጉዳይ ሁሉ ልታይ ልታይ ይላል:: ሀገር ያውካል:: ይህ አይነቱ ውድጅት “ይሉኝታ” ሲያልፍም አይነካው:: እንደደጎች ሁሉ የዚህን ቡድን ደቀ መዛሙርት በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ::
- የጋራ የሆነችውን ሀገራችንን ጠፍጥፈው ዛሬ የሰሯት ይመስል: እኔ ብቻ አውቅልሻለሁ ይሏታል:: መሽቶ እስኪነጋ “አያምኗትም” ከቆሙበት ስፍራ በቀር ተጨማሪ ወይም የትየለሌ ግላዊም ቡድናዊም አንጻር/ምልከታ/አ ቋ ም ወዘተ. እንዳለ አይረዱም::
ቢረዱም ሌላው ሁሉ የማይረባና የተዋረደ ነው:: በጉልህ የሚታያቸው “ከሀገር የሚሰፋው ሆዳቸው” ነው:: ሀገር አፍ አውጥተሽ ተናገሪ ቢሏት ስለነዚህ ሰዎች ቃላት የሚያጥሯት ይመስለኛል::
በሌላ ወገን እኒህ ሰዎች በሰይፉ መታፈርያ ፍሬው አንዲት የግጥም አንጓ እንዲህ ይታዩኛል:-
“ይህ ዓለም ይህ ዓለም” ይላሉ:
ይህን ዓለም ሞልተው እንደኖሩ ሁሉ”
ሀገሩ የማናየው፣ የማናውቀው፣ የማንሰፍረው፣ የማንለካው ፣ የማንገምተው ጭምር ብዙ ጉዳይ አለው:: ዓለም ሰፊ ነው:: ይህን ሲያውቅ ሰው ትህትና ትዘልቀው ይመስለኛል::
- ጩኸት መቀማት አይነተኛ ጠባያቸው/ፍሬያቸው ነው:: በዚህ ጠባያቸው “ራሳቸው ገርፈው ራሳቸው አልቃሽ” በምሆን ከፊት ተሰላፊ ናቸው::
- ስለመቃወም መቃወም የሚያስገኘውን ትርፍ ያሰላሉ:: ጀብድ እንጂ ጀግንነት አያውቃችውም::
- ተቆርቋሪ ከሚመስለው የፊት ገፃቸው ባሻገር ድብቁ ህልማቸው ሆድ መሙላት ወይም ጥቅም ማሳደድ በመሆኑ ያቀዱት ሲከሽፍ ካሸናፊው ጎን ለመሰለፍ እፍረት አታውቃቸውም:: የጠበቁት ጥቅም ካልተገኝ ጠላት ለመሆን እንዲሁ አይሰንፉም:: ይቸኩላሉ::
- በነሱ ዘንድ ወዳጅ ማለት ከጠባብ ሆዳቸው የመንጨ ደካማ ህልማቸውን የሚያገለግል እና ለሙት ህልማቸው ሕይወት መዝራት “ለምን? ” ሳይል የሚሰለፍ agent/object ነው::
እኒህ ሰዎች ውድጅት የሚያስፈልጋቸው የሰው ልጅ ለብቻው የማይገፋቸው በርካታ ሕይዎታዊ ጉዳዮች ስላሉት ነው:: ወዳጅነት ለብቻ የማይ’ገፋውን ለመግፋት የሚመሰርቱት ስልታዊ ኮንትራት ወይም strategic alliances ነው::
እንደተራራ የከበዳቸውን ሸክም ካራገፉ በኃላ ግን “ሆዳቸው አምላካቸው” ሆኖ ያርፈዋል::
በተለምዶ “ባንዳነት” ለፍርፋሪ ተገዝቶ ከውጭ ጠላት ጋር በግልፅ በመወገን ሀገርን መጉዳት/መክዳት ብቻ የሚመስለው ብዙ የዋህ አለ:: ነገር ግን ባንዳነት መጠነ ዙሪያው እጅግ ሰፊ ነው:: የሀገርን ህልም ለግል ሆድ መሸቀጫ ማድረግ መጠኑም ልኩም ካቅም በላይ ነው::
የገዳይ ወንድማማቾቹን መስፋፋት በማህበራዊ ድረ ገፆች፣ በቴሌቪዢን መስኮቶች፣ በሬዲዮና በመሰለው ሁሉ አዋጅ ነጋሪ ሆነው ማየት አዲስ አልሆን አለ:: ተለመደ:: የምናዋጣው ማንኛዋም “ቅንጣት” ነገ ለሚፈጠረው ሀገራዊ ግዙፍ ምስል አስተዋፅኦ ስላለው እየተስተዋለ ለማለት የተፃፈ:: ምክሩ መካሪውን እንዲጨምር ይሁን አሜን!
#አገኘሁ_አዳነ_ድልነሣሁ
***
ማስታወሻ:- አቶ አገኘሁ በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ፤ የአለ ፈለገ ሰላም የሥነጥበብ ት/ቤት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።