Connect with us

እናት አገር ኢትዮጵያ በነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተ-መንግስት የጻፈቺው

እናት አገር ኢትዮጵያ በነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተ-መንግስት የጻፈቺው
Photo: AP

ነፃ ሃሳብ

እናት አገር ኢትዮጵያ በነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተ-መንግስት የጻፈቺው

እናት አገር ኢትዮጵያ በነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተ-መንግስት የጻፈቺው

(አሳዬ ደርቤ ~ ድሬ ቲዩብ)

ውድ አሜሪካ፡- ‹‹የምታከብሪው ዘመን መለወጫ እንደ ባለፈው ምርጫ መስፈርቱን የማያሟላ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም›› ትይኛለሽ ብዬ ሳስብ፣ የዘመን ለውጡ እንዲካሄድ ፈቅደሽ በጆባይደን አማካኝነት ‹‹እንኳን አደረሰሽ›› ስላልሽኝ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ከሁሉ አስቀድሜ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ 

የቀድሞ ልጄና የአሁኗ ጎረቤቴ ኤርትራም ምኞትሽን ስትሰማ ከምስጋናዋ በማስከተል ‹‹ለቀጣይ ዓመትስ በሰላም ታደርሺናለሽ ወይ?›› ማለቷን ልነግርሽ እሻለሁ፡፡ ክክክክ

የእንቁጣጣሽ መልዕክትሽን በደስታ በተቀበልኩ ማግሥት ደግሞ ‹‹I am deeply concerned›› የሚል ጣጣሽንና ማዕቀብሽን ማስከተልሽ ምቾት እንደነሳኝ ልደብቅሽ አልሻም፡፡ ‹‹የራሴ ሉኣላዊነት ያለኝ አገር ነኝ›› ብዬ ሳስብ እኔ ሳላውቅ በዲቪ ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ አሻግረሽ 51ኛ ስቴት ያደረግሽኝ ይመስል እንደ ክፉ እንጀራ እናት በሁሉም ነገር ልቆጣሽና ልቅጣሽ ማለትሽ የሚከነክን ጉዳይ ሆኖብኛል፡፡

ሌላው ደግሞ USA:- በራስሽ የማታደርጊውን ነገር እኔ እንዳደርገው ወስነሽ ‹‹ድርድርና ውይይት›› የሚል ምናባዊ አቋምሽን ማጠናከርሽ አስገራሚ ሆኖብኛል፡፡ ቆይ እኔ እምለው አሜሪካ፤ ከአሸባሪዎች ጋር ሰላም ለመፍጠር ብቸኛ መፍትሔው መደራደርና ሰላማዊ ውይይት ከሆነ አፍጋኒስታን ድረስ ተጉዘሽ ከአሸባሪዎች ጋር ግብግብ መግጠም ስለ ምን አሰኘሽ?

ከአልቃይዳም ሆነ ከአይ ኤስ ኤስ ጋር በመደራደር ፈንታ ወታደሮችሽን ማሰማራት ስለ ምን ፈለግሽ? ነው ወይስ በርካታ ከተሞችን ያወደሙትና ንጹሐንን የጨፈጨፉት የኔዎቹ አሸባሪዎች ባንቺ ዘንድ በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ሐይማኖታቸውን ቀይረው በሕዳሴ ግድብ ፈንታ ያንቺን የሁቨር ግድብ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ምትክ ያንቺን ዜጎች ዒላማቸው ማድረግ አለባቸው? እያሰብን እንጂ…

ውድ አሜሪካ፡- አሁን አሁን ሃያልነትሽንና ጉልበትሽን ልታሳይኝ በሞከርሽ ቁጥር ደካማነትሽንና የአስተሳሰብ ዝቅታሽን በግልጽ እያሳየሽኝ ነው፡፡ በፍርዴ ገምድልነት እሳቤ ችግሬን ለማወቅ ሳትሞክሪ መፍትሔ ልስጥ ማለትሽ፣ በአንድ እጅሽ ልማት በሌለኛው እጅሽ ጥፋት ይዘሽ መከሰትሽ ‹‹ይህቺ ሴትዮ ከአባት አገር ራሽያ ጋር በጀመርኩት የፍቅር ግንኙነት ተበሳጭታብኝ ይሆን?›› እያስባለኝ ነው፡፡ 

የእነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርትም ከእነ አታክልቲ ሪፖርት ላይ የሚቀዳ መሆኑ ተቋማቱ ለሰብዓዊ መብት የሚታገሉ ሳይሆኑ የደበራቸውን መንግሥት የሚወነጅሉ መሆናቸውን ግልጽ አድርጎልኛል፡፡

ሲቀጥል ደግሞ ‹‹ለተራቡ ዜጎችሽ የላኩትን እርዳታ እያከፋፈልሽ አይደለም›› እያልሽ ደንፉ ስትጭሪብኝ ትከርሚና ስንዴ ሊያደርሱ የሄዱ ተሸከርካሪዎች በዚያው ቀልጠው አሸባሪና ወራሪ ጦር ሲያመላልሱ ግን ‹‹ጋራጅ ገብተው ይሆናል›› ብለሽ እንዳላየሽ ትሆኛለሽ፡፡ ‹‹ሕጻናት ልጆቼ በአዛውንቶች እየታፈሱ ወደ ጦር ሜዳ እየዘመቱ ነው›› ብዬ ትዊት ሳደርግልሽ ላይክ ገጭተሽ ታልፊውና ‹‹ሞቱ›› ሲትባይ ግን ‹‹I express my heartfelt condolences…›› ከሚል ፖስት ባለፈ ነጠላሽን መዘቅዘቅና ባንድራሽን ዝቅ ማድረግ ያምርሻል፡፡  

አሸባሪው ሃይል ወራራ የፈጸመባቸውንና ጦርነት የሚደረግባቸውን የአማራና የአፋር ክልሎች አልፈሽ ትሄጂና ውጊያ ከሌለበት ስፍራ የሚካሄደው ጦርነት እንዳሳሰበሽ ትገልጫለሽ፡፡ ‹‹የኤርትራ ጦር ከትግራይ ባስቸኳይ ይውጣ›› የሚል ትዕዛዝ ስታስተላልፊ ጎንደር የገባውን የሱዳን ጦር በፈገግታ ታልፊዋለሽ፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ሚዛናዊነት የጎደለው መድሎኛ እይታይሽ ከሆሊውድ ፊልሞችና ከእነ ሲድኒ ሸልደን ድርሰቶች የሸመደድኩትን ማንነትሽን ቢያደበዝዝብኝ ምኑ ይገርማል?

ውድ አሜሪካ፡- ፈርጣማ ክንድ ያለሽ ታላቅ አገር መሆንሽን አውቃለሁ፡፡ ግን ያ ታላቅነትሽ የሌሎችን አገራት ሉኣላዊነት ሊያስረሳሽ አይገባም፡፡ እና ደግሞ የቀድሞ ፕሬዝዳንትሽ ባይመችሽም የዜጎችሽን ድምጽ አክብረሽ ከነጩ ቤተ-መንግሥት አራት ዓመት እንዲቆይ እንደፈቀሽው ሁሉ የኔም ዜጎች የመረጡትንም ሆነ ያስወገዱትን መንግሥት አምነሽ መቀበል ግድ ይለሻል፡፡ ይሄን የምልሽ ታዲያ የተመረጠው መንግሥት በምቾት አንደላቅቆ ስለያዘኝ እንዳይመስልሽ፡፡ 

ሉኣላዊ አገር እንደመሆኔ መጠን አንቺ ከምትመርጪልኝ መልካም ሥርዓት ይልቅ ዜጎቼ የመረጡትን ማንኛውም አይነት መንግሥት መሸከም ስለምመርጥ እንጂ፡፡ ስለዚህም መስከረም መጀመሪያ ላይ የለወጥኩትን ዘመን እንደተቀበልሽው ሁሉ በዚሁ ወር መጨረሻ ላይም የሚደራጀውን መንግሥት እየመረረሽም ቢሆን አምነሽ መቀበል ይኖርብሻል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን በሽታን እና ጤንነትን አስማምቶ የሚያኖር ሰውነት፣ አገር አፍራሽ አሸባሪን እና ሰላማዊ አየርን አቻችሎ የሚያኖር መሬት የለምና… ለሰባት ሚሊዮን ዜጎቼ ለምታቀርቢው ስንዴና ዱቄት ስል እኔን ለማፍረስና መቶ ሚሊዮን ዜጎቼን የሚላስ የሚቀመስ ለማሳጣት ከሚጥር አሸባሪ ጋር ልደራደር ባለመቻሌ አዝናለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ካንቺም ጋር ሆነ ከጆ ባይደን ጋር ለመስማማት ከደብረ ጽዮን ጋር መስማማት አይጠበቅብኝና ሉኣላዊነቴን በማይዳፈሩ ጉዳዮች ላይ ትእዛዝሽንም ሆነ እርዳታሽን ለመቀበል ዝግጁ መሆኔን በመግለጽ ደብዳቤዬን እቋጫለሁ፡፡

ኢትዮጵያ!

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top