Connect with us

ቦኖሯ-የሲዳማ ውብ ተፈጥሮ ባለ ዜማ ምስክር

ቦኖሯ-የሲዳማ ውብ ተፈጥሮ ባለ ዜማ ምስክር
ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

ቦኖሯ-የሲዳማ ውብ ተፈጥሮ ባለ ዜማ ምስክር

ቦኖሯ-የሲዳማ ውብ ተፈጥሮ ባለ ዜማ ምስክር

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ሲዳማ ክልል ነው፡፡ ስለ ሲዳማ ውብ የተፈጥሮ ጸጋዎች ይነግረናል፡፡ ውብ ፏፏቴዎችን ያስተዋውቀናል፡፡ ቦኖሯ ደርሷል፡፡ ዜማ አለው ያውም የሲዳማን ውብ ተፈጥሮ የሚያስረዳ ሲል ውቡን መዳረሻ እንዲህ ያስቃኘናል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

የሲዳማ ደጋ ምድር ምንጣፍ ነው፡፡ አረንጓዴና በጀርባው የተኛ፤ ደግሞ ተራሮች የሚቀባበሉት፣ በተራሮች ጉያ ውብ ባህላዊ ቤቶች እዚህም እዚያም እንደ አስማት ዐይንን አስረው የሚያስቀሩበት፡፡ ወደ ውቡ ምድር ጉዞ ላይ ነኝ፡፡

ሀዋሳ ቅዳሜ የደረሰ የሚመለከተው ልዩ ነገር ነው፡፡ አንድም ቅዳሜን፤ አንድም ቅዳሜ መሳይ ከተማን፡፡ ሀዋሳ የሀገር ውስጥ ጉብኝት ተመራጯ የመዝናኛ ቱሪዝም መዳረሻ ናት፡፡ አዲስ አበቤዎች በርረው ይመጣሉ፤ አዳማዎች ትናፍቃቸዋለች፡፡ ደግሞ የሻሼዎች የእረፍት ቀን መናገሻ ናት፡፡

አረንጓዴ ቀሚስ የለበሰች መዲና፡፡ ንጹህና ውብ፡፡ ሁሌም እንግዳ ይመጣል ብላ ቤቷን አሰናድታ ከምትጠብቅ ብርቱ የቤት እመቤት ጋር ትመሳሰልብኛለች፡፡ እውነትም ደግሞ ሁሌም እንግዳ ይመጣባታል፡፡ ይኸው እኔም እንግዳ ሆኜ መጣሁ፡፡ እጅግ ለብዙኛ ጊዜ፤ ከቁጥር በላይ ለሆነ፤

ሀዋሳ አድሬ በጠዋት ጉዞ ጀምሬያለሁ፡፡ ወደ አፖስቶ ከዚያ ወደ አለታ ወንዶ ከዚያ ወደ ውቡ መስህብ፡፡ መንገዱ አይጠገብም፤ የሚያጠግበው ፍራፍሬ ደግሞ በየትንንሹ የገጠር መንደር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ዳዬ ዳዬ ቡሹ የሚለው የብጽአት ስዩም ዜማ ወደ ልቤ ይመጣል፡፡ ድምጻዊቷ ጭንቅ ሲላት፤ ምናለ እንደ እኔ ሌላው ቢያይሽ ደግሞ ትላለች፡፡ እውነትም፤ እንደ እኔ እዩት፡፡

አለታ ወንዶ ደማቅ ከተማ ናት፡፡ ትናንትናዋን ዛሬ ተረክቦታል፡፡ ቀደምት የምርት ምድር በመሆን ስሟ ታላቅ ስፍራ ይዟል፡፡ የወርቅ ሀገሩ ወርቅ መንገድ ናት፡፡ አንድ ቀን እነግራችኋለሁ፡፡ አሁን እንቀጥል ወደ ፊት፡፡

በንሳ ዳዬ ከተማ ነኝ፡፡ ከተማው ውስጥ እንዲህ ያለ ፏፏቴ አትገምቱም፡፡ ያለ አንዳች ድካም ግን እንዲህ ያለ ውብ ቦታ ደርሰናል፡፡

እዚህ ድንቅ ተፈጥሮ ተደብቋል፡፡ ገና ወደ ቅጥሩ ስጠጋ ዜማው ተቀበለኝ፡፡ ዜማው ስለ ሲዳማ ውብ ተፈጥሮነቱ ራሱ ለራሱ ምስክርነት የሚሰጥበት ነው፡፡ ቀጠለ፤ በንፋስ ሽውታ ይዳስሰኝ ጀመር፡፡ አየሁት፡፡ ልቤ ወከክ አለ፡፡ ቦኖሯ ፏፏቴ ሲዳማ፡፡

የሚገርም መጠን አለው፡፡ ግዙፍ ጢስ፡፡ ደግሞ የተኛበት ሸለቆ ሌላ ውብ መልክ ፈጥሯል፡፡ እዚህ ተፈጥሮ እንዲህ ለዝንት ዓለም ትዕይንቷን ለራሷ እያጣጣመች ኖራለች፡፡ ይሄንን የሚያህል ፏፏቴ ከኢትዮጵያ ውሃ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተሸሽጎ ኖሯል፡፡ አሁንም ለምን ማለት አያዋጣም፤ ይልቁንስ መጣሁ ማለት ዋጋ አለሁ፡፡ መጥቼ እዚህ ደርሻለሁ፡፡

ዋሻው ግዙፍ ነው፡፡ እንደ መጋረጃ በቦኖሯ ፏፏቴ ውሃ ግማሽ አካሉን ዘግቶታል፡፡ እንደ ሸማ መጋረጃ ውብ ቅርጽ ባለው ተፈጥሮ፤

በጣም ደንቆኛል፡፡ ምናልባት ሃምሳ ሜትር ከፍታ ባለው ርቀት የሚወረወር ውሃ፤ በጣም ንጹህ፤ ደግሞ ብዙ፡፡ በክረምት ጠላ መልክ የሌለው፤ አፈር ከሚታደግ ደጋ መንደር የሚመጣ፡፡

ገና እንሄዳለን፡፡ ወደ ሎጊታ፣ ጋላናን እናያለን፡፡ ሲዳማ ክልል የ2014 ዓ.ም. የዓለም ቱሪዝም ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበርበት የኩነት ስፍራ ነው፡፡ ሲዳማ ደርሳችሁ በክረምት ቦኖራን ሳትመለከቱ የምትመለሱ ዓለም አምልጧችኋል፡፡ ደግሜ እላለሁ ዓለም አምልጧችኋል፡፡

ኑ ወደ ሎጊታ እንውረድ፡፡

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top