#ሰበዝ
(ውድነህ ክፍሌ)
የመጀመሪያ የቲቪ የዝግጅት ስራዋ “አቋራጭ” ይሰኛል፡፡ አሪፍ አድርጋ አዘጋጅታዋለች፡፡ አቋራጭን በዝግጅት “ሀ” ብላ የጀመረችው ጀግኒት አቋራጭ መንገድ አትወድም፡፡ ሁለነገሯ ፊት ለፊት ነው፡፡ እውነትን ተጋፍጦ ማሸነፍ የህይወቷ መርህ ነው፡፡ እንደአዲስ ብትፈጠር እንኳን የመአዚ አቋም አንድ ነው፡፡ አቋሟን ከ”ደርሶ መልስ” የቲቪ ተከታታይ ድራማዋ ጋ ታያይዘዋለች፡፡
“በዚህ ምድር በድጋሚ የመፈጠር ዕድል ባገኝ “ደርሶ መልስ” ድራማ ያነሳቸውን ርእሰ ጉዳዮች፤-ፍትሐዊነት፤ እና እኩልነት እንዲሰፍን፤ሙስና እንዲጠፋ፤ሁሉም ሰው ከኢኮኖሚው ተሳታፊ የሆነበት ማህበረሰብ እንዲፈጠር መትጋትና ሲፈጠር ማየት እፈልጋለሁ፡፡…ለምን ሙስና ይኖራል? ለምን እኩል አልሆንንም? ለምን ሰው በላቡ ብቻ አልኖረም? ለምን ሰው የሰው ላብ ይነጥቃል?…” ይህ የእውነት ጥያቄዋ አብሯት የኖረ ጥያቄው መልስ እስኪያገኝ ድረስ ውስጧ የሚኖር ነው፡፡
ስለመአዚ የቅርብ ወዳጆቿ እንዲህ ይላሉ፡፡ “መአዚ ጽኑና ቀጥተኛ ነች!” ይሄንን እኔም መስካሪ ነኝ፡፡ ለዚህም ነው እኮ በሮች ሲዘጉባት ሌላ በር የምታንኳኳው፡፡ ለዚህም እኮ ነው “ዝነኞቹ” የተሰኘውን ቴአትር ፈተና ቢበዛባትም በራሷ ጥረት ለመድረክ ያበቃችው፡፡ ለዚህም እኮ ነው አንዳንድ የቴአትር ቤት አሰራር አልመች ስላላት “ከሰላምታ ጋር” ቴአትርን በራሷ አቅጣጫ በጣይቱ ሆቴል ለተመልካች ያቀረበችው፡፡ በነገራችን ላይ “ከሰላምታ ጋር” ቴአትር ትርጉም ነው፡፡ “ዴስፐሬት ቱ ፋይት” ከተሰኘው የእንግሊዝኛ ቴአትር የተተረጎመ ነው፡፡
ይህ የእንግሊዝኛ ተውኔት በምስራቅ አፍሪካ፤በአውሮፓና በአሜሪካ ተወዳድሮ ለመድረክ የበቃ ነው፡፡ በአሜሪካም በኒውዮርክ “ፍሊፕ ኢምበርግ” በሚባል ታዋቂ ባለሙያ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ እና የዚህ እንግሊዘኛ ተውኔት ደራሲ ማን ይመስሎታል? የኛዋ ጀግኒት መአዚ ነች፡፡ አኩርናለች! ግና እኛ መች ጀግናችን አልናት! ለእሷ ሳይሆን ለኛ ስንል፡፡ በእርግጥ መአዚ ልታይ ልታይ አትወድም፡፡ ነጻነቷን ማጣት አትፈልግም፡፡
“እኔ በነጻነት መኖር የምፈልግ ሰው ነኝ! መንገድ እንኳን እየሄድኩኝ ሰዎች ትክ ብለው እንዲያዩኝ የማልፈልግና በጣም ነጻነቴንና ብቻዬን ያለሁ እስኪመስለኝ ድረስ በመንገድ መሄድ የምፈልግ ሰው ነኝ!” ትላለች መአዛ ወርቁ፡፡ ደራሲዋ፤አዘጋጅዋ፤ከቀንደኞቹ የቴአትር መቶኛ አመት ንቅናቄ አጋፋሪዋ፤አንዷ!
ጀግኒት ከትናንሽ ህልሞች ይልቅ ትልልቅ ህልሞች ላይ ጊዜዋን ታጠፋለች፡፡ ለዚህም እኮ ነው የ100ኛ አመት የቴአትር ንቅናቄ በሃሳብ ተወልዶ ወደ ተግባር የተለወጠው፡፡ ሃሳቡን ብዙዎች እንዳዋለዱም እማኝ ነኝ፡፡ ሁሉም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ሀሳብ፤እውቀት፤ገንዘብና ጊዜ አዋጥተዋልና፡፡ ምንም ፈተናው ከባድ ቢሆንም ይኸው የንቅናቄው አባላት ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ እየታየ ነው፡፡ ሰሞኑንም ከነሐሴ 21-25 ቀን 2013 ዓ.ም የቴአትር ፌስቲቫል ይካሄዳል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርም መደበኛ ቴአትሮች ቆመው ፊስቲቫሉን ያስተናግዳሉ፡፡ እሰየው፤ተገቢም ነው፡፡ 50 አጫጭርና የሙሉ ሰአት ቴአትሮች በተለያዩ አዳራሾች ይቀርባሉ፡፡ ለተመልካቹም በነጻ የሚታዩ ይሆናሉ፡፡ እኔም ፕሮግራሙን ከማስተዋወቅ አልቦዝንም፡፡
መአዚና የንቅናቄው አባላት ወዳጆችሽ ባለቤትሽን ዘካሪያስ ካሱን ጨምሮ በቴአትር ዙሪያ ስላደረጋችሁት አስተዋጽኦ ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ ክበሩልኝ፡፡