ዓለም ሬንጀሮች ቀን፤ ሀገር አደባባይ ያላወጣቻቸው የሀገር ጀግኖች!
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
ዛሬ ዓለም የሬንጀር ቀንን እያከበረ ነው፡፡ የዱር ሕይወት ጥበቃ ባለሙያዎች የፕላኔታችንን ዱር ህይወት ለመጠበቅ ነፍሳቸውን ያልሳሱ ዓለም አቀፋዊ ጀግኖች ናቸው፡፡ በመላው ዓለም ለዓለም ጤናማነት ጤናን መገበር ቀላል ኾኖ ህይወትን ስጦታ በመለገስ የሚሰራ ሙያ ነው፡፡
እንደ WWF የዓለም ዱር እንስሳት ፋውንዴሽን መረጃ ባለፉት አስር አመታት ከ871 በላይ የዓለም ሬንጀሮች በስራ ላይ እያሉ ህይወታቸው አጥተዋል፡፡
ሬንጀርስ የዓለምን ዱር እንስሳት በዙሪያቸው ካሉ ሁሉም ስጋቶች የሚከላከሉ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ናቸው፡፡ ዓለም መስመሮች ይላቸዋል፡፡ ጥፋት እንዳይኖር የተከለሉ፤
እንደ አፍሪካን ፓርክስ መረጃ በሬንጀሮች ጥረት በማላዊ የሚገኙት የማጄቴ ሬንጀር ቡድኖች Majete’s Ranger teams አውራሪስ እና ዝሆን አደንን ታድገዋል፡፡
በበቻድ ዛኩማ ውስጥ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው የ Mamba Ranger አደን አደብ አስገዝተው ዛሬ ከአስርተ ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቁጥራቸው የጨመረ ዝኆኖች መጠለያ ጠባቂ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ አዳዲስ ኤልሞሌዎችም እየታዩ ነው፡፡ በጋራምባ ሬንጀርስ Garamba’s Rangers ዛሬ የዝኆን አደን በግማሽ እጅ ቀንሷል፡፡
ዓለም ባንክ በበኩሉ የዱር ህይወትን ለመጠበቅ ሲሉ በብሔራዊ ፓርኮችና በዱር እንስሳት መጠለያዎች ውስጥ በሥራ ላይ እያሉ በየዓመቱ 150 የሚደርሱ የዱር ህይወት ጠባቂዎች ህይወታቸውን ያጣሉ ይላል፡፡
ዓለም ባንክ ባወጣው መረጃ ለአብነት ባነሳው በዛምቤዚ እና ዙምባቤ ሸለቆ የዱር ሕይወት ጀግኖች የነቃ እንቅልፍ በሚሉት መርህ የተራዘመውን የፓትሮል ስራ ለቀናት ምሽት ከሌት የሚከናወንን የዱር ህይወት ጥበቃ ከባድ ፈተናዎች አስፍሯል፡፡
Wildlife Ranger Challenge ያሉ ተቋማት ዛሬም ለእነኚህ የዱር ህይወት ጀግኖች ዓላማ ማሳኪያ ዓለምን ነዋይ ይማጸናሉ፡፡
እንደ One Earth ጥናት በአፍሪቃ የሚገኙ የሬንጀሮች ቁጥር አርባ ሺህ ይደርሳል፡፡ ለሚወድመው የአህጉሪቱ ተፈጥሮ ሀብት ይህ ቁጥር በራሱ እጅግ ትንሽ ቢሆንም የሚያሳዝነው ግን ሞት የተጋፈጠበት የስራ መስክም መሆኑ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ሬንጀሮች ከዓለምም ኾነ ከአፍሪቃ የከፋ እጣ ፈንታ አላቸው፡፡ የሚሰሩትን የሚያውቀው ጥቂት ነው፡፡ ማን እንደሆኑ የሚረዳው ህዝብ ቁጥሩ ገና አላደገም፡፡ ብዙ ችግሮች አሉባቸው፡፡ በደሃ ሀገር እንኳን ዱር እንስሳ ሰው መጠበቅና መታደግ ፈተናው ብዙ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካል ስርዓት ሰው ነው እንስሳ የሚበልጠው ብሎ ለሰው የሚጠበቅ እንስሳና መኖሪያውን ለማውደም ለተፈጥሮ ጥበቃ ጀርባውን ሰጥቶ ኖሯል፡፡ በዚያ ሁሉ ፈተና ውስጥ ከባዱን ስራ እየሰሩ ቀላል ድጋፍ ሳያገኙ የኖሩ ጀግኖች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዱር ህይወት ጥበቃ ጀግኖች አደባባይ አይታዩም፡፡ ሀገር ስማቸውን ጠርታ አመሰግናለሁ ብላቸው አታውቅም፤ ግን ሀገር አኑረዋል፡፡ ሀገር አትርፈዋል፡፡ አንዳች ሳያመነቱ ለሀገር ኖረዋል፡፡
ዛሬ ዓለም የዱር ሕይወት ጥበቃ ጀግኖችን ቀን ከዳር ዳር ያከብራል፡፡ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ ላይ ታከብረዋለች፡፡ ተግባራቸው ይዘከራል፡፡
የኢትዮጵያ ሬንጀሮች ሀገራዊ ማኅበር አቋቁመዋል፡፡ እርግጥ ነው በጎረቤት ሀገርና በተፈጥሮ ሀብቱ በምንቀናበት የአፍሪካ ምድር ሁሉ ሙያው ክብር አለው፡፡
እዚህ ግን እያንዳንዱን ቀን ከሞት ጋር መጋፈጥ ነው፤ መሞትና ቤተሰብ መበተን፡፡ በእኛ ሀገር እንደሌላው የአፍሪቃ ሀገር ደን አላስወድምም፣ እንስሳ አላሳድንም ብሎ ሲዋደቅ ለሞተ ጀግና ቤተሰብ የሚተርፍ አንዳችም የፍቅር ልብ የለም፡፡
ማን ያውቃል ነገ ሁሉም ጥሩ ይሆናል፡፡ ወደ ብሔራዊ ፓርኮቹ የተመለከተው ብልጽግና ወደ ጠባቂዎቹ የሚያይበትም እድል ይኖራል፡፡
ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ ለሀገራችሁ የተፈጥሮ ፍቅር ለወደቃችሁ፤ ስኬት ሰላም እና ውጤት ዛሬም በጽናት ለቆማችሁ ይሁን!