እንደምን ነው ኮንታ፤ ጉም ያጣፋው ምድር
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጉዟል፡፡ አመያን ጉም አጣፍታ ደርስኩባት ሲል የኮንታ ቆይታውን ትረካ ይጀምራል፡፡ ገበታ ለሀገር በታወጀበት ውቡ የሀገራችን ክፍል ያደረገውን ቆይታ ትከታተሉት ዘንድ ጋበዝናችሁ፤)
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
አመያ አትታይም፡፡ ሁሌም ስደርስ እንዲህ ናት፡፡ ዛሬም አስቀድሳ የምትመለስ ወይዘሮ መስላለች፡፡ ተፈጥሮ ከሰማይ ነጭ ኩታ አልብሳት የቀጠሯት ተራሮች ሳይቀር ተሸሽገዋል፡፡ ጉም ያጣፋችው የኮንታዎች መዲና ተቀበለቺኝ፡፡ ከዚህ በኋላ የለጋሱ ምድር እንግዳ ነኝ፡፡
ለምን አትመጡም? ሩቅ አይደለም፡፡ ይህ ከአዲስ አበባ በጅማ ለዘለቀ 454 ኪሎ ሜትር ቢጓዝ የሚደርስበት ምድር ነው፡፡ በወላይታ ለሚመጣ ደግሞ የዳውሮን ተአምራዊ ምድር እየጎበኘ በታርጫ አድርጎ እዚህ ይደርሳል፡፡ እኔ ደርሻለሁ፡፡
ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ህዝብ የሚኖርበት የኮንታ ምድር 8 የከተማ እና አርባ አራት የገጠር ቀበሌያት ያዋቀሩት ልዩ ወረዳ ነው፡፡ አርባ በመቶው ቆላማ ቢሆንም አስር ወር ድረስ ዝናብ የማይነጥፍበት የበረከት ምድር በመሆን ይታወቃል፡፡
አመያ ትቀዘቅዛለች፡፡ እዚህ አንድ ቀን ነው የማድረው፡፡
በዙሪያዋ ከሚገኙ መስህቦች አንዱ የሆነውን ፏፏቴ እጎበኛለሁ፡፡ ከዚያ ወደ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ አብረን እንጓዛለን፡፡ እዚያ ተደብቆ የኖረውን ሐይቅ ፍለጋ አብራችሁኝ ትደክማላችሁ፡፡
የአመያ ውበት የከበባት መልካዓ ምድር ነው፡፡ አቤት ሞገስ፤ ተራሮች እንዲህ ለከተማ ሲያረግዱ መመልከት ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥር አልነግራችሁም፡፡
አሁን አብረን የምንጓዘው ወደ ሾኬላ ነው፡፡ ዝናብ ዘንቧል፡፡ መንገዱ የሞተር ሳይክል ጉዞን የሚፈልግ ነው፡፡ ሦስት ሞተሮች ላይ ወጥተን በታከለ መሪነት ወደ ፊት ገሰገስን፡፡
ታከለ ወጣት ነው፡፡ የልዩ ወረዳውን ባህልና ቱሪዝም ይመራል፡፡ እንዲህ ያለ አገልጋይነት መቼም የሚደንቅ ነው፡፡ እረፍት አይሻም፤ ዳገት ቁልቁለቱን ደስ እያለው አውጥቶ አወረደን፡፡ አብሮ ያለበት እንግልት ከባድ ነበር፡፡ ሰባት ኪሎ ሜትሮች ተጉዘን የሞተሩ ጉዞም አበቃ፡፡ ቀሪው መንገድ የእግር ኾነ፡፡
እውነት ለመናገር ከባድ ነበር፡፡ በጋ ቢሆን አልያም ባይዘንብ እንዴት ቀላል ጉዞ እንደሚሆን ገመትኩ፡፡ አሁን ግን ሳሩ ውሃ ጠጥቷል፡፡ ጎዳናው ቁልቁለት ነው፡፡ ሁለቴ ራሴን ስንከባለል አገኘሁት፡፡ ስቆ ማለፍ፣ ተነስቶ መቆም፤ ድጋሚ መንገድ መቀጠል፡፡
የኮንታ መንደሮች ያምራሉ፡፡ ዓይኔ ግራና ቀኝ ተንከራተተ፤ ውበታቸው እግር ይጎትታል፡፡ ማሳው ልምላሜ ለብሷል፡፡ ተራሮች እዚህ እርቃናቸውን አይደሉም፡፡ አረንጓዴ ናቸው፡፡ ደጋው ምድር ጢስ የሚተፋ ጉም ይንደባለልበታል፡፡
እዚህ ፏፏቴ ብርቅ አይደለም፡፡ የመንደሩ ዥረት የሚሰራው ትዕይንት ሌላ ቦታ ቢሆን ስንት የሚወራለት የተፈጥሮ መስህብ በሆነ፡፡ መንገድ ላይ የማልፋቸው፣ ከተራራው የሚንደረደሩት ወንዞች አንዳች ምስል ፈጥረው ቁልቁል ይገማሸራሉ፡፡
እኔ ግን ወደ ሾኬላ ተጓዥ ነኝ፡፡ የሾኬላ ናፋቂ፡፡ ስሙ ነው፡፡ ስንደርስ የምንመለከተው ፏፏቴ፣ ዋሻ ጉያው የሸጎጠ መስህብ፡፡ ጓጓሁ፡፡ አይቼው አላውቅም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ እየሄድኩ ነው፡፡ እናንተም ልክ እንደ እኔ ናችሁ፡፡ ቁልቁል ደልዳላ ሜዳ ላይ ጎጆ አርፋለች፡፡ ድምጹ መሰማት ጀመረ፡፡ ደስ አለኝ፡፡