ታላቋ ኢትዮጵያዊት እትዬ እሌኒ መኩሪያ አረፈች
(ጥበቡ በለጠ)
በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ አላት። በእንግሊዝኛ ቋንቋ የጋዜጠኝነት ሙያ ከኢትዮጵያ እስከ እንግሊዙ ቢቢሲ ሬዲዮ በወርቃማ ድምጿ አገልግላለች። ቢቢሲ ላይ አፍሪካዊቷ ኮከብ ነበረች።
እትዬ እሌኒ የሐኪም ወርቅነህ እሸቱ የልጅ ልጅ ናት። ሐኪም ወርቅነህ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ሲሰው እርሳቸው የሶስት አመት ህጻን ነበሩ። አባታቸውም ልክ እንደ አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላ አምባ መስዋዕት ሆነዋል። የእንግሊዝ ወታደሮች የአጼ ቴዎድሮስን ልጅ፣ ልዑል አለማየሁን እና የሶስት አመቱን ልጅ፣ ወርቅነህን ከኢትዮጵያ ይዘው ሄዱ።
ልዑል አለማየሁን እንግሊዝ ለንደን ውስጥ አሳደጉት። ወርቅነህን ደግሞ ቅኝ ግዛታቸው በሆነችው ሕንድ አገር ውስጥ አሳድገው አስተማሩት። ወርቅነህ በመጨረሻም የሕክምና ዶክተር ሆነ። በርማ ውስጥም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እስከ መሆን ደርሷል። የአድዋ ጦርነት በ1888 ሊካሄድ ሲል ወደ ኢትዮጵያ ሐገሩ ሲመጣ ሶማሌያ ድንበር ላይ ያለ የእንግሊዝ ኮሎኔል ከለከለው።
” ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ልትገባ ስለሆነ ለደህንነትህ ሲባል ይለፍ አልሰጥህም” አለው።
ወጣቱ ዶክተር ወርቅነህም ተከራከረ። “እንደውም አሁን ለጦርነቱ ለኢትዮጵያ ልድረስላት። ሐገሬን፣ የናፈቀችኝን ምድሬን ልዋጋላት” ብሎ ከፍተኛ አምባ ጓሮ ተፈጠረ።
“አንተ እንግሊዛዊ ነህ። አልፈቅድም” ብሎ ኮሎኔሉ ክችች አለ።
ዶክተር ወርቅነህም እያለቀሰ ተመልሶ ወደ በርማ ጉዞ ቀጠለ። የሶስት አመት ህጻን እያለ ከጀግኖች ምድር ተነጥቆ የሄደው ወርቅነህ፣ ወላጆቹ እንክዋን እነማን እንደነበሩ ገና አላወቀም ነበር። ኢትዮጵያ አገሩም ምን እንደምትመስል አያውቅም። የሚጠራበት ስም እንግሊዞቹ ባወጡለት ስም “ማርቲን” ተብሎ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ የአድዋን ጦርነት ስታደርግ አብሬ ባለመሆኔ ብሎ አለቀስ።
ወደ በርማ እየተጓዘ ሳለ በአለም ላይ ታላቅ ዜና ተደመጠ። ኢትዮጵያ አድዋ ላይ በግማሽ ቀን ጦርነት ኢጣሊያን አሸነፈች ተባለ። የነ ምኒልክ፣ የነ ጣይቱ ጀግንነት በአለም ላይ እየናኘ ይተረክ ነበር።
ወጣቱ ዶክተር ወርቅነህ አሁንም የደስታ እንባ አነባ። የማንነቱ መለያ ሐገሩ ኢትዮጵያ አሸነፈች። መንገዱ፣ ጉዞው የደስታ ሆነ። በርማ ደረሰ። አሁንም ልቡ ወደ ኢትዮጵያ ተንጠለጠለች። ከስድስት ወር በኋላ ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ ተጓዘ።
አሁን ተፈቀደለት። ወደ ኢትዮጵያ ገባ። አዲስ አበባ ሲደርስ ከአጼ ምኒልክ እልፍኝ በክብር አቀባበል ተደረገለት። ምኒልክ እና ጣይቱ ተቀበሉት። ወጣቱ ዶክተር ማርቲን የሕይወት ታሪኩን ተረከላቸው። ከመቅደላ ጦርት ላይ በሶስት አመቱ ተይዞ ወደ ሕንድ መሄዱን ተናገረ። ወላጆቹን እንደማያውቃቸው ተናገረ።
ምኒልክና ጣይቱ ጎንደር ላይ አዋጅ አስነገሩ። በመቅደላ ጦርነት ልጅ የጠፋህ ካለህ እኔ ዘንድ አለ። ከፈለከው ወደ እኔ ዘንድ ና! ብለው አወጁ። አንዲት ትልቅ ሴት መጡ። ከምኒክ እልፍኝ እንደገቡ ደነገጡ። ወዲያው በደስታ እልልልልል! አሉ። ሮጠው ሄደው ወጣቱን ሐኪም አቀፉ። ወርቅነህ! ወርቅነህ! ወርቅነህ! እያሉ ጮሁ። ምኒልክና ጣይቱ ግራ ገባቸው። እናም ሴትየዋን ጠየቁ።
ስሙ ማን ነው? አሉ።
ሴትየዋም “ወርቅነህ ነወ። አባትና እናቱ መቅደላ ዘምተው ነበር። አባቱ በጦርነቱ ሞቷል። ልጁ ወርቅነህም በጦርነቱ ጠፋ። የወርቅነህ እናትም በልጇ መጥፋት አረረች። በብስጭትም ሞተች። እናቱ ልጄ ናት። አያቱ ነኝ።
አሳድጌዋለሁ። እግሩ ላይ የተፈጥሮ ምልክት ጠባሳ አለበት።” አሉ ሴትየዋ።
ምኒልክም የሐኪሙን ምልክት ሲጠይቁ እውነት ሆነ። ምኒልክ ዶ/ር ማርቲን፣ ዶ/ር ወርቅነህ እሸቱ ማለት ነው አሉ። ከዚያም ምኒልክ እና ሐኪም ወርቅነህ ወዳጅ ሆኑ። ሐኪም ወርቅነህ የምኒልክና የጣይቱ የግል ሐኪም ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ከዚያም ሐኪም ወርቅነህ ከወይዘሮ ቀጸላ ቱሉ ጋር ሚኒልክ አጋቧቸው። በርካታ ልጆችም ወለዱ።
ፋሽስቶች ከ40 አመታት በኋላም ተመልሰው ኢትዮጵያን ሲወሩ ሐኪም ወርቅነህ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ፋሽስቶችን ተፋልመው፣ ልጆቻቸውን በጦርነቱ መስዋዕት አድርገው የኢትዮጵያን ነጻነት አስከብረዋል።
እንግዲህ በሕይወት ያጣናት ታላቋ ጋዜጠኛ እትዬ እሌኒ መኩሪያ የእኚህ የሐኪም ወርቄነህ የልጅ ልጅ ናት። የጀግና ዘር፣ በሙያዋም ጀግና ነበረች። ሙያዋ ትምህርት ቤታችን ነበር። አዋቂ፣ ለኢትዮጵያ ጥልቅ ፍቅር የነበራት፣ ተጫዋች፣ ቀልደኛ፣ ሰው ወዳድ፣ የጋዜጠኝነት ሙያ ፈርጥ ነበረች። እትዬ እሌኒዬ ፈጣሪ ነብስሽን ይማርልን።
***
ከአዘጋጁ:- የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሀኪም ወርቅነህ የልጅ ልጅ የዕሌኒ መኩሪያ የቀብር ሥነስርዓት ሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ 6 በየካ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ይፈጸማል፡፡