“ዘመቻችን የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግሥት የማጽናት ተልዕኮ ነው” የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
አሸባሪው ትህነግ ከፍጥረቱ ጀምሮ ፀረ-ኢትዮጵያ ሆኖ የተነሳ ድርጅት ነው፡፡ በተለይም የአማራን ሕዝብ እንደ ቀዳሚ ጠላት ፈርጆ መነሳቱ በታሪክ የተመዘገበ እውነታ ነው፡፡ ሴረኝነት፣ ጸረ-ሕዝብነት፣ የግዛት ተስፋፊና ተገንጣይነት የዚህ ድርጅት መገለጫ ባህሪያት ናቸው፡፡ ይሄን እውነታ ከአሸባሪው ትህነግ ማንፌስቶ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ኢትዮጵያን በበላይነት በገዛባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት የአገዛዝ ባህሪው፣ የተጠኑ ሴራዎቹና በሕዝብ ደም ፖለቲካ የመስራት ደመ-ቀዝቃዛ ድርጊቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡
በሌሎች ጉዳት ላይ የተመሠረተ ተናጠላዊ ጥቅምን በማረጋገጥ የሚታወቀው አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን እርስ በርስ በማጋጨት እራሱን ዳኛ አድርጎ በመሾም የአገዛዝ ዕድሜውን በሸፍጥና በሴራ ሲያስቀጥል የኖረ እኩይ ኃይል ነው፡፡
ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሁለት ሐገረ-መንግሥት እይታ ያለው፣ አንድም ቀን ለሕዝቦች አንድነት የማይጨነቅ፣ በሥልጣን ላይ እስከቆየና የበላይነቱን የሚያረጋግጥበት ጥቅም እስካገኘ ድረስ ብቻ ‹አስመሳይ የአንድነት ኃይል› ሁኖ መቀጠል የሚፈልግ፤ ነገር ግን የእኩልነት፣ የነጻነትና የእውነተኛ ፌዴራሊዝም ጥያቄዎች ሲነሱበት የሚበረግግ፣ የተገንጣይነት አጀንዳውን የሚያነሳ ‹የዥዋዥዌ ፖለቲካ›ን የሙጥኝ ብሎ የኖረና አንዳች እምነት የማይጣልበት ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነ ስብስብ ነው፡፡
ለዘመናት ሲሰራው የነበረውን ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባሮቹ በመላ ኢትዮጵያዊያን የማያቋርጥ ትግል እንዲሁም እንደድርጅት ከሌሎች የለውጥ ኃይሎች ጋር በመሆን በግንባር- ቀደምትነት አምርረን በመታገላችን ጥፋቱ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ፊት ተጋልጧል፡፡
ከለውጥ ማግሥት በአደባባይ ተሸንፎ ህዝባዊ እርቃኑ የተጋለጠበት አሸባሪው ትህነግ፣ ከአፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ድርጊቱ ከመጋቢት 2010 እስከ ጥቅምት 24/ 2013 የሀገር ክህደት ተግባሩ ድረስ 113 ግጭቶችን በመላ ኢትዮጵያ ላይ አስነስቷል፡፡ በእነዚህ ግጭቶች ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከኃይማኖት፣ መንግሥትን ከሕዝብ፣…ወዘተ ለማቃቃር በፕሮፖዳንዳ፣ በፋይናንስ፣ በሎጀስቲክስና በሥልጠና የተደገፉ አውዳሚ ግጭቶችን ፈጥሯል፡፡
በግብሩ ልክ የቀረጻቸውን ‹ሳተላይት አሸባሪዎች› በአራቱም ማዕዘናት ለጥፋት ተልዕኮው አሰማርቶ መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችን ወግቷል፡፡ ረፍት ነስቷል፡፡ በትህነግ እኩይ ሴራ ደም ያልፈሰሰበት የኢትዮጵያ ግዛት አካል የለም፡፡
ይህ አልበቃው ብሎ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ውህድ ማንነት አካል የሆነውንና የሐገረ-መንግሥቱ ዘብ ስለመሆኑ በተግባር በማስመስከር ላይ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከጀርባው በመውጋት የእናት ጡት ነካሽ ከሃዲነቱን በተግባር አስመስክሯል፡፡ ይህ ታሪክ ፈጽሞ ሊዘነጋው የማይችል ጸረ-ኢትዮጵያ ድርጊቱ የአሸባሪውን ኃይል የመከነ ስብዕና ለአለም ያጋለጠበት አውዳሚ ድርጊቱ ሁኖ ተመዝግቧል፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ካለው ንቀት የተነሳ የሕዝብ ልጅ የሆነውን የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ከጀርባ ወግቶ ስለሕገመንግሥቱ መከበር ደጋግሞ ሊያወራ ሞክሯል፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የጦር ወንጀለኝነት እና ሕገ-መንግሥታዊነት እንደሚለያዩ ከገባው ቆይቷል፡፡ ልጆቹ በግፍ የታረዱበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአራጁ ዕድል የሚሰጥበት ጊዜ የለውም፡፡
ሰብዓዊ ኃላፊነትና የሞራል ግዴታዎቹን በተግባር በማስመስከር ላይ ያለው የኢፌዴሪ መንግሥት ከሳምንታት በፊት የተናጠል የተኩስ ማቆም አቋሙን ይፋ ሲያደርግ ውሳኔው ፖለቲካዊና ሰብዓዊ እንድምታዎችን ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡ ይሁንና ሰብዓዊም ሆነ የሞራል ኃላፊነቶች የማይሰማው አሸባሪው ትህነግ የሰላም አማራጮችን ከመጠቀም ይልቅ በአሽሽ የደነዘዙ ታዳጊ ህጻናትን ከፊት አሰልፎ የሚዋጋበትን የጥፋት መንገድ የሙጥኝ ማለትን መርጧል፡፡ አሸባሪው ኃይል በአፈቀላጤው በኩል ዓላማው ‹ኢትዮጵያን ማፍረስ› ስለመሆኑ ለአለማቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ የእብደት ተግባሩ መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን በቁጭትና በእልህ ዳግም እንዲነሱ አድርጓቸዋል፡፡
ዛሬ ከየአቅጣጫው ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት በጋራ ተሰልፈው ወደግዳጅ ቀጣና እየዘመቱ ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች መነሻ ምክንያታቸው የተናጠል ሳይሆን የጋራ ዕጣ ፈንታ ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡ አሁን አጠቃላይ ትግሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከአሸባሪው የትህነግ የጥፋት ኃይል ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ስለመሆኑ በተግባር በመታየት ላይ ነው፡፡
ዘመቻው የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ህልውና የማስከበር ልዩ ተልዕኮ አካል ነው፡፡ ሲንቃቸውና ሲነግድባቸው የኖሩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነውን አሸባሪውን ትህነግ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የሐገረ-መንግሥቱን ህልውና ለማጽናት የጋራ ተልዕኮ ላይ ናቸው፡፡
የሀገር ህልውና ከልዩ ልዩ ማኅበረሰቦችና የብሔር ብሄረሰቦች ታሪካዊ አንድነት፣ የጋራ መስዋዕትነቶች፣ ኅብረተሰባዊ እሴቶች፣ የእምነቶች ትስስርና በአብሮነት የመዝለቅ ተስፋ በማሳደር የሚወሰን ጉዳይ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውም መነሻው ከዚህ ተጨባጭ እውነታ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ ከሀገረ-ኢትዮጵያ ምስረታ ጀምሮ ያለው የሺህ ዓመታት ታሪካችንም የሚያሳየን ይህንን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህልውና በጋራ ቁመን የምንጠብቀው እንጅ ለጥቂቶች አደራ የሚሰጥ ጉዳይ እንዳልሆነ የውጭ ወራሪዎችንና የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን በጋራ ቁመን የመከትንባቸውና ድል የነሳንባቸው ብሔራዊ ኩራት የሆኑን (የጦርነት) የጋራ ድሎቻችን ሕያው ምስክር ናቸው፡፡
ትላንት በአያት ቅድመ አያቻችን የታየው ኢትዮጵያዊ ወኔና ህብረት ዛሬ በዚህ ትውልድ ላይ መታየት ጀምሯል፡፡ የሀገር ህልውና ፈተናችን በድል እንደምንሻገረው ብሔር ብሔረሰቦች የኢትዮጵያን ሐገረ-መንግሥት የማጽናት የጋራ ተልዕኮ ላይ በጋራ መሰለፋቸው አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡
ቆም ብለን ታሪካችንና አሁን እንደሀገር እያንዣበቡብን ያሉ ብሔራዊ አደጋዎችን ስናስተውል የዛሬው አይነት አንድነት የኢትዮጵያ ብቸኛ መሻገሪያ መንገድ ስለመሆኑ እናምናለን፡፡
ዛሬ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት የማይፈልጉ፤ ሀገሪቱ ተረጋግታ ወደ ልማት ስራዎች ትኩረት ማድረጓ የሚያሳስባቸው የውጭ ኃይሎች በቀጠናው እያንዣበቡ ነው፡፡
አፍንጫችን ስር ደርሰው እየዛቱብን ትንኮሳም እየፈጸሙብን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገር ውስጥ ባንዳ የሆነው አሸባሪው ትህነግ ግንባር ቀደም አጋር ሁኗል፡፡ በግልጽ እኛን ለማተራመስ እየሰሩ ባሉበት በዚህ አስቸጋሪ የፈተና ወቅት፤ እንደኢትዮጵያ በጋራ በመቆም ኃይልና አቅማችን አሰባስበን ህልውናችንን ለማጽናት የጋራ ክተት አዋጅ አውጀናል፡፡
አዋጁም ኢትዮጵያዊነት የጋራ መዳኛ ምርጫችን ስለመሆኑ በተግባር አስመስክረንበታል፡፡
ሁሉም ክልሎች በመግለጫዎቻቸው ያሰመሩት ሀቅ ትህነግ የኢትዮጵያ ካንሰር ስለመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነት የህልውና ፈተናችን መሻገሪያ ተደማሪ ጉልበት ስለመሆኑ በመግለጫዎቻቸው አጽኖት ሰጥተውበታል፡፡
በዚህ የጋራ ዘመቻችን ኢትዮጵያዊነት በነጻነት የመኖር ምልክት ስለመሆኑ ዳግም እናረጋግጣለን፡፡ ኢትዮጵያዊነትን መምረጥ ነጻነትን መምረጥ ስለመሆኑ በግብር የምናስመሰክርበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡
ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች ያሉባት፣ ብዝሃ ባህል የሚንጸባረቅባት ታሪካዊ ሀገር የመሆኗን ያህል በህልውና ትግሏና በነጻነት ታሪኳ እንደአንድ ቤተሰብ በጋራ የመሰለፍ አኩሪ ታሪክ ያላት የነጻነት ቀንዲል ስለመሆኗ አለም የሚመሰክረው እውነት አለን፡፡ ይህን እውነት ዛሬም በተግባር ማስመስከራችንን እንቀጥላለን፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ልጆች ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ለሐቀኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት፣ ለእውነተኛ ህገ-መንግስታዊ ስርዓትና ለእውነተኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ለጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት ፅኑ እምነት ይዘው መታገላቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ይህን ዘመቻም የኢትዮጵያን ሐገረ-መንግሥት የማጽናት ተልዕኮ ነው ስንል መዳረሻ ግባችን የጋራ ነጻነት በመሆኑ ነው።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት
ሐምሌ 10/2013
ባሕርዳር-ኢትዮጵያ
(አሚኮ)