የአባይ አጀንዳ ወደአፍሪካ ህብረት እንዲመለስ ተወሰነ
~ የግብፅና ሱዳን ሀሳብ ወዳጅ በሚሏቸው ሀገራትም አልተደገፈም፣
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ኃላፊነት ጸጥታን በሚያደፈርሱ ጉዳዮች ላይ መምከር እንጂ የኤሌትሪክ ማመንጫ ግድብን በሚመለከት መወያየት ባለመሆኑ ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ ዶ/ር ኢጂነር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ።
በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ዛሬ ለሊቱን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሲመክር የሃገራቸውን የኢትዮጵያን አቋም ያስረዱት ሚኒስትሩ ምክር ቤቱም ከተመሰረተ ግዜ አንስቶ በግድብ ጉዳይ ሲመክር ይሄ የመጀመሪያው ነውም ብለዋል።
ግብጽና ሱዳን ጉርብትናን፣ አብሮ መልማትን ሊማሩ ይገባል፤ የነሱ ፍላጎትም በቅኝ ግዛት ውል ሰበብ ውሃውን ለብቻቸው የመጠቀም ፍላጎት ነው አንዱ እየጠጣ ሌላው የሚጠማበት አካሄድ አግባብ አይደለም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
እንደ ህዳሴ ግድብ አይነት ፕሮጀክቶችን መገንባት ተሰደው ከሄዱበት ሃገር በባዶ እግራቸው የሚባረሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት የሚቀይርም ነው ብለዋል።
በግብጽ ፍላጎት ስብሰባ የተጠራው የፀጥታው ምክርቤት አባላት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ዛሬ ለሊቱን በመከረበት በዚህ መድረክ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገራት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ድርድሩ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።
በስብሰባው ላይ የግብጽና ሱዳን ተወካዮችም ንግግር አድርገዋል።
የሃገራቸውን የኢትዮጵያን አቋም ያስረዱት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ምክር ቤቱ በህዳሴው ግድብ ላይ የሚያደርገው የመጨረሻው ስብሰባ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ በማለት ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ ጠይቀዋል ሲል ኢትዮ ኤፍ ኤም ዘግቧል ።
በመጨረሻም የፀጥታው ው ምክር ቤት አባል አገራት በምሽቱ ጉባዔ የህዳሴ ግድቡ ድርድር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲቀጥል ወስነዋል::
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተወካይ በመድረኩ ላይ እንዲህ ብለዋል።”የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት መፍትሄ ይሰጠዋል። የፀጥታው ምክር ቤት አስፈላጊ ከሆነ አፍሪካ ህብረትን ሊደግፍ ይችላል”
በተጨማሪም ጎረቤት ኬንያ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ሜክሲኮ፣ ቻይና፣ አየርላንድ፣ ሩስያ፣ ሕንድና ሌሎች በርካታ ሀገራት ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት መታየቱን እንዲቀጥል በመስማማት የግብፅና ሱዳንን አሳሪ ስምምነት ይፈፀምልን አቤቱታ ውድቅ አድርገዋል።