Connect with us

ቴሌብር ምን ይዟል?

ቴሌብር ምን ይዟል?
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ቴሌብር ምን ይዟል?

ቴሌብር ምን ይዟል?

(ፀጋዬ ዳባ)

በተያዘው ሳምንት ኢትዮ ቴሎኮም ‹ቴሌብር› የተሰኘውን የብር ማስተላለፊያ መንገድ በይፋ ሥራ አስጀምሯል፡፡ መተግበሪያው ማንኛውም ሰው በእጁ ላይ ባለው የእጅ ስልክ ምክንያት ወደ ፈለገው ሰው ገንዘብ ማስተላለፍ የሚችልበትን ሥርዓት የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በአገራችን ካሉት ባንኮች በላይ ተደራሽነት ያለው ተቋም ነው፡፡ በመሆኑም የተቋሙ ወደ ዘርፉ መግባት የባንክ ተደራሽ ላልሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ትልቅ ዕድል ይዞ ይመጣል፡፡ ቴሌ ከ53 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ተቋም መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ 

ተቋሙ ይህን አገልግሎት በማስጀመሩ ከ53 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ይህን የፋይናንስ ሥርዓት የሚጠቀሙበትን ዕድል ስለሚፈጥር የሚኖረው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡

በአገሪቱ ከ16 በላይ ባንኮች ቢኖሩም እስካሁን የፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል 35 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም ሁለት እና ሦስት የባንክ ሒሳብ ደብተር ያለው ዜጋ በርካታ ነው፡፡ ቁጥሩን ከመቶኛ አውጥተን ብናየው የባንክ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ  ከ35 ሚሊዮንም በታች ነው፡፡ የቀረው ከ65 ሚሊዮን በላይ ዜጋ እስካሁን ድረስ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ አይደለም፡፡ 

ይህን ዓይነቱን ትልቅ ክፍተት በሞባይል ስልክ በኩል ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መታሰቡ ሊበረታታ የሚገባው ድንቅ ሀሳብ ነው፡፡ የቴሌብር ዋነኛው ዓላማ የፋይናንስ ተቋም ተደራሽ  ያልሆነውን ሰፊውን የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ ነው።

አገልግሎቱ በቀላሉ የሚገኝ እና በየትኛው ስልክ መጠቀም  የሚያስችል በመሆኑ ከገጠር እስከ ከተማ ያለውን ማኅበረሰብ በአንድ ላይ አገልግሎት መስጠት ያስችላል፡፡ ቴሌ ብር ወደ አገልግሎቱ መምጣቱ በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት በቅንጅት የሚሠሩበትን ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በዘርፉ ላይ ውድድር በመፍጠር ለአገልግሎቱ ማደግ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡

ባንኮች ከቴሌብር ጋር በጋራ የሚሠሩበትን ዕድል ለመፍጠር ለሁሉም ባንኮች ግብዣ መላኩን የኢትዮ ቴሌኮም  ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ተናግረዋል፡፡ በቴሌብር የገንዘብ ሥርዓት ላይ ባንኮቹን ለማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት  አብሮ መዘርጋቱን ሰምተናል ይህ ለባንኮቻችን ትልቅ ዕድል ነው። ባንኮች ተጨማሪ ሀብት ሳያወጡ በቀላሉ አዳዲስ ደንበኞችን የማፍራት እና አገልግሎት የመስጠት ዕድልን ይሰጣቸዋል፡፡

ቀደም ብሎ ባለው የባንኮች ሥርዓት አንድ ሰው የሞባይል ባንክ ተጠቃሚ ለመሆን የአንድ ባንክ ደንበኛ መሆንን እና ደብተር ሊኖረው ይገባል።  አሁን ወደ ተግባር የገባው  ቴሌብር በየትኛውም ባንክ ደንበኛ መሆን ሳይጠየቁ ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጠው የሲምካርድን ብቻ ደንበኞች አገልግሎቱን ማግኘት ይቻላሉ፤ አልያም በቀጣይ ኢትዮ ቴሌኮም ከባንኮች ጋር በሚፈጥረው ትስስር የሒሳብ ደብተር ላይ ያለን ተቀማጭ ማንቀሳቀስ የሚቻሉበትን ዕድል ይፈጥራል ተብሎ  ይታሰባል፡፡  ይኼ በገጠር ላለው  በተለይም የባንክ ተጠቃሚ ላልሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ትልቅ በረከት ነው።

ይህ አገልግሎት በጎረቤት አገራት ጭምር ቀደም ብሎ የተለመደ ቢሆንም በኢትዮጵያ ኢትዮ ቴሌኮም በዘርፉ ላይ እንዳይገባ ታግዶ መቆየቱን ተከትሎ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራን ከማይሠሩ ጥቂት ቴሌኮሞች መካል አንዱ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ የመንግሥት ይሁንታን አግኝቶ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ጎረቤት ኬንያ አገልግሎቱን ከ14 ዓመታት በፊት የጀመረች ሲሆን በዚህም ከ72 በመቶ በላይ የአገሪቱ ዜጋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሆነ ይነሳል፡፡

በዓለም ላይ በዚህ አገልግሎት በርካታ ልምድ ያላቸው ተቋማት ያሉ ሲሆን በሰባት አገራት የሚሠራው ኤምፔሳ 42 ሚሊዮን ንቁ ደንበኞችና 400 ሺሕ ወኪሎች በማፍራት በአፍሪካ ግንባር ቀደም ተቋም ሆኗል።

በቅርቡ ይፋ ለተደረገው ቴሌብር ገንዘብ ገቢ ወይም ወጪ የማድረጊያ ስርዓት  ለመጀመሪያ ዙር 1 ሺሕ 500 ወኪሎች መዘጋጀታቸውን ሥርዓቱ ይፋ በተደረገበት ቀን ላይ ሰምተናል፡፡  ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች በቀላሉ ይህን አገልግሎት ለመጠቀም እንዲችሉ ወኪሎቹን የማስፋት ሥራ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ በተለይም የመሠረተ ልማት ባልተሟላባቸው እና  የባንክ ዘርፉ ተደራሽ መሆን ባልቻለባቸው የአገሪቱ ገጠራማ አካባባዎች ላይ ወኪሎቹን ማስፋት ላይ ተቋሙ በትኩረት መሥራት አለበት፡፡

በቀጣይ አንድ ዓመት በቴሌብር ላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን እንደሚመዘግብና ከዚህ ውስጥ ከ12 ሚሊዩን በላይ የሚሆኑት ንቁ ደንበኛ ሆነው 710 ሚሊዮን ብር ይዘዋወራል ተብሎ እንደሚታሰብ ኢትዮ ቴሌኮም በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡ 

በዚሁ ሥርዓት በቀጣይ አምስት ዓመታት 33 ሚሊዮን ደንበኞች በማፍራት 3.5 ትሪሊዮን ብር ለማንቀሳቀስ አቅዷል፡፡ ይህን ዕቅድ ስናይ መንግሥት በቀጣይ የኤሌክትሮኒክስ የባንክ አገልግሎት ምን ያህል በፍጥነት ለማዳረስ ቁርጠኛ እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ለፋይናንስ ዘርፉ ትልቅ አብዮት የሚፈጥር ጉዳይ ነው፡፡

ሌላ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ገበያ ለሚቀላቀሉት የውጭ ተቋማት ይህ ሥርዓት ዝግ እንዲሆን የተደረገበትን ውሳኔ የሚደነቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ያልዘመነው የባንክ ሥርዓታችን ለውጭ ተቋማት በሩን ክፍት ማድረጉ ለፋይናንስ ሥርዓቱ አደጋ እንደሆነ በተደጋጋሚ በተለያዩ ባለሙያዎች (በዚህ ጋዜጣ ላይ ጭምር) ሲገለጽ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ መንግሥት ይህን ሰምቶ ለውጭ ተቋማት ይህን አገልግሎት ዝግ ማድረጉ የሚያስመሰግነው ነው፡፡

ነገር ግን ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ምን ያህል በተቀላጠፈ መልኩ መስጠት ይቻላል በሚለው  ላይ ትልቅ ስጋት አለኝ፡፡ ዘርፉን ስንመለከተው ሞባይል እያለ የኔትዎርክ ደካማ መሆን፤ አልፍ ሲልም መቆራረጥ የተለመደ የዘርፉ ችግር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በገንዘብ ዝውውሩ ላይ ትልቅ እንቅፋት ሊፈጥር ስለሚችል ተቋሙ አቅሙን በማጠናከር ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል፡፡( ሲራራ)

 

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top