Connect with us

#ምን_እናድርግ?!

#ምን_እናድርግ?!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

#ምን_እናድርግ?!

#ምን_እናድርግ?!

ለማሕበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚ ወገናችን የቀረበ ጥያቄ

(በመሐመድ ካሳ እና በያሬድ ሹመቴ)

በየቦታው ጦርነት፣ ግድያ፣ መፈናቀል፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ሰው ሰራሽ ረሃብ፣ በሽታ፣ የእሳት ቃጠሎ፣ አረ ስንቱ ይነገራል። ህዝባችን በዘመኑ ሁሉ ያያቸው መከራዎች ተባዝተው፣ ተደቅነውበት ፈተናውን ለመሻገር መከራውን እያየ ነው።

ብዙኃን ፖለቲከኞች ችግሩን ፖለቲካዊ እና መፍትሔውንም ፖለቲካዊ ሲያደርጉት፤ የኔ የሚሉትን “ሕዝብ” እንደየ ርዕዮተ ዓለማቸው ተሻምተው ሲያሰልፉት ይስተዋላል። ሊሳሳቱ ወይም ልክ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል! እዚህ ላይ ሃሳብ መስጠት በራሱ ፖለቲካ ይመስለናል።

ስለዚህም በአራቱም ማዕዘን ለሚገኝ ለዚህ ምስኪን ህዝብ እኛ ምን ማድረግ እንችል ይሆን? ስንል በተደጋጋሚ ተወያይተናል። ከዚህ ቀደም በቻልነው አቅም ሁሉ ቸር የሆነውን ህዝባችንን አደባባይ ወጥተን ለምነን ህዝባችንን ለመታደግ ጥረናል። የለመንነው ህዝብ አላሳፈረንም። በሚልዮኖች የሚቆጠር የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ለህዝባችን ለግሷል። እግረ መንገዱንም በተግባር ስለ ኢትዮጵያ ያለውን ቀና መልዕክት በግልጽ ቋንቋ (ልገሳው ላይ በመሳተፍ) አሳይቷል።

ይህንን ቸር ህዝብ በየጊዜው እየወጣን ‘ህዝባችንን እንታደግ የቻላችሁትን የአቅማችሁን ለግሱ!’ እያልን በብርቱ አድክመነዋል። ይህ ምስኪን ህዝብ ከልጆቹ ጉሮሮ እየነጠቀ  ለወገኖቹ አሌኝታ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቶ አኩርቶናል።

ዛሬ ግን ድጋሚ ለመጠየቅ አፈርን። ድጋሚ ወገናችንን ‘እንርዳ እንተባበር’ ለማለት ተቸገርን። ኑሮው መቃወሱን፤ ገቢው መንጠፉን፤ ህይወቱና ተስፋው በድንግዝግዝ ጨለማ ውስጥ መዋጡን እናስተውላለንና አሁንም በኩራት አደባባይ ወጥተን ለመለመን አቅም ተሳነን።

ምን እናድርግ?

ምን ይደረግ? ብለን መጀመሪያ የጠየቅነው ራሳችንን ነው። እኛ ጊዜና ጉልበታችንን ድጋሚ ለሕዝባችን እንስጥ ብለን መልሰን ተነቃቅተናል።

እናንተስ?

ይህንን ግዙፍ ሸክም በትንሽ በትንሹ እንኳን ለማገዝ ፍቃደኛ ናችሁ ወይ? ሁሉም ለጋሽ ዜጋ ያለበትን የግል ሸክም ስለምንረዳ ኪስን የማይጎዳ መጠነኛ ተሳትፎ በማድረግ፤ ነገር ግን  ብዙኃን የዚህ ቅዱስ አላማ ተባባሪ እንዲሆኑ የቅስቀሳው አካል በመሆን ልታግዙን፣ ወገናችንን በጋራ ልንደግፍ የምንችልበትን ትኩረት ትሰጡናላችሁ ወይ?

በዚህ ሁሉም በተቸገረበት ሰዓት ለአገራችን ተስፋ መሆን የሚችል ግዙፍ ንቅናቄ ለመፍጠር እያንዳንዱን ዜጋ ለበጎ ስራ እንዲሰለፍ ከጎናችን ትቆማላችሁ ወይ?

የገጠመንን አገራዊ መከራ በጋራ ለማለፍ ወሳኝ መፍትሔ ነው ብለን ያሰብነው ልገሳው ለማንም ሳይከብደው እንደ አቅሙ እንዲሳተፍ የሚያስችል የእርዳታ ማሰባሰብ ስራ መጀመር ነው። ለዚህ የሚቸግረን ብዙ ሕዝብ ጋር መልዕክታችን ማድረስ እና በተግባር ሚልዮኖችን ማሰለፍ እንችላለን ወይ? የሚል ጥያቄ ነው።

ስለዚህም ህዝቡን በማስተባበር ለበጎ ተግባር፣ የአቅሙን ሳይቸገር እርዳታ እንዲለግስ የሚያስችል ጥሪ ለማድረግ የማሕበራዊ ትሥስር ገጽ ቤተሰቦቻችን እንደ ቋሚ ስራ ቆጥሮ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ናችሁ ወይ?

ምላሻችሁን በቶሎ ከገለጻችሁልን። የክርስትና ዐቢይ ጾም እና የእስልምና ረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ ከሚያዝያ 18 እስከ ሚያዝያ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. (ከበአለ ህማማት ሰኞ እስከ አርብ/ጁምአ) ድረስ የሚቆይ የአምስት ቀናት የምግብና አልባሳት ልገሳ ለማካሔድ አስበናል።

ዝግጁ ከሆናችሁ በኛ ስም ፋንታ የእናንተን ስም እየተካችሁ በማሕበራዊ ትሥስር ገጾቻችሁ ላይ ፖስት እንድታደርጉ፤ ይህንንም መልዕክት እያጋራችሁ እና ዝግጁነታችሁን የሚገልጽ መልዕክት በመጻፍ ከወዲሁ ፍቃዳችሁን ትሰጡን ዘንድ ብታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

አዎ ምን እናድርግ?

#ምን_እናድርግ?

 

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top