Connect with us

የአጣዬና አካባቢው ጥቃት በተመለከተ የአማራ ክልል መግለጫ

የአጣዬና አካባቢው ጥቃት በተመለከተ የአማራ ክልል መግለጫ
አሚኮ

ዜና

የአጣዬና አካባቢው ጥቃት በተመለከተ የአማራ ክልል መግለጫ

የአጣዬና አካባቢው ጥቃት በተመለከተ የአማራ ክልል መግለጫ

በአማራ ክልል የተፈፀመውን ጥቃት ለማስቆም ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል መግባቱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።

ትናንትና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን አጣዬ ከተማን የጸጥታ ኃይሉ መቆጣጠሩንም የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኀንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ  ሲሳይ ዳምጤ አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰ ጥቃት ንጹሐን ተገድለዋል፣ አካል ጎድሏል፣ ሀብትና ንብረት ወድሟል።

ዜጎች ቀያቸውን ለቀው ራሳቸውን ለማዳን ሸሽተዋል። በአካባቢው ከአሁን በፊት የተከሰተው ችግር በመረጋጋት ላይ ባለበት ወቅት ነው ችግሩ  በድጋሚ ነው የተነሳው። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም ጉዳዩን እየተከታተለ ሲዘገብ መቆዬቱ ይታዎሳል።

በአማራ ክልል ስለተፈጠረው የጸጥታ ችግር የክልሉ የሰላምና ሕዝብ ደኀንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢ መጠነ ሰፊ የሆነ ችግር ተፈጥሯል ብለዋል። በአካባቢው ከአሁን በፊት ሲከሰቱ የነበሩ ችግሮችን ከሕዝብ ጋር በመሆን ሲፈቱ እንደቆዬ ያመላከቱት ኃላፊው ችግሩ በድጋሜ ማገርሸቱን ነው የተናገሩት።

ትናንት በአጣዬና በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ጽንፈኛ ቡድን ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱንም አመላክተዋል። በደረሰው ጉዳትም ንጹሐን ሞተዋል፣ አካል ጎድሏል፣ የመንግሥትና የሕዝብ  ሀብትና ንብረትም ወድሟል ነው ያሉት።

በአጣዬ በማረሚያ ቤት የነበሩ ታራሚዎች ከእስር እንዲወጡ ተደርጓል።

ከአጣዬ ባለፈ በካራቆሬ፣ በማጀቴ፣ በአንፆኪያ፣ በመኮይና በሸዋሮቢት ሕዝቡ በውጥረት ውስጥ ነው ያለው ብለዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ያለው ችግር እየከፋ የመጣና ሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንቶች ጭምር በግፍ የተገደሉበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የኦነግ ሸኔ  ቡድን በሸዋሮቢት የሚገኙ ታራሚዎችን ለማስለቀቅ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊው በአካባቢው አሁንም የተኩስ ልውውጥ መኖሩን ነው የተናገሩት።

የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአካባቢው የጸጥታ መዋቅርና የፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅር ከፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። አካባቢውን ለማረጋጋት እና አጥፊውን ቡድን ለሕግ ለማቅረብ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል ወደ ስፍራው መግባቱንም ተናግረዋል። የአካባቢውን ሚሊሻ በማደራጀት ከሌላው የጸጥታ ኃይል ጋር እንዲገባ እያደርግን ነውም ብለዋል። ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን አጣዬ ከተማን የጸጥታ ኃይሉ መቆጣጠሩን አስታውቀዋል።

በሸዋሮቢት ያለውን ችግር ለመቅረፍ የመከላከያ ሠራዊት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

የኦነግ ሸኔ ጽንፈኛ ቡድን የአማራን ሕዝብና መንግሥት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ እየሠራ መሆኑንም አመላክተዋል። ችግሩን የፈጠሩ፣ ያደራጁና የመሩ ለሕግ መቅረብ አለባቸው፤ ጽንፈኛውን ቡድን ከሕዝብ እየነጠሉ ለሕግ ማቅረብ ይገባልም ብለዋል።

በሌላ በኩል በጭልጋ አካባቢም የታጠቁ ኃይሎች በመከላከያ ሠራዊትና በአማራ ልዩ ኃይል ላይ ጥቃት በመፈፀም  ችግር  መፍጠራቸውን የተናገሩት  ኃላፊው የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ መዋቅር ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ የሚሰጡትን አጀንዳዎች በሰከነ መንገድ በማዬት ከመንግሥት ጎን በመቆም ችግሮችን በጋራ እንዲፈታም ጥሪ አቅርበዋል።

#አሚኮ

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top