Connect with us

ፖለቲከኞቻችን፣ዲያስፖራው፣ ሚዲያዎቻችን  እና ማኀበረሰብ አንቂዎቻችን ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በእሳት የሚፈተኑበት ወቅት ነው፤

ፖለቲከኞቻችን፣ዲያስፖራው፣ ሚዲያዎቻችን እና ማኀበረሰብ አንቂዎቻችን ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በእሳት የሚፈተኑበት ወቅት ነው፤ እናስተውል ታሪክ ሰሪ እንጂ የታሪክ ተወቃሽ አንሁን
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ፖለቲከኞቻችን፣ዲያስፖራው፣ ሚዲያዎቻችን  እና ማኀበረሰብ አንቂዎቻችን ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በእሳት የሚፈተኑበት ወቅት ነው፤

ፖለቲከኞቻችን፣ዲያስፖራው፣ ሚዲያዎቻችን  እና ማኀበረሰብ አንቂዎቻችን ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በእሳት የሚፈተኑበት ወቅት ነው፤ እናስተውል ታሪክ ሰሪ እንጂ የታሪክ ተወቃሽ አንሁን

(ሻምበል ጥላሁን)

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለውጤት ተጠናቋል።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ባወጣችው መግለጫ  ብሔራዊ ጥቅሟን የሚጎዳ ስምምነት ውስጥ እንደማትገባ በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂሚኒስቴር በኩል ትናንት ይፋ አድርጋለች።

ኢትዮጵያ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የሆነውን፣ የአሁንና የወደፊቱን የአባይን ውሃ የመጠቀም መብቷን የሚገድብ ማንኛውንም ስምምነት አትፈርምም ሲል የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአገሪቱን አቋም በማያሻማ ሁኔታ ገልጿል።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በታዛቢነት በተገኙበት በተካሄደው ድርድር ላይ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተው የሦስቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት አሸማጋይነት ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ ድርድሩ ላይ ደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ በታዛቢነት እንዲቀጥሉ ተስማምታለች።

ይሁን እንጂ ሱዳንና ግብጽ ግን በድርደሩ ላይ የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ ከአፍሪካ ሕብረት እኩል ሚና እንዲኖራቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም ፤ ጥያቄው በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንዳላገኘ በወጣው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ ይህንን ሐሳብ ውድቅ ያደረገቸው የአፍሪካ ሕብረትን ሚና የሚያሳንስ ነው በሚል እንደሆነ ሚኒስቴሩ ጠቁሞ፤ ነገር ግን ታዛቢዎቹ የድርድሩን ሂደት እንዲደግፉ ሦስቱም አገራት በጋራ ሲስማሙ ብቻ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ተስማምታለች።

በውይይቱ ማብቂያ ላይ በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በአፍሪካ ሕብረት የቀረበውን ረቂቅ መግለጫ ኢትዮጵያ መቀበሏን ያስረዳው መግለጫው፤ ግብጽና ሱዳን ግን ረቂቅ መግለጫውን ባለመቀበል ሁለቱ አገራት ድርድሩ አውንታዊ ውጤት እንዳይኖረው እንቅፋት ሆነዋል ሲል ወቅሷል።

ግብጽና ሱዳንም በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ያለ ውጤት መጠናቀቁን በመግለጽ ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርገዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ሁለቱ አገራት ለድርድሩ የቀረበውን ሐሳብ ኢትዮጵያ ሳትቀበለው አንደቀረች መግለጻቸውን ዘግቧል።

“ይህ የኢትዮጵያ አቋም በቅን ልቦና ለመደራደር ፖለቲካዊ ፈቃደኝነቱ እንደሌላት በድጋሚ የሚያሳይ ነው” ሲል የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የሱዳን መስኖና የውሃ ሀብት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ደግሞ “ይህ የኢትዮጵያ ግትር አቋም ሱዳን ሕዝቧንና ደኅንነቷን ለመጠበቅ ሌሎች አማራጮችን እንድትፈልግ ያደርጋታል” ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በድርድሩ ዙሪያ ትናንት ማታ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ ለድርድሩ ስኬታማ አለመሆን ሱዳንና ግብጽ የያዙት ግትር አቋምን እንደምክንያት አቅርቧል።

ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫ እንደሚያትተው፤በግድቡ አሞላል፣ ውሃ አያያዝ እንዲሁም አለቃቀቅን በተመለከተ ከስምምነት ለመድረስ ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደሆነች ጠቅሷል።

ይሁን እንጂ ሁለቱ አገራት ድርድሩ የኢትዮጵያን የውሃ ድርሻ የሚገድብና አለን የሚሉትን የውሃ ክፍፍል የሚያፀና አስገዳጅ ስምምነት ካልተደረሰ የሚል አቋም በመያዛቸው ከውጤት አለመደረሱን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫ ጨምሮ እንዳመለከተው፤ ግብጽና ሱዳን በተደጋጋሚ ሲሉት የነበረውን አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረግ የግድቡ ሙሌት መከናወን የለበትም የሚለው ሃሳብ የሕግ መሠረት የሌለውና ኢትዮጵያ የላትን የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል ውድቅ አድርጎታል።

በዚህም መሠረት የግድቡ ሁለተኛ ዓመት የውሃ ሙሌት ከዚህ በፊት በተደረሰው የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በተያዘለት የጊዜ ሠሌዳ መሰረት ይካሄዳል ሲል የኢትዮጵያን አቋም  መግለጫው በድጋሚ ይፋ አድርጓል።

የአባይ ወንዝን 85 በመቶ ውሃ የምታመነጨው ኢትዮጵያ፣ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት አሳሪና ሕጋዊ ስምምነት እንድትፈርም እየወተወቱ ያሉት ሱዳንና ግብጽ ባቀረቡት ሐሳብ ላይ ኢትዮጵያ ሳትስማማ ቆይታለች።

የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ፣ ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግድብ ሳቢያ አገራቸው በምታገኘው የውሃ መጠን ላይ ተጽእኖ የሚፈጠር ከሆነ ‘የከፋ አካባቢያዊ ችግር’ ይፈጠራል ሲሉ አስጠነቅቀው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ “ማንም ከግብጽ ውሃ ላይ አንዲት ጠብታ መውሰድ አይችልም፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሚታሰበው በላይ አደገኛ አለመረጋጋት በአካባቢው ይፈጠራል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን የምትጠቀመው ውሃውን በግዛቷ ውስጥ ለሚያስቀሩ ፕሮጀክቶች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ብታስረዳም ሱዳን በተለይም  ደግሞ ግብጽ የትኛውም አይነት በውሃው ላይ የሚከናወን ሥራ የሁለቱን ሀገራት ይሁንታ ሳያገኝ መካሄድ እንደሌለበት ሲገልጹ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር፣ ኢንጂነር  ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማታራዝመውና ለዚህም የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ተናግረዋል።

በአሜሪካ ለተራዘመ ጊዜ ሱዳን ላይ ተጥሎ የቆየውን ማዕቀብ ካዝናዋን አሟጣ ካሳ በመክፈል የተገላገለችው ሱዳን ከባላንጣዋ አሜሪካ ጋር የጫጉላ ሽርሽር ላይ ናት።

ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በስልክ የተወያዩት የአሜሪካው ውጩ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን፣ አሜሪካ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ አለመግባበት በውይይትና ሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸው የሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በአሜሪካና በግብጽ ወቅታዊ ወዳጅነትና አይዞሽ ባይነት የልብ ልብ የተሰማት ሱዳንም ኢትዮጵያን የመተነኳኮስ፣ የማስፈራራትና የማሸበር ሥራዋን አጠናክራ ቀጥላለች።

የሱዳን መስኖና የውሃ ሀብት ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ ደግሞ “ይህ የኢትዮጵያ ግትር አቋም ሱዳን ሕዝቧንና ደኅንነቷን ለመጠበቅ ሌሎች አማራጮችን እንድትፈልግ ያደርጋታል” ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

ግጥምጥሞሽ ይሁን ታቅዶበት ድርድሩ ያለስምምነት በተጠናቀቀበት ትናንት ምሽት አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ፈጽሟል የሚል ሪፖርት አውጥታለች።

ሀገር በማፍረስ የዳበረ ልምድ ያላቸው እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አንዳንድ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት፣ ሳውዲ አረቢያና ሌሎችም  ሀገራት ኢትዮጵያን እንደ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመንና ማይናማር ለመበታተን ቆርጠው የተነሱ መስለዋል።

ፖለቲከኞቻችን፣ ዲያስፖራው፣ ሚዲያዎቻችን እና ማኀበረሰብ አንቂዎቻችን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል በእሳት የምንፈተንበት ወቅት ላይ ነን።

ፖለቲከኞቻችን የውስጥ ችግሮቻችንን ከእልህና ከመበሻሸቅ ፖለቲካ ወጥተን በሰከነ መነገድ እንፍታ።

በተደጋጋሚ ጊዜ በተለይም በለውጡ ወቅት  ግጭትና ዘርን መሰረት ያደረገ ግጭት የሚከሰትባቸው የኦሮሚያና የአማራ ክልል አመራሮች ችግሮቻቸውን ለመፍታት ለውይይት መቀመጣቸው በጎ ጅምር ነው።

በሁለቱም ክልሎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ተከትሎ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለዉን ሞትና መፈናቀል በፍጥነት ማስቆም፣ የግጭቱ ጠንሳሾች እና ተዋናዮች ላይ አስፈላጊዉን እርምጃ መዉሰድ፣ በተከሰቱ ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸዉ ወገኖች ፍትሕ እንዲያገኙ እና ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀረቡ ማድረግ፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው በፍጥነት መመለስና ማቋቋም የሚሉ ሐሳቦች ለውይይት ለመቀመጥ የተስማሙባቸው ነጥቦች መሆናቸው የውይይቱን ፍሪያማነት እንድንጓጓ አድርጓል።

ለውይይቱ ከተቀመጣችሁ ተወያዮች ለመወያየት በተስማማችሁባቸው ነጥቦች ላይ ያለ ቅድመ ሁኔታ በመስማማት አሳውቁን።

ስምምነታችሁ ለውይይት ጊዜ የሚወስድ ከሆነም ፌዴራል መንግሥቱ ገለልተኛ ሆኖ የሚያጣራ ከሁለቱ ክልል ውጪ ያለ አካል አዋቅሮ የችግሩን ምንጭ ያጣራ።

ችግሩ በተከሰተባቸውና የደህንነት ሥጋት ባለባቸው የሀገሪቷ አካባቢዎች ከሁሉም ክልሎች የተወጣጣ ልዩ ሃይል ይሰማራ መከላከያው የሀገሪቷን ድንበርን በንቃት በመጠበቅ ይትጋ።

ፖለቲከኞቻችን፣ ዲያስፖራው፣ ሚዲያዎቻችን እና ማኀበረሰብ አንቂዎቻችን አሁን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በእሳት የሚፈተኑበት ወቅት ላይ ነን።

በሁለቱም በኩል ያላችሁ “ማኀበረሰብ አንቂዎቻችን” ሚዲያዎችና ዲያስፖራው ችግሮቹ በሰላም እንዲፈቱ በመትጋት እንጂ ችግሮቹ እንዲባባሱ ነዳጅ በማርከፍከፍ አንፋጠን።

አሁን ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በእሳት የሚፈተኑበት ወቅት ነው፤ ታሪክ ሰሪ እንጂ የታሪክ ተወቃሽ አንሁን።

(ለዚህ ጽሑፍ  የቢቢሲ፣ ሮይተርስ ያወጡትን ዘገባ ተጠቅሚያለሁ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top