ደንቆሮ ጫካ አፋፍ፤
ሁሉ ያለበት “አለባቸው” ዋሻ
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የቦረና ሳይንት ወረሂመኖ ብሔራዊ ፓርክን እያስጎበኘን ነው፡፡ ዛሬ ከደንቆሮ ጫካ አፋፍ የሚገኘውን ሰፊ ዋሻ አብረን እንግባበት ብሎ ወደ ውስጥ ይወስደናል፡፡ ስለ አለባቸው ስምና ዝና በስሙ ከተጠራው ዋሻ ጋር እያዛመደ ይተርክለናል፤ መልካም ንባብ)
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
ደንቆሮ ጫካ ከስር ተዘርግቷል፡፡ እኔ አፋፉ ላይ ነኝ፡፡ እዚህ ለመድረስ የመጣሁት መንገድ በየጎዳናው ሊጠለኝ ያሰበ የተፈጥሮን ውበት ተጠንቅቄ ነው፡፡ የዛፉ ሽበት እንደ ኮረዳ ጉንጭ ዳብሱኝ ሳሙኝ ይላል፡፡ የአስታ ዛፍ የእርጅና ጢም ተንዠርጎ የተዘናፈለ ጸጉር ይመስል በየገደሉ ከበቀለው አስታ ቅርንጫፍ ላይ ሆኖ መንገድ ያስቀራል፡፡ እያለፍኩ እዚህ ደረስኩ፡፡
ያለሁበት እንግዳ አይሁንባችሁ፡፡ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ነኝ፡፡ ስሙን ቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ይሉታል፡፡ ሳምንት ነግሬያችኋለሁ ረዥሙ የፓርክ ስም፤ ስለ ፓርኩ ስጽፍ ቤተ አማሐራ ብሔራዊ ፓርክ ይባል ብለው የነገሩኝ አሉ፤ የነገሩኝን መንገር እንጂ ሌላ ስም መቀየር አልችልም፡፡ እውነት ለማናገር ግን ከታሪክም ከእውነታም ቤተ አማሀራ ውብ ስም ነው፡፡
ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙት ቦረና፣ ሳይንትና መሀል ሳይንት ወረዳዎች ያካልሉታል፡፡ የታላላቅ አድባራት ስምና ክብር ከቦታል፡፡ አትሮኖስና ተድባበ ማርያም ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ሥሬ የተዘረጋው ደን ቀድሞ ምን ይዋብ ይባል እንደነበር አንብቤያለሁ፣ ሰምቻለሁ፡፡ እዚህ የደረሰ እውነትም ምን ይዋብ ማለቱ አይቀርም፡፡ ደንቆሮ ጫካ የሚለው ስሙ ግን ገኗል፡፡
ወደ ዋሻው አፍ ተጠጋን፤ ወዲያው ጎረሰን፡፡ ተከታትለን ዋሻው ሆድ ውስጥ ገባን፡፡ አንዳንድ ቦታ ዝቅ ደግሞ መልሶ ሌላው ጋ ከፍ ይላል፡፡ ጎንበስ ቀና እያለን ወደ ውስጥ ገባን፡፡ ሰፊ ነው፡፡ በደርግና ኢህአዴግ ጦርነት ለኢህዴን ታጋዮች ብዙ ውለታ የዋለ ዋሻ ነው፡፡ ከዚያም እስር ቤት አደረጉት፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ይዞ ኖሯል፡፡
አለባቸው ዋሻ፤ ብዙ ነገር አለበት፡፡ ታሪኩ ግን ከአለባቸው ይቆራኛል፡፡ ሰውዬው አማጺ ነው፡፡ እንቢኝ ብሎ ሸፈተ፡፡ እዚህ ገባ፡፡ በዋሻው አፍ እገባለሁ የሚል ከአነጣጠረው ጥይት ስለሚገባ ስሙን የዋሻ መጠሪያው አድርጎ በክብር ኖረ፡፡
ወደ ዋሻው ሌላ ክፍል መሩኝ፡፡ የአለባቸው ክፍል የተባለች አንዲት ጠባብ ስቱዲዮ የምታክል ሌላ የዋሻ ክፍል ዋሻ ውስጥ አለች፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ያኮረፈ እንደሚሸሸግበት ለማብሰልና ለብርሃን የተለኮሰው እሳት ያጠቆረው ጥቀርሻ ይናገራል፡፡
ሌት የዱር አራዊቱ ማሳለፊያ ነው፡፡ የብሔራዊ ፓርኩ ተፈጥሯዊ መስህቦች ከሚባሉት ዋናው አለባቸው ዋሻ፡፡ የቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሔራዊ ፓርክ ከ25 በላይ ዋሻዎች ይገኙበታል፡፡ ይላስ እና አለባቸው ዋሻዎች ስማቸው ጎልቶ ይነሳል፡፡ ወደ ውቡ ፓርክ አናት አብረን እንወጣለን፡፡ ከፍታው ላይ እናድራለን፡፡ ከጅብራው አየር እንጋራለን፡፡ ቁልቁል የሳይንትን ምድር ተዝርግቶ በዓይናችን እንጋልብበታለን፡፡ ደንቆሮ ወንዝ ሲንፏለል እናደምጠዋለን፡፡ ገና አልተመለስንም፡፡