ዋግኽምራ ለምን ሄድን ?!
( አምስት ደቂቃዎትን ይስጡኝ)
ነገሩ እንዲህ ነው።
የዛሬ አንድ ዓመት ከአስር ወር ገደማ ።
ምሳ በልተን ሻይ ቡና እያልን ነበር ፡ እኛ ሶስት ጓደኛሞች። እንደ አጋጣሚ በጫጫታው መሃል በቴሌቪዥን ከሚተላለፈው የረባና ያልረባ ዜና ውስጥ አንዱ ዓይናችን ላይ ቀረ።
አረንጓዴ ቀለም ( ጎመን መልክና በዛጎል ያጌጠ ) አዳፋ ልብስ የለበሱ ህፃናት ተማሪዎች ከባሕር ዛፍና ግራር ቅጠሎች እንደነገሩ በተከለለ የዳስ ትምህርት ቤት ውስጥ በድንጋይ ላይ ተኮልኩለው ሩብ በምታክል ሰሌዳ (ያቺውም የተበሳሳች) ከመምህሩ ጠመኔ የሚጫረውን ፅሁፍ ይለቅማሉ።
ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳዳር ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው ቦታው።
ዘጋቢ ጋዜጠኛው ግራ መጋባቱ፣ የህፃናት ተማሪዎቹ የቧዘዘ እይታ እና የዳሱ ነገረ ሁኔታ የሆነ ቅዝዝ የሚያደርግ ስሜት ነበረው።
እኛንም የተሰማን ይኸው ነበር።
የህፃናት ተማሪዎቿን ቢያንስ በክፍል ውስጥ የማታስተምር አገር እንዴት ኖረችን የሚለው መብሰልሰል የጋራ ስሜታችን መገለጫ ሆነ።
መንግስትን፣ ፖለቲከኛውን፣ ምሁሩን፣ ባለሀብቱን፣ ዲያስፖራውን፣ በጥቅሉ ራሳችንን ጨምረን ሁሉንም በዚያች ቅፅበት ወቀስን ፣ ረገምን።
በነጋታው የሆነው ግን ወደራሳችን እንድንመለከት አስገደደን።
የዚሁ የዳስና ዛፍ ጥላ ስር ትምህርት ቤትን ዘገባ ያየው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ትምህርት ቤት ገንብቶ ለማስረከብ ቃል መግባቱን የተመለከተ ዜና ተላለፈ።
አሁን ሶስታችን ጓደኛሞች በቀጭን ገመድ ላይ እንደመራመድ የሚከብድ የሚመስል ግን ኃይሌ እንደሚለው ይቻላል በሚል መንፈስ አንድ ሃሳብ ወጠንን።
እስኪ ከየመስሪያ ቤቱ የወዳደቁ ቁሳቁሶችን አሰባስበን ወደ ፋይናንስ እንቀይርና ምቹ የመማሪያ ክፍሎችን ለማስገንባት እንሞክር ተባባልን።
ከዚህ የተሻለ አማራጭ ለጊዜው አልመጣልንም።
ኃይሌ ሀብትና ቀና ልብ ነበረውና ከኪሱ አውጥቶ ሊገነባ ወሰነ። እኛ ከዕለት ጉርሳችን የዘለለ ጥሪት የለንም።
ጎፈንድሚ ለማስከፈት ዲያስፖራ ሁነኛ ወዳጅ በአጠገባችን የለም ፣ ባለሃብቶችን እየዞርን እንዳንለምን በበነነ በተነነው ጥያቄ በዝቶባቸዋል ፣ በቴሌቶን እንዳንሞክረው እሱም በኛ አቅም ቶሎ የሚፈፀም አልነበረም።
በተከታታይ ቀናት በሻይ ቡና ወሬያችን እየተጨቃጨቅንም፣ እየተወያየንም ፣ እርስ በእርስ እየተበረታታንም ይዘነው ልንሞክረው የምንችለው ይህ ” ከተጣሉ ቁሳቁሶች ” ፋይናንስ ማግኘት የሚለው ሃሳብ ነበር።
እናም ” ምቹ ለህፃናት ተማሪዎች ” ብለን ሰየምነው።
ሃሳባችንን ፃፍነው።
መነሻና መድረሻችንን አሰፈርነው።
ክፉና ደግ ብለን ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶችን ለይተን ለመተየብ ሞከርን።
በአጭር ሳምንታት ውስጥ ያነሳሳንን፣ ያሰብነውንና ያቀድነውን ትልም የያዘ ሰነድ አዘጋጀን።
ከዚያስ?
ለመጀመር እንቅስቃሴ አደረግን።
ነገር ግን የመጀመሪያው ፈተና እንደ ቋጥኝ ተደነቀረ።
መስሪያ ቤቶች የንብረት ማስወገጃ ስርዓታቸውና ቢሮክራሲያቸው ቆሺት የሚልጥ ነበር።
መላ ዘየድን።
ሃሳባችንን ማበረታታት ቢፈልጉም ግለሰቦች በመሆናችን የመስሪያ ቤታቸውን የተጣለ ቁሳቁስ ለመስጠት እንደሚፈሩ ተረዳን።
ይህን ጊዜ አብሮን የሚሰራ ተቋም የግድ ሆነ።
በዚህ መኃል የአንዱ ጓደኛችን ከአስር ዓመት በላይ ትምህርትና ጤና እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች የምግባረ ሰናይ ስራዎችን የሚከውን ድርጅት ተቀጣሪ በመሆኑ በዚህ ድርጅት ጥላ ስር ሃሳባችን እንዲተገበር ልክ እንደእናት የፕሮጀክታችን ጥላና ከለላ እንዲሆን አሰብን።
ይህም ሌላ ሳንካ ይዞ መጣ።
ይህ ግሪን ኢኒሺዬቲቭ ኢትዮጵያ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ፈቃድ የተሰጠው በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ብቻ ነበር።
የድርጅቱ ቦርድ ባደረገው መተባበር በአማራ ክልልም መስራት የሚችልበትን ፈቃድ እንዲወስድ ተደረገ።
አሁን የኛ የሶስት ጓደኛሞች ምኞት ተቋማዊ ጥላ ስር ሆነ።
በየቀኑ የሚያጋጥሙን ችግሮች ብዙ ነበሩ። መጀመሪያ ግለሰቦች በመሆናችን ቁሳቁስ መስጠት እንቸገራለን ያሉ መስሪያ ቤቶች ቀጥለው ደግሞ ከትምህርት ቢሮ የድጋፍ ደብዳቤ ቢኖራችሁ አሉን።
ከዚያ ጉዳዩን በጥልቀት ለመረዳትና ለማስረዳት ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ባሕር ዳር ሄደን ምኞታችንን አስረዳን።
እርግጥ ነው እኔ ከጓደኞቼ አርቲስት ቶማስ በየነና ከጤና ባለሙያው ፋሲል አስማማው የተሻለ ስለዳስ ትምህርት ቤት ጉዳይ መረጃ ነበረኝ። ይሁንና በጋዜጠኝነቴ እግሬ ካልረገጣቸው አካባቢዎች አንዱ ዋግኽምራ ነው። ቶማስም የአዲስ አበባ ልጅ ነው ፣ ፋሲል ደግሞ ውልደቱም ዕድገቱም ነገሌ ቦረና ነውና እንኳን ስፍራውን ሊያውቁ የዳስና የዛፍ ጥላ ስር መማሪያዎች ስለመኖራቸው ከዚያ በፊት ሰምተው አያውቁም።
ታዲያ ባሕር ዳር የትምህርት ቢሮ ሰዎች የዋግኽምራው ሲገርመን በሰሜን ጎንደርም ብዙ የዳስና የዛፍ ጥላ ስር ተማሪዎች እልፍ መሆናቸውን ነገሩን። ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ሁኔታና ዓይነት እንዲሁም የሚገኙበትን ዝርዝር ስፍራ ነግረው በማንኛውም ሁኔታ አይዟችሁ ሊሉን ቃል ገብተው ሸኙን።
የድጋፍ ደብዳቤም ሰጡን።
እኛ ይህንን ሁሉ ግራንጃ ስንጋፈጥ ኃይሌ የሆነ ግንባታ ምዕራፍ ደርሶ ነበር። ይህንን መስማታችን እንደ ማነቃቂያ ይሆነን ነበር።
ቀጠልን።
የፕሮጀክታችንን ጥራዝ ተከፋፍለን በየመስሪያ ቤቱ አደረስን።
በቅድሚያ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ኤምባሲዎች፣ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ፣ ኤጄንሲዎች ሰጠን።
የሰጠናቸውን በአካል እያስረዳን፣ በስልክም እየጨቀጨቅን የሆነ መልካም ትብብሮች መስማት ጀምረን እያለ ልባችንንም ወኔያችንንም ቀጥ የሚያደርግ መርዶ መጣ።
አዎ ፡ መርግ ተጫነን።
ኮሮና ኢትዮጵያ ገባ።
ስራዎች ቆሙ ፣ የቢሮ እንቅስቃሴዎች ተገቱ።
በተለይ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፊል ስራዎችን ዘጉ። ይህ ወገባችንን የተጫነ ሸክም ሆነ።
ወዲህ ለራሳችን መንቀሳቀሱን ፈራን፣
ወዲያም በየቢሮዎች የማይገቡ ሰዎች በመኖራቸው የኛን መጠየቂያ ደብዳቤዎች በ “ይቆይ ” ጠረጴዛና ሼልፎች ላይ የሚያስቀምጡት በዙ።
በዚህ መኃል ፋሲልና የግሪን ኢኒሺየቲቭ ባልደረቦች በድፍረት ብዙ ተራወጡ።
እኔና ቶማስ ፍርሃትንንና ንዴታችንን ለመወጣት በሚመስል መልኩ ኮሮና ላይ ዘመትን።
ቀን ሄደ።
ቀን መጣ።
የኃይሌ ገብረ ሥላሴ መማሪያ ክፍሎች ግንባታ ተጠናቀው ተመረቁ።
ከፍና ዝቅ ቢልም ተስፋ ግን ይታየን ነበር።
በራቸውን እንዳንረግጥ የዘጉ ቢኖሩም ከእኛ በላይ ምኞታችን የተጋባባቸውም ብዙ ነበሩ።
አንድ ፣
ሁለት፣
ሶስት —-
እያሉ የሚፈቅዱልን ብቅ ብቅ አሉ።
አሮጌና የተጣሉ ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮች፣ የማባዣናኮፒ ማሽኖች፣ የመኪና ጎማዎች፣ ሼልፎች፣ ወዘተዎችን እያጠራቀሙና በየመጋዘኑ ከተከዘኑት እየዘገኑ ሰጡን።
ብዙ ናቸው ሰጪዎቻችን።
ግን በተለይ በአስፈሪው የኮሮና ወረርሺኝ ወቅት አይዟችሁ እያሉ ከቁሳቁስ ማሰባሰብና መስጠት በተሻገረ ትብብር ድጋፍ ያሳዩን የግብርና ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር ባልደረቦችና ኃላፊዎች የምር ብርታት ሆነውናል።
ቁሳቁሶችን ሰብስበን እያከማቸን ፣ እሱንም በጨረታ እየሸጥን ፣ በየጠረጴዛው አስቀምጠው ” እሺ ወይም እምቢ ” የሚል ቁርጠኛ መልስ ያልሰጡንን እየተከታተልን ነጎድን።
ውጥናችንን በትክክል ከጀመርን ልክ በ18ኛ ወሩ የሰበሰብነው የወዳደቀ ቁሳቁስ ተሸጦ ያገኘነው ገንዘብ ሁለት ዘመናዊ መማሪያ ህንፃዎችን በሁለት የተለያዩ ስፍራዎች እንደሚያስገነባልን አረጋገጥን።
አሁን ገንዘብ እጃችን ላይ ገባ።
ያውም በክልሉ ትምህርት ቢሮ ስታንዳርድ ሁለት ምቹ መማሪያዎችን ማስገንባት የሚችል ፋይናንስ አገኘን።
ዲዛይኑን አሻሻልን።
አራት ምቹ መማሪያ ክፍሎች ፣ አንድ የመምህራን ቢሮ እና አንድ ቤተ መፃህፍት ያለው ህንፃ እንዲሆን ወሰንን። የዚህም 3D ዲዛይን በነፃ ተባባሪ ወዳጆቻችን ተዘጋጀልን።
ይህን ጊዜ ወሰንን።
ፋሲልንና ሌሎች ባለሙያዎችን ወደ ዋግኽምራ ሰቆጣ ላክን።
የዛፍ ጥላ ስር ትምህርት ቤቶቹ ተለዩ።
በዞኑ ሙሉ ሳይሆን ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ብቻ ካሉ 52 ትምህርት ቤቶች 43ቱ የችግሩ ተጠቂዎች ናቸው።
ከእነዚህ መኃል አባ ዮሐንስ እንዲሁም ወለህ የሚባሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የዛፍ ጥላ ስር መማሪያ ክፍሎች እንድንገነባ በዞኑና በወረዳው ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች ተወሰነልን።
ፋሲል ደርሶ መጣ።
አሁን ማስጀመር እንደምንችል አረጋገጥን።
እኔ ፣ ቶማስ ፣ ፋሲልና የግሪን ኢኒሺየቲቭ ኢትዮጵያ ባልደረቦች ሆነን ወደ ዋግኽምራ ተጓዥ ለመሆን ተዘጋጀን።
ከጉዟችን ጥቂት ቀናት በፊት ግን ወደ ቦሌ አቀናን።
ኃይሌን አገኘነው።
” ስላነሳሳኸን እናመሰግንሃለን ፣ አሁን የወዳደቁ ቁሳቁሶችን አሰባስበን ባገኘነው ገንዘብ ምቹ የተማሪዎች መማሪያዎችን አንተ እንዳደረከውን ልናስገነባ ልንሄድ ነው ” አልነው።
ከስፖርትና ቢዝነስ ውጭ የኛን የትምህርት ቤት ግንባታ መነሳሳት እፈጥራለሁ የሚል ግምት አልነበረውምና መገረሙ አልቀረም።
” አስጀምራችሁ ስትመለሱ እኔም በየድርጅቶቼ የሚገኙ አገልግሎት የማይሰጡ ቁሳቁሶችን እሰጣችኋለሁ ፡ በርቱ።” አለን።
የኃይሌን የሞራል ስንቅ ታጥቀን ወደ ዋግኽምራ 720 ኪሎ ሜትሮችን ስንጓዝ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አብሮን ተጓዘ። ምክንያቱም አጀንዳው የእሱ ነበረና።
አስገራሚውን የሰሜን መልክዓምድር እየተገረምንበት ፣ እየፈራንበትና በመሰረተ ልማቱ አለመሟላት እያዘንንለት ደረስን።
የምር ለመናገር ከሰቆጣ ከተማ በሃምሳ ኪሎ ሜትር ራዲየስ የሚገኙትና ከአርባ ዓመታት በላይ ( 1970 ዓም ጀምሮ ) ትውልድ በማስተማር ላይ የሚገኙት የ አባ ዮሐንስና የወለህ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በዛፍ ጥላ ስር ካስተማሩ ሌሎቹን ራቅ ያሉትን ደግሞ አስቧቸው።
እኔና ጓደኞቼ የተሰማንን ጥልቅ ስሜት እንተወው።
የተማሪዎቹ ምኞት ላጋራችሁ።
እያወራናቸው አንዱ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እንዲህ አለን።
” ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለን፣ ነፋሱን፣ አቧራውን፣ ዝናቡን ችለን እየተማርን ነው። ከፊሎቹ በክፍል ሲማሩ እኛ ግን የሰውን ፣ የወፍና አሞራውን እንቅስቃሴ እያየን ቀልባችን እየተሰረቀ መምህሮቹ የሚያስተምሩትን ለማዳመጥ እንቸገራለን።” አለን። የእናንተ ልጅ ፣ ወንድም ወይም እህት እንዲህ ቢላችሁ ምን ይሰማችኋል?
ሌላኛው በፎቶው የምታዩት ህፃን ፓይለት መሆን ይመኛል ፣ ይህች ባለጎመኔ ልብሷ ውብ ደግሞ ሀኪም የመሆን ህልም አላት።
ከልጆቹ ድንጋይ ላይ በዛፍ ጥላ ስር ተቀምጦ መማር በላይ መምህራኖቹ በቁራጭና በተበሳሳ ሰሌዳ መሬት ላይ አጎንብሰው ሲያስተምሩ ይውላሉ። የሚገርመው የልጆቹን ህይወት የመቀየር ፍላጎታቸው ነው።
” ከዛሬው የኔ ማጎንበስ የልጆቹ የነገ ህይወት ቀና ማለት ይበልጣል። ዛሬ የወዳደቁ ቁሳቁሶች ሰብስባችሁና ሽጣችሁ ባጠራቀማችሁት ገንዘብ ለእነዚህ ልጆች ምቹ ክፍሎች ልትገነቡ ስትመጡ የፈጠራችሁልን መነሳሳት ትልቅ ነው። እኔና ባልደረቦቼ ከወዳደቁ ቁሳቁሶች አገር የሚቀይር ፈጠራ የሚያፈልቁ ልጆች ከዚህ ትምህርት ቤት እንዲወጡ ጠንክረን እናስተምራለን” ያለን የርዕሰ መምህሩ ቃል ልባችን ላይ አለ።
እኛ እነዚህን ሁለት ምቹ መማሪያ ህንፃዎች ስናስጀምር የአባ ዮሐንስና ወለህ ገጠር ነዋሪ ወላጆችን፣ መምህራኑን፣ የብሔረሰብ አስተዳደሩን፣ እና ግሪን ኢኒሺዬቲቭን ታላቅ አደራ በመስጠት ጭምር ነው።
ግንባታዎቹን በፍጥነትና በጥራት ሊፈፅምልን የጥረታችን አካል ለመሆንና በነፃ ትብብር ሊያደርግልን የሰቆጣው ተወላጅ ኢንጅነር ኃይሌ ሙሉ ኃላፊነቱን ተረክቧል።
አርሶ አደሮቹ በጉልበት ሊያግዙን ቃል ገብተዋል።
የግሪን ኢኒሺዬቲቭ ቦርድም ሌላ መነሳሳትን ፈጥሮ አስደስቶናል። የኛን የሶስት ጓደኛሞችን ጥንስስ ተረክቦ ዛሬ ያስጀመርናቸውን በሁለት ትምህርት ቤቶች የሚገነቡ ባለ ስድስት ክፍሎች መማሪያ ህንፃዎች ወደ አስር ትምህርት ቤቶች ለማሳደግ ውሳኔ አሳልፏል።
ለትንሿ የሙከራ ፍሬያችን ልብ እንጅ ገንዘብ ይዘን አልተነሳንም።
ከ18 ወራት ከፍና ዝቅ በኋላ እዚህ ደርሰን ግንባታውን አስጀምረን ፣ ወዲህ ወደ አዲስ አበባ ወደመደበኛ ህይወታችን መጣን።
ግን አሁን አይዟችሁ እንድትሉን እንሻለን።
በየመስሪያ ቤታችሁ የተቀመጠውን መጠየቂያችንን ምላሽ እንድትሰጡበት ፣ በየቢሯችሁ የተጣሉ የተሰባበሩ ቁሳቁሶቻችሁን እንድትሰጡን እንሻለን።
በውጭ የምትኖሩ ወገኖች ልትደግፉን ካሰባችሁ ለመማሪያ ክፍሎቹ የሚያስፈልገውን የግንባታ ግብአቶች ልትገዙልን ትችላላችሁ።
አቅም ያላችሁ ባለሃብቶች፣ ድርጅቶች ወይም በቡድን አዋጥታችሁ የዳስና የዛፍ ጥላ መማሪያዎቹን በስማችሁ መገንባት የምትሹ ካላችሁ መደበኛውን ስራ ( the donkey work) እኛ እንሰራላችሁና እናስረክባችኋለን።
በሌላ መልኩም አይዟችሁ ልትሉን የምትሹ ብትኖሩ ደስታችን ወደር የለውም።
በተለይ ሚዲያዎች እንዲሁም የሶሻል ሚዲያ ወዳጆቻችን ይህንን መረጃ ተደራሽ ብታደርጉልን የቁሳቁስ ድጋፉን ለማቀላጠፍ ይረዳናል።
አዎ ፡ የማትጠቀሙባቸውን የመስሪያ ቤት ቁሳቁሶች አትጣሉ ፣ ይልቁን ለእኛ ስጡን ፣ ትምህርት ቤት ለመገንባት እናውላቸዋለን!!
—–
እኛ ( ፋሲል አስማማው ፣ ቶማስ በየነና ደመቀ ከበደ )
እና ግሪን ኢኒሺየቲቭ ኢትዮጵያ !