Connect with us

“አትሳደቡ” ለማለት “ስድብ”ን ምን አመጣው?

"አትሳደቡ" ለማለት "ስድብ"ን ምን አመጣው?
ጀርመን ድምፅ

ነፃ ሃሳብ

“አትሳደቡ” ለማለት “ስድብ”ን ምን አመጣው?

“አትሳደቡ” ለማለት “ስድብ”ን ምን አመጣው?

( ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ)

በሙያዊ አጠራሩ “Audience” በጥሬ ትርጉሙ አድማጭ ፣ ተመልካችና አንባቢ የብዙኃን መገናኛ ይዘትን ተደራሽ በማድረግ ወቅት ትኩረት የሚሰጠው አንኳር ነጥብ ነው። የፆታ፣ የሙያ፣ የዕድሜ፣ የአካባቢ ፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ጉዳዮች የ ” ኦዲየንስ ” ስብጥርን ( Audience Diversity ) ግምት ውስጥ ለማስገባት መነሻም መድረሻም ናቸው።

የጋዜጠኝነት ወዲያና ወዲህ ” ኦዲየንስን ” ከማክበርና ስብጥሩን ከመረዳት አልፋው ይጀምራል፣ ኦሜጋውም ይሆናል።

ትናንት በነበረው የነባሩ / ” Mainstream Media = Newspaper/Magazine, Radio & Television”/  የጋዜጠኝነት ጅማሮ ዘመን “ኦዲየንሱ” የቀጥታ ተሳታፊ አልነበረም። የተሰማውን ( ስሜቱ ልክም ይሁን የተሳሳተ) (Feedback) የሚያደርሰው ወዲያውኑ አልነበረም። በፖስታ ፅፎ በመላክ ፣ አልያም ቅርብ ከሆነ በአካል አስተያየት ይሰጥ ነበር።  ስልክ ሲመጣ አንፃራዊ ፍጥነት ጨመረ።

ቴክኖሎጂ ሲያድግ የብዙኃን መገናኛዎችንና የ “ኦዲየንሱ”ን ግንኙነት ፈጣን አደረገው። በተለይ ህዝብ የሚናገርባቸው የቀጥታ ዝግጅቶች መጀመር ከተቀባይነት ( Messege/information decode) ወደ ተሳታፊነት ( Audience as a participant  ) አሸጋገረው።

ይህም አደገና ዕድሜ ለበይነ መረብ ወደ ብዙኃን መረጃ አቅራቢነት ( Audience as a journalist = citizen journalist) አዘነበለ።

በተለይ አራተኛ መንግስትነቱን በኩራት ተቆናጦ ለነበረው ነባሩ ብዙኃን መገናኛ በማህበራዊ ትስስር ገፆች ( Social Media) መፈጠር ምክንያት ከዕድልና ፈተና ጋር መሳ ለመሳ ተፋጥጦ ይገኛል። የተፅዕኖው ከፍታን የሚያወድሱት አምስተኛ መንግስት (Social Media as a fifth estate) ሆኗል ይሉታል።

ታዲያ በጦማሮች ( Blogs) እና ድረ ገፆች (Websites) አጎንቁሎ የነበረው የ “Citizen Journalism” ጭራሹኑ በማህበራዊ ትስስር ገፅ መረጃ አቅራቢዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ( Social Media Informants and Opinion Leaders, Vlogers and YouTubers etc) የተነሳ የህብረተሰቡን የመረጃ ማግኘትም ሆነ ማድረስ አማራጭ እንዲሁም በቀረበው መረጃ/ News /Programs etc/ ላይ የተሰማቸውን ስሜት ወዲያውኑ እንዲያደርሱ ማስቻሉ ይጠቀሳል።

ዘመኑ የመረጃ ፍሰት ከታች ወደ ላይ የነበረውን ወደ ጎንም ወደላይም ወደታችም እንዲሆን አድርጓል። በ ማህበራዊ ትስስር ገፆች ሰበር ዜናን በቀጥታ ጭምር ከታላላቅ ብዙኃን መገናኛ ቀድመው የሚያደርሱ “Facebookers, YouTubers, Twitterers, Blogers እንደ ህልቆ መሳፍርት በዝተዋል።  ሌሎችም ተጠቃሽ ጠቀሜታዎችን ፈጥሯል። ለራሳቸው ለብዙኃን መገናኛዎቹም እንደ ማሰራጫና መቀበያ ግብአትነት ( platforms) በማገልገል ሌላ አማራጭ ሆነውላቸዋል።

ይህ መሆኑ በብዙኃን መገናኛዎችና በ”Social Media Information/News” የሚያደርሱ ግለሰቦችና ቡድኖች (vis-a-vis)  ዘንድ የትስስር ዕድል በመፍጠሩ “Networked Journalism” እንዲተገበርም መነሻ ሆኗል። ብዙዎቹ ሚዲያዎች በተለይ የራሳቸው ቅጥር ዘጋቢ ጋዜጠኞች በሌሉባቸው ቦታዎች በየአካባቢው ለሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች ጉርሻ ወይም ክፍያ እየሰጡ መረጃ መጋራትን መተግበር ጀምረዋል። የተቋም ለተቋም እንዲሁም  የባለሙያ ለባለሙያ ትስስር መጠናከርን ስለፈጠረ መረጃ መለዋወጥንና ልምድ መጋራትን አቀላጥፏል።

ይህ እንዳለ ሆኖ በራሳቸው ትክክለኛ ስምም ይሁን ድብቅ ስም (Fake or Psyudo Name) ተጠቃሚዎች ለነባር ሚዲያዎች የዝግጅት ክፍሎችና አዘጋጅ ጋዜጠኞች አሁናዊ ግብረ መልስ ( Immidiate Feedback) መስጠታቸው አሳታፊነቱ መልካም ቢሆንም በተቃራኒው ( ተቋምንም ሆነ ጋዜጠኛን ) መፈረጅ፣ መዝለፍና ኢ ስነ ምግባራዊ በሆኑ ቃላት መሸንቆጥና በስድብ ማጥረግረግ ብሎም ዛቻ ማድረስ የዕለት ተዕለት ችግሮች ሆነዋል።

በዚህ “Post Truth Politics” ህዝብ በሚታመስበት ዘመን  የ ” ኦዲየንስ ” ግብረ መልስ በፖስታ፣ በስልክ፣ በአካል አልያም አሁን ደግሞ በ ” comment box, Inbox or status update etc ” ላይ ወዲያውኑ መንፀባረቁ ግድና አስፈላጊ ነው። የግብረ መልሶች ጥናት በብዙኃን መገናኛ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ዘንድ ትልቅ የጥናት መስኮች ( Audience Research ) የሆኑት ብዙኃን መገናኛዎች ያለነሱ ባዶ በመሆናቸው ነው። ይዘት የሚመነጨውም የሚሰራጨውም ከህዝብ ለህዝብ ነውና። ትናንት መረጃ ተቀባይ ብቻ ሆኖ የጫና ሰለባ የነበረ ( Media Indoctrination and Influence) ዛሬ የህብረተሰብ ዝማኔና የዓለም ስልጣኔ ነገሩን ቀይሮታል።

ይህ ከላይ ያነሳሁት የዝማኔ ተግባቦት ምክንያት እንደተጠበቀ ሆኖ የግንኙነት ( Media and Audience relationship) ከበሬታንና ውዴታን ሊያማክል ይገባል።   የቢዝነስ ተቋም ደንበኛ ንጉስ ነው እንደሚለው ሁሉ ለብዙኃን መገናኛዎችም “ደንበኛቸው” ህዝብ ሁለመና ነው። ታዲያ “ደንበኞቹ” ሆን ብለው ፣ በግንዛቤ እጥረት ፣ ከበዛና ከተጋነነ ጥበቃ (expectations) ፣ ከጫና እና ከተለያዩ ምክንያቶች በመነጨ መነሻ ብዙኃን መገናኛዎችን ሊሳደቡ ፣ በስሜት ሊያጠቁ ፣ ሲከፋም የዕቀባ አመፃ ” Boycot” ሊያደርጉ ይችላሉ። እዚህ ላይ “ልክነት” የሚወሰነው አብዝቶ በብዙኃን መገናኛዎቹ ዘንድ ነው። ለዚህም ነው ዘገባ ተደራሽ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን የሚመጣውን ግብረ መልስ ለመቀበልና ለማስተናገድም የ ” Diversity of Audience ” ሁልጊዜ ሊረሳ አይገባም የሚባለው።

በተለይ ለዚህ ፅሁፌ መነሻ የሆነው እንደ ጀርመን ድምፅ ያሉ ዓለም አቀፍና ነባር ብዙኃን መገናኛ ተቋማት ተደራሽነታቸው ትልቅና ተፅዕኗቸውም ሰፊ በመሆኑ ለሚያቀርቡት ይዘት ጥራት ብቻ ሳይሆን የትኛውንም ቀይነት ግብረ መልስ ለማስተናገድ የሚኖራቸው ዝግጁነትና የደንበኛ አያያዝ ብልኃት ለሌሎችም አብነት ( Examplery ) እንዲሆን ይጠበቃል። የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በተለየ ኃላፊነታቸውን እጥፍ ድርብ የሚያደርገው አንድም ድንበር ተሻጋሪ (Cross Continental) ፣ ሁለትም አገር ወካይ (Flagship)፣ ሶስትም ብዝኃነት (Aknowledging diversity) የሚረብባቸው በመሆናቸው ለወከሉት አገርና ህዝብ (Media Owener States) እና በቋንቋው መረጃ ለሚያሰራጩለት አገርና ህዝብ ( Target Audience ) ክብር ሊኖራቸው ይገባል። ባሕር ሲሻገሩ ባሕር ልብ ያስፈልጋቸዋል።

በግብረ መልሶች መጥለቅለቅ ሲያጋጥም የሚመከረው መነሻ ምክንያቱን በአጭርና በረጅም ጊዜ የ ” Audience Feedback Reaserch” ይሰራል። በጥናቱ መነሻ ምክንያቱን መለየት ፣ መመርመርና በጥናቱ ውጤት ተመስርቶ የሚስተካከለውን የማረም፣ የጎደለውን የመሙላት እንዲሁም በግብረ መልስ ሰጪዎች ዘንድ ” ትክክል ያልሆነ” ግንዛቤ ካለም በአክብሮት ማስረዳትና ስህተታቸውን እንዲያርሙ ማሳወቅ ነው። ይህም ጨዋነትን ታሳቢ ባደረገ አቀረረብ ማለት ነው።

ያለዚያ ያያዝኩትን “ስክሪን ሹት” ዓይነት በ ግብረ መልስ ፈታሹ / Feedback Monitor / ስሜት ላይ የተመሰረቱ የሚመስሉና ምናልባትም በተቋሙ “ኤዲቶሪያል” ታውቆ ያልተፃፈ የሚመስል ልጥፍ ብዙዎቹን ቀናኢ ” ኦዲየንሶች” አለማክበርና መናቅ ነው። እንዲህ ያሉ ልጥፎች ” የነኛ እንጂ የኛ ” አይደለም ( Not ours, but theirs) ወደሚል ስሜት ሊመራ ይችላል። የብዙኃን መገናኛዎች የብዙኃን ድምፅ መሆን እንደሚገባቸው ሁሉ የብዙኃንን ግብረ መልስም በብዙኃን ልብ ሊታገሱ ይገባል። ብዙኃኑ ህዝብ የኔ ነው የሚል ስሜት / Belongingness / የሚሸረሸረው በዘገባ ሽፋን ብቻ ሳይሆን ጥቃቅን በሚመስሉ ነገሮችም ነው።

( በነገራችን ላይ ቢቢሲ ሞኒተሪንግ ይቅርታ የጠየቀበት መንገድም ይሁን በደብዳቤው የተጠቀመው ጉዳዩን በጨዋነት ለማስረዳት የተጠቀማቸው ቃላት የሸጋ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው።)

እናም ለአሁኑም ይሁን ለወደፊቱ ብዙኃን መገናኛዎች በሚመጥናቸው የግብረ መልስ ተግባቦት ከፍታ ሊገኙ ይገባል እላለሁ። የጀርመን ድምፅም በትልቁ ስዕል ውስጥ ትንሿን ነቁጥ የሚፈትሹ አንጋፋ ጋዜጠኞች ያሉበት ተቋም ነውና ይህንን ልጥፌን ከረብ እንደሚቆጥረው ተስፋ አደርጋለሁ።

ግልባጭ:- ለጀርመን ድምፅ (አማርኛ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top