ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምን ጠብ ይልልናል?
ከእንግሊዘኛው ጽሁፍ ተነስቶ የተተረጎም
(ክቡር ገና)
የሀገራችን ልሂቃን ምን አይነት መጽሀፍ እያነበቡ ፖሊሲ እንደሚቀርጹና ሀገር እንደሚያስተዳድሩ አይገባኝም፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ የካፒታሊስት ወይም የነጻ ገበያ ስርአት በምድርችን ላይ እያበቃለት መሆኑን የተረዱት አይመስልም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ካፒታሊዝም በአለም ላይ ዘላቂነት ያለውና ለሁሉም የሚዳረስ ሀብት እያስገኘ አይደለም፡፡ ይብሱኑ ካፒታሊዝም በአሁኑ ወቅት በርካታ የሰው ሀይል ከስራ ውጭ በማድረግ አምራች ሀይሉን ስራ አጥ እያደረገ ነው፡፡
በርካታ ገበሬዎችንና አምራች ላብአደሮችን ለድህነት እየዳረገ ነው፡፡ በሰዎች መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት ይበልጥ በማስፋት ላይ ይገኛል፡፡ እንደ ባንክ ባሉ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ቀውስ አባባሽ ሆኗል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትለው መቅስፍት ደንታ ቢስ በመሆን የሰው ልጆችን ህይወት ፈተና ላይ ጥሏል፡፡
ውድ አንባቢያን
የካፒታሊስት ስርአት ፖሊሲዎች ከ20ኛው ክፍል ዘመን ጀምሮ ገሸሽ የመደረጋቸው ነገር እየጨመረ መጥቷል፡፡ በተለይም እንደ ፕራይቬታይዜሽን፣ ልቅ የገበያ ስርአት፣ ሀብታሞች የሚከፍሉትን ግብር መቀነስ የመሳሰሉትና ለአሰሪዎችና ለባለአክሲዎኖች የበለጠ ስልጣን ለሰራተኞች ደግሞ መብት የሚነፍገው የካፒታሊስት የአመራርና የአስተዳደር ዘይቤ ተቀባይነት እያጣ ሄዷል፡፡ ካፒታሊስቶች ፖሊሲዎቻቸውን መተኪያ የሌላቸው አድርገው ቢያቀርቧቸውም ውጤታማነታቸውና ተቀባይነታቸው ግን ከእለት እለት እያሽቆለቆለ መጥቶ ህልውናቸው ፈተና ላይ ወድቋል፡፡
እርግጥ ነው፤ ካፒታሊዝም በውድቀት ጎዳና ላይ ያለ ስርአት ነው ሲባል ጭርሱኑ ሞቷል ማለት አይደለም፡፡ ካፒታሊዝም በሞትና በህይወት መካከል ሆኖ ሊከስም ገደል አፋፍ ላይ የቆመ ስርአት መሆኑን ግን ማመልክት ይቻላል፡፡ ካፒታሊዝም አንገቱ ተቆርጦ ከመሞቱ በፊት አንደሚንፈራፈር ዶሮ ሊቆጠር ይችላል፡፡
አንገቱ የተቆረጠ ዶሮ ሲንፈራፈር በህይወት ያለና በሀይል የተሞላ መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ በመጨረሻ ግን ተንደፋድፎ ይደክምና እስከ ወዲያኛው ያሸልባል፡፡ ወድ አንባብያን ካፒታሊዝም መጀመሪያ ከነበረበት በታሪክ አስፈላጊና ዘመናዊ ስርአትነት ዛሬ በታሪክ ወደ ማያስፈልግና አጥፊ ስርአትነት ተሸጋግሯል፡፡
በጣም የሚገርመው ነገር ግን መሪዎቻችን ይህን በለወጥ ላይ ያለውን አለም አለመገንዘባቸው ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የለውጥ ሀይል ነኝ የሚለው ቡድን ወደ መንግስት ስልጣን ከመጣ በኋላ ይፋ የተደረገው ‹‹የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ›› የሚለው የፖሊሲ ሰነድ ነው፡፡
በነሀሴ ወር 2011 ዓ.ም የወጣው ይህ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ የተሰኘው የመንግስት ሰነድ በይድረስ ይድረስ የተዘጋጀ ከመሆኑም በላይ በጥሞና ሲታይም አደገኛ ሰነድ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ አሁን በተጨባጭ ላለው የአለም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጭራሽ እይታው የተጋረደ መሆኑ ነው፡፡ ሰነዱ የተምታታና አሳሳች ከመሆኑም በላይ በተቻለ መጠን የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትንና የልማት አጋሮች ተብዬዎችን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው፡፡
እስቲ ከሰነዱ ውስጥ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አንኳር አንኳሩን ጉዳይ እንጠቃቅስ፡፡ በመጀሪያ በኢኮኖሚ ማሻሻያው አስፈላጊነት ላይ የተሰጠውን ሀተታ እንይ፡-
በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረግ አስፈለጊ የሆነበት ምክንያቶች በሶስት መሰረታዊ ሃሳቦች ላይ ይመሰረታሉ፤
- አንደኛው፣ ባለፉት 15 ዓመታት በአገራችን ከፍተኛ የሰው ኃይልና የመሰረተ ልማት ግንባታ ተከናውነዋል፤ እነዚህ ስኬቶች በራሳቸው ጠቃሚ ከመሆናቸው ባሻገር ምረታማነቱ የላቀ ሠራተኛ ለመፍጠር ያለቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን መሰሉን አጋጣሚ በመጠቀም ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ለግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ አመች ሁኔታዎች መፍጠር አጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
- ሁለተኛ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን ቀጣይ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት ያጋጠሙ የማክሮ ኢኮኖሚና መዋቅራዊ መዛባቶችን በመፍታት ለኢኮኖሚ እድገትና አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት አስፋላጊውን መደላድል መፍጠር ተገቢ ነው፡፡
- በሶስተኛ ደረጃም በመካከለኛ ዘመን እንደርስበታለን ብለን በዕቅድ የያዝነውን የመካከለኛ ገቢ አገሮች ጎራ የመቀላቀል ራዕይን ለማሳካት የፖሊሲና ተቋማዊ ማዕቀፎችን ደረጃ ማሻሻል የግድ ይላል፡፡ ለአብነትም፣
○ የማክሮ ኢኮኖሚ ማእቀፉ ዘመናዊ፣ ወቅቱ በሚፈልገው ደረጃ የሚገኝ እና የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል ሊሆን ይገባል፣
○ የምናስበውን ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሉ ቀልጣፋና ግልጽነት የተላበሱ መንግሥታዊ ተቋሞች መኖር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡
ከላይ እንዳየነው በኢኮኖሚ ማሻሻያው አስፈላጊነት ትንታኔ ውስጥ ያሉት ‹‹ የማክሮ ኢኮኖሚ ማእቀፉን ዘመናዊ ለማድረግ፣ የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓትን ለመዘርጋት፣ የምናስበውን ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት›› በሚሉት አባባሎች ውስጥ ከላይ የጠቀስናቸው የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትንና የልማት አጋሮች ተብዬዎች ድምጽ ጎልቶ ይሰማናል፡፡
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አጀንዳን ቀጣይ አቅጣጫን በተመለከተም በሰነዱ የሚከተለው ሰፍሮ ይገኛል፡-
በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት የሚኖረን የልማት ግባችን አቅጣጫ የሚከተለው ነው፡-
- ጠንካራና መጠነ ሰፊ መካከለኛ ደረጃ ኢኮኖሚን መገንባት፣
- ስር የሰደ ደድህነትን በማስወገድ እንዲሁም ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችን አኃዝ በግማሽ መቀነስ፤
- መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስፋፋት፤
- ታዳጊ የሆነ የገበያ ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችል የፖሊሲና ተቋማዊ ማዕቀፍ መዘርጋት፣
- ለኢንቨስተሮችና ሸማቾች አስፈላጊ የሆነ የፋይናንስ አቅም የሚፈጥር ቀልጣፋ፣ ጠንካራና የተሳለጠ የፋይናንስ ገበያ መሰረተ ልማት መገንባት፣
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ሀብት በተመለከተ ደግሞ አጀንዳው የሚከተለውን ይላል፡-
- ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳውን ለማሳካት የሀገር ውስጥ ቁጣባን በማሻሻል እንዲሁም የውጭ ፋይናንሲንግ በሚመለከት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በመሸጥ የሚገኝ ገቢ ይሆናል፡፡
- በዚህም መሠረት ማሻሻያውን ለመተግበር የውጭ ሀብት በስፋት ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡
በመሆኑም ይህን ገንዘብ ለማሰባሰብ የተለያዩ የብዙሃንና የሁለትዮሽ የውጭ ሀብት ግኝት ምንጮችን ቀላል ያለ ብድርን (concessional borrowing) ጨምሮ ለመጠቀም የሚያስችሉ ስልቶችን በሥራ ላይ ለማዋል በዕቅድ ተይዟል፡፡
ወድ አንባቢያን
በሚቀጥሉት አስር አመታት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ሀብት በተመለከተ ሰነዱ በግልጽ እንዳስቀመጠው አንደኛው ስልት የሀገር ውስጥ ቁጠባን ማሻሻል ነው፡፡ ሆኖም ግን ሰነዱ የሀገር ውስጥ ቁጠባ የሚሻሻልበትን መላ ዘርዝሮ አላስቀመጠም፡፡ ከላይ አንደ ተመለከተው ግን አጀንዳውን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው ሀብት ከሁለት ምንጮች ለማግኘት ትኩረት ተደርጓል፡፡ እነርሱም
1ኛ. የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መሸጥ
2ኛ. የውጭ ሀብት በብድር በስፋት ማሰባሰብ
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አጀንዳ አልፋና ኦሜጋ ፍንትው የሚልልን፡፡ አጀንዳውን ተግባራዊ ለማድረግ በዋነኛነት ሀገሪቱ ከመቶ አመታት በላይ ጀምሮ ስትገነባቸው የቆየችውን እንደ ቴሌ ያሉ የህዝብና የመንግስት ድርጅቶችን በመሸጥና ከአለም አቀፍ ገንዘብ ተቋማት ከሚገኝ ብድር እቅዱን ሊያሳካ የተነሳ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምኑን ሀገር በቀል ሆነው?
ወገኖቼ ሙሉውን ሰነድ አንብቡና ደግሞ ፍርዱን ስጡ፡፡ ለማሳያ ያህል ከጠቀስኩት አንኳር ነጥብ በተጨማሪ ሙሉን ሰነድ በጥሞና አንብቡና አጀንዳው መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ወይም የውጭ ድርጅቶች ይጠቅም እንደሆን ፍረዱ፡፡ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ፕሮግራም በእውነት ለተባበረችና ለጠንካራዋ ኢትዮጵያ ሲባል የተቀረጸ ነው ወይስ ሀላፊነት የማይሰማቸውን የውጭ የገንዘብ ተቋማትን ለማስደሰት የወጣ ሰነድ ነው? ወይስ ህዝብን ማደንዘዣ ፕሮፓጋንዳ ነው?
እናም ወገኖቼ አጀንዳው ከአጭር ጊዜ ግብ ይልቅ የረጅም ጊዜ ዘላቂ ጥቅምን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንና አለመሆኑን አይታችሁ ፍረዱ፡፡ ኧረ ለመሆኑ ፕሮግራሙ ኢትዮጵያውያንን ለመመገብ፣ ለማስተማር፣ ከህመም ለመፈወስና የመጠለያ ችግር ለማቃለል በሚያስችል መልኩ አቅዷል? ተስፋ ያላትንና ውጤታማ ኢትዮጵያንስ ለመገንባት ይችላል? ወይስ ኢትዮጵያን ከናካቴው ለባእድ ካፒታል አሳልፎ የሚሰጣትና ብሎም ለብዝበዛ የሚዳርጋት አጀንዳ ነው? ውድ ወገኖቼ ፍርዱን ለናንተ እተወዋለሁ፡፡
በዚህ ከእለት ወደ እለት አለመረጋጋት እያየለ በሚሄድበት የፖለቲካ ምህዳር ይህ መንግስት የተለያዩ አመለካከቶች ያሏቻን ልሂቃንን በማሰባሰብ በጥበብ ስርአቱን አንጸው የሁሉም መብት የሚከበርበትና የሁሉም ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት አስተዳደር ለመመስረት ተስኖታል፡፡ ከዚህ በተጻራሪ ግን መንግስታችን በሁሉም የአለማችን ክፍል ከገበያ ውጪ ሆኖ የተረታውን የኒዮ ሊብራሊዝም ስርአት ለመመስረት እየተጣደፈ ይገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሀገሪቱን የመደመር ፍልስፍና፣ የፓርኮች ግንባታ፣ የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ፣ የግጭቶች፣ የአክቲቪስቶችና የፖለቲከኞች እሰጥ አገባ ዜና አጥለቅልቋታል፡፡ ሁሉም ግን ማስቀየሻ ዘዴዎች ናቸው፡፡
ውድ አንባቢያን ከምንድነው የሚያስቀይሱት ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም፡፡ ማስቀየሻ ዘዴውማ የኢትዮጵያ ስትርቴጂያዊ ሀብት ሆኑትን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውጤታማ አይደሉም በሚል ሰበብ ለአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጥቅም ሲባል የሚከናወነውን ሽያጭ ለማቀላጠፍ ሲባል ነዋ!
ሀሳቤን ለማጠቃለል ያህል አሁን ካፒታሊዝም በስርአቱ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ አይደለም፡፡ በስርአቱ ፍጻሜ ላይ የሚገኝም አይደለም፡፡ በርግጠኝነት ግን ካፒታሊዝም በእድሜው መጨረሻ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ስርአት ነው ግን ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህም ካፒታሊዝምን የሚተካ ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበና በተግባር የሚገለጽ ስርአት ካልመሰረትን ስርአተ አልበኝነት በመላ ሀገሪቱ ይነግሳል፡፡ ይህ ስርአተ አልበኝነትና ደም መፋሰስ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ውድመት ከማስከተሉም ባሻገር እስካሁን ገነባነው የምንለውን ጥሩ ነገር ሁሉ የሚያጠፋብን ነው፡፡ የዚህን አውዳሚ ሁኔታ ጅምሩን ደግሞ በሀገራችን እያየነው ነው፡፡