የምርጫ 2013 ክራሞት
(ፍሬው አበበ)
የዘንድሮ ምርጫ ሒደቱ ቀጥሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከታህሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የምርጫ ክልል ቢሮዎች መከፈት፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና መስጠት፣ ለዕጩዎች ምዝገባ ትምህርት መስጠት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክቶቻቸውን እንዲመርጡ ማድረግ ከሞላ ጎደል ተከናውኗል፤ እየተከናወነም ይገኛል፡፡
በአሁን ሰዓትም የተወዳዳሪ ዕጩዎች ምዝገባ እንዲሁም የምረጡኝ ቅስቀሳ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ይህ ሒደት የምርጫው የመጨረሻ ውጤት እስከሚገለጽበት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል ተብሎ ይገመታል፡፡
በእስካሁን ሒደት ከታዩ ችግሮች አንዱ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል መገደል የሚጠቀስ ነው፡፡ የኢዜማ የቢሾፍቱ ከተማ አድአ ምርጫ ወረዳ 1 ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ግርማ ሞገስ የካቲት 7 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቋል፡፡
ኢዜማ በመግለጫው የተፈጸመው ወንጀል እንዲጣራ፣ ቀደም ሲል በሟች ላይ ማስፈራሪያ ሲፈጽሙ የነበሩ የቢሾፍቱ የፓርቲና የመንግስት ኃላፊዎች የምርመራው አካል እንዲሆኑ፣የክልሉም ሆነ የፓርቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች ድርጊቱን በይፋ እንዲያወግዙ መጠየቁም አይዘነጋም፡፡
የኢዜማ ቃል አቀባይ ናትናኤል ፈለቀ እንደሚሉት በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለዕጩዎች ምዝገባ እና ለምርጫ ቅስቀሳ ፓርቲያቸው ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ ወደስራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡ በእስካሁኑ ሒደትም በአንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች ያለመከፈት እና አንዳንድ የተከፈቱትም ቢሆን የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ያለመቻል ችግሮች እንደነበሩና እነዚህን ችግሮች ለምርጫ ቦርድ አሳውቀን አንዳንዶቹ እየተፈቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ኢዜማ በአዲስአበባ በተለያዩ አካባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳ ባካሄደበት የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ሽሮሜዳ አካባቢ በሚገኙ ፖሊሶች ቅስቀሳ መኖሩን አናውቅም በሚል ስራቸውን ማስተጓጎላቸውን፣ በኮንሶ አካባቢ በአባሎቻቸው ላይ ድብደባና እስር ማጋጠሙንና የፓርቲው አባሎች ከሁለት ቀናት እስራት በኋላ መለቀቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የኢዜማ አባሉ አቶ ግርማ ግድያ በማስመልክት ፓርቲው ባወጣው መግለጫ በምርጫው ሒደት ነጻና ፍትሐዊ እንዲሆን መሟላት ከሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል የሚከተሉትን ጠቅሷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢዎች በነጻነት መንቀሳቀስ፣ ለማህበረሰቡ አማራጫቸውን ማቅረብ መቻል እና ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በምርጫው ውስጥ ያለምንም ፍርሃት መሳተፍ መቻላቸው እንዲሁም ከምርጫው ጋር በተያያዘ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ለማንም ሳይወግኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በገለልተኝነት ማስተናገድ መቻላቸው መረጋገጥ የምርጫውን ነጻና ዴሞክራሲያዊነት እንደሚወስን ይጠቅሳል፡፡
በምርጫ ቅስቀሳ ዋዜማ በፓርቲው አባል ላይ የተፈጸመው ግድያ እነዚህን መስፈርቶችን በተመለከተ ብዙ መሰራት ያለባቸው የቤት ስራዎች እንደሚቀሩ በግልጽ ያሳየ ነው”ብሏል፡፡
የዘንድሮ ምርጫ ከጀምሩ በብዙ ውጣውረዶችና ውጥንቅጦች ውስጥ ያለፈ መሆኑ የመጀመሪያ ችግር ነው የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ ናቸው፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ተከትሎ የምርጫ መራዘም፣ የህገመንግስት ትርጓሜ ጉዳይ፣ የምርጫው መራዘም ተከትሎ ከህወሓት ጋር ውዝግብ ውስጥ መገባቱና ሰንብቶም ጉዳዩ ወደግጭት ማምራቱ፣ በዚህም ምክንያት ንጹሃን ሰዎች ጭምር ሞት፣ መፈናቀልና ጉዳት መድረሱ፣ የተፈጠረው ምስቅልቅል ኢኮኖሚውም ላይ መንጸባረቁ የዘንድሮ ምርጫ ያስከተላቸው ጣጣዎች መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
አቶ ሙሼ እንደሚሉት በእስካሁን ሒደት ከምርጫ ጋር ተያይዞ በህዝብ ዘንድ መነሳሳት እያዩ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የምርጫ ጉዳይን ስሜት ሰጥቶ የመከታተል፣ እገሌ ቢመረጥ የተሻለ ነው ብሎ ተስፋ የማድረግ፣ የመከራከርና የመሳሰሉ ጉዳዮች በሕዝብ ውስጥ እየታየ ነው ማለት እንደማይቻል በመጥቀስ ምናልባት በቀጣይ ሒደቱ እየገፋ ሲመጣ፣ የሚዲያ የፊት ለፊት ክርክር ተጀምሮ ሲሟሟቅ የህዝቡም ስሜት ሊሻሻል እንደሚችል ተስፋ ያደርጋሉ፡፡
አቶ ማሙሸት አማረ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚደንት በበኩላቸው ዘንድሮ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ተጨባጭ ሁኔታ እንደሌለ በተደጋጋሚ ብንገልጽም ሰሚ አጥተን ወደምርጫው ገብተናል ብለዋል፡፡
በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላም የለም፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ያለምንም ስጋት ተዘዋውረው የምረጡኝ ቅስቀሳ ሊያደርጉ የሚችሉበት አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት የለም፡፡ እንኳንስ እኛ ገዥው ፖርቲ ራሱ በአንዳንድ አካባቢዎች መንቀሳቀስ የማይችልበት ሁኔታ መፈጠሩን ታዝበናል፡፡ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንዴት ይቻላል ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
ይኸም ሆኖ ግን ባንምንበትም በሒደቱ መሳተፍ ስላለብን ምርጫ ውስጥ ገብተን በመላ ሀገሪቱ ዕጩዎቻንን እያቀረብን እንገኛለን ብለዋል፡፡ ሆኖም በደቡብ እና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ ክልል ቢሮዎች እጅግ ዘግይተው የተከፈቱበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ምርጫ ቦርድ የካቲት 21 ይጠናቀቃል ያለውን የዕጩ ምዝገባ ጊዜ የሚራዘምበት ሁኔታ ሊያጤነው ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ ማሙሸት አያይዘውም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተባብረን በመስራት የህዝባችን ድምጽ ላለመሻማት እየሰራን እንገኛለን ያሉ ሲሆን በተለይ የሚዲያ ዘገባ ሽፋን አሰጣጥ ጉዳይ እስካሁን በታየው ሁኔታ አድሎአዊ በመሆኑ በፍጥነት ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ብልጽግና ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ቅቡልነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት በቅርቡ ከፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባካሄደው ውይይት የብልጽግና ፓርቲ ዋነኛ ትኩረት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ህጋዊ መንግስት መገንባት መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የምርጫ ክትትል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ ጠቅሰዋል፡፡
በየደረጃው ያለው የብልጽግና አመራር ድርጅታዊ ዲስፕሊኑን መጠበቅና አመራሩም የሚያወራውን በተግባር የሚፈጽም መሆን ይገባዋል ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አለሙ ስሜ ናቸው፡፡
በሱፐርቪዥኑ የተለዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል በድክመት የተገለጹት ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ማመላከታቸውን ከፓርቲው ይፋዊ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ በብሔራቸው ከተሰየመ ክልል ውጪ የሚኖሩ ዜጎችን የምርጫ ተሳትፎ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ማሳሰቡም የሚታወስ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የአማራ ክልል ተወላጅ ሆኖ ኑሮውን የመሰረተው በኦሮሚያ ወይንም በሌላ ክልል ሊሆን ይችላል፡፡
የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ ሰውም በተመሳሳይ ሁኔታ ለብዙ አመታት በአማራ ክልል ኖሮም ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ወገኖች በመጪው ምርጫ በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት የሚሳተፉበት አስቻይ ሁኔታ እንዲመቻች መማክርቱ ጠይቋል፡፡
የምርጫ ቦርድ የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት በመጪው ምርጫ በሚያደርገው ዝግጅት አንዳንድ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ባለስልጣናት ትብብር እንደነፈጉት መናገሩ ተሰምቷል፡፡
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ባቀረቡት ሪፖርት በተለያዩ አካቢዎች ያሉትን የሎጀስቲክ እቅስቃሴና አስፈጻሚዎች በተገቢው ሰዓት ከምርጫ ጽ/ቤት ወደ ምርጫ ጽ/ቤት እየተንቀሳቀሱ ስራቸውን ለመስራት የሚያስችላቸውን የመጓጓዣ መኪኖች ከክልል መንግስታት በሚፈለገው መጠን እንዳልቀረበና ይኸም አጠቃላይ ሒደቱ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ሚና አስረድተዋል፡፡
ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በተገኙበት በበይነ መረብ አማካይነት ከክልል መንግስታት ጋር ስለምርጫው ሒደት የስራ ግምገማ ውይይት አድርገዋል፡፡
በዚህ ውይይት በተገኘ መግባባት መሰረት የገጠሙ ችግሮች በቶሎ ሊፈቱ እንደሚችሉ ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ያሰፈሩት ማስታወሻ ይጠቁማል፡፡(ማስታወሻ፡- ይኸ መጣጥፍ በኢንተር ኒውስ ኢትዮጵያ ድጋፍ የተዘጋጀ ነው)