መካነ ሥላሴ-መሀለ ሥላሴ፤ ታላቁ ቅርስ ጉያ ደረስኩ
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በኢትዮጵያ ታሪክ በውጪ ጸሐፍት ጭምር ገናናነቱና ውበቱ የተገለጸለትን የወረኢሉ መካነ ሥላሴ ጎብኝቶታል፡፡ መሀለ ሥላሴ ሲል የቦታውን ዛሬ ከትናንት እያነጻጸረ እንዲህ ይተርከዋል፡፡)
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
እንደ አልቫሬዝ ፈዝዣለሁ፡፡ እሱ እንደምን ከነ ሕይወቱ አይቶ ቻለው ያስባለኝ ያፈዘዘኝ የቅርሱ ፍራሽ ነው፡፡ ወረኢሉ ነኝ፡፡ ከወረኢሉ ከተማ አስራ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፡፡ ቦታውም ታሪኩም መካነ ሥላሴ ይባላል፡፡ ደቡብ ወሎ ኢትዮጵያ፤ አፍሪቃ፡፡
ዐፄ ናኦድ ያሰሩት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ እንዲሁ አላለቀም፤ የሁለት ነገሥታት ጉልበት ፈጅቷል፡፡ ጨርሰው ውብ ያደረጉት ደግሞ ዐፄ ልብነ ድንግል ናቸው፡፡ ከአስር ዓመት በላይ የፈጀው መካነ ሥላሴ በጥርብ ነጭ ድንጋይ የተሰራ እንደነበር አልቫሬዝ ሲደርስ ያየውን ነግሮናል፡፡ ያ ነጭና ጥርብ ድንጋይ ፈራርሶ ዙሪያውን ከቦ እኔ ስደርስ አይቼዋለሁ፡፡
ምን አፈረሰው? ትሉኝ ይሆናል፡፡ ከዚያ ቀድሞስ ትናንቱን ልንገራችሁ፡፡ መጠኑ ግዝፈቱ ውበቱና ግዛቱ ታላቅ ነበር፡፡ መጋረጃዎቹ በሙሉ ባለ ጌጠኛ ግምጃ ናቸው፡፡ ያኔ አልቫሬዝና ጓዶቹ እጅግ ያማረና ለአንድ ታላቅ ንጉሠ ነገሥት የሚገባ መሆኑን የመሰከሩለት መካነ ሥላሴ፡፡
ዛሬ ምልክቱ አልጠፋም፡፡ ግዙፉ ቤተ ክርስቲያን ፍራሹ መጠኑን አይሸሽግም፡፡ በናድነው ታሪክ ላይ እንደ ተራራ ከፍ ብሎ የሚታይ አሻራን አትሟል፡፡ የማየውን እነግራችኋለሁ፡፡ እኔ እንደ አልቫሬዝ መካነ ሥላሴ ቆሞ አልደረስኩም፤ አልቫሬዝ የነገረንን ግን ወድቆ አይቼዋለሁ፡፡ ጌጠኛ ባለ ሀረግ ድንጋዮች እዚህም እዚያም ወድቀዋል፡፡
መካከሉ ላይ አንዲት ትንሽ ቤተ ክርስቲያን ቆማለች፡፡ የግዙፉ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ገላ እዚያ ውብ ደልዳላ ሜዳ ላይ ተኝቷል፡፡ አቤት የድንጋዮ ንጣፍ ውበት፡፡ ፈርሶ የሚኖር ወድቆ የሚነሳ ቅርስ፤
ዛሬ በያኔው በወርቅና በብር በተለበጠው በር አልገባሁም፡፡ የፍቱል አል ሐበሽ ጸሐፊና የኢማም አህመድ ዜና መዋዕል ከታቢ እንደ እኔ እዚህ ቆመው ኢማሙ ያዩትን ሲጽፍ እንዲህ ይላል፤
“ከቅርብ ረዳቶቻቸው ጋር ሲመለከቷት ዓይን የምትማርክ ሆና አገኙዋት፡፡ በወርቅና በብር ቅብ የተንቆጠቆጠች ናት፡፡ የል ፈርጦችም በብዛት አሉባት፡፡ በሯ ከእንጨት የተሰራ ሲሆን ርዝመቱ አስር ክንድ ስፋቱ ደግሞ አራት ክንድ ይሆናል፡፡ በሩ በብርና በወርቅ የተንቆጠቆጠ ነው፡፡”
ዛሬ ጠፍ መሬት አያለሁ፡፡ ግን የማይፈርስ ታሪክ፡፡ የማይጠፋ ክብር፡፡ የሚናገር ውበት፡፡ ትናንት የሚመልስ ያልኖሩት ትዝታ፤
ግራኝ መሐመድ አብረዋቸው የነበሩትን አረቦች እዚያ መካነ ሥላሴ ደጃፍ እንደቆመ በሥራው ከተደነቁ በውበቱ ከፈዘዙ በኋላ እንዲህ ያለ ነገር በዓለምስ አለ? ብለው ነበር፡፡ ማንም አለ ብሎ አልመለሰም፡፡ ይልቁንስ “በሮምም ይሁን በህንድ እንዲህ ያለ ነገር መኖሩን አላየንም አልሰማንም” አሉ፡፡
የእርስ በእርስ ጦርነቶቻችን ትናንትን በሙሉ ነበር አድርገውት ቀርተዋል፡፡ የፈዘዙ እንግዶች ያዩትን እኛ ባለቤቶቹ አንባቢዎች ሆነን ቀርተናል፡፡ በዚያ የቆላውና ደጋው መሪዎች የሃይማኖት ጦርነት መካነ ሥላሴ ዛሬ የለም፡፡ 1528 እንደ ፈረሰ ቀረ፡፡
የመካነ ሥላሴ ታቦት ከዚህ ሄዶ አዲስ ዓለም አካባቢ ፍየታ ሲኖር መቆየቱንና በኋላም አዲስ አበባ የአሁኑ ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል የገባው ታቦት መሆኑን የቤተክርስቲያን መረጃዎች ላይ ዳንኤል ክብረት አስፍሮታል፡፡
ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ በታሪከ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ እንዳሰፈሩት የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ንጉሥ ምኒልክ በነገሡ በ25 ዓመት ከሰባት ወር ከስምንት ቀን በዘመነ ሉቃስ 1883 ዓ.ም. ሚያዚያ መጀመሩንና ሐምሌ ሥላሴ ታቦቱ መግባቱን ነግረውናል፡፡
መካነ ሥላሴ ዳግም አጠገቡ ግዙፍ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን እየተሰራ ነው፡፡ እንግዳ ነህ ብለው ወደ ጎጆአቸው ያስገቡኝ የመንደሯ ሰዎች ጥሩ አድርገው ጋበዙኝ፡፡ “የሥላሴ እንግዶች እኮ ናችሁ፤ እንኳን መሃል ሀገር መጥታችሁ” አሉ አንዲት እናት፡፡
ሀገሬ ካርታ ላይ ያለሁበትን አየሁ፡፡ ዓይኔ ኢትዮጵያ እንብርት ላይ ያረፈ መሰለኝ፡፡ ለዚህ ነው መካነ ሥላሴዎች መሀለ ሥላሴ ነው ብለው የሚያምኑት፡፡