Connect with us

አድዋ ዘመቹ ወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስና ተአምረኛው የጊዮርጊስ ስዕል፤

አድዋ ዘመቹ ወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስና ተአምረኛው የጊዮርጊስ ስዕል፤
ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

አድዋ ዘመቹ ወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስና ተአምረኛው የጊዮርጊስ ስዕል፤

አድዋ ዘመቹ ወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስና ተአምረኛው የጊዮርጊስ ስዕል፤

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የወረኢሉ ቆይታ ጉዞውን ተረካ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በወረኢሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገውን ቆይታና አድዋ ተጉዞ የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕል በተመለከተ በዛሬ ትረካው እንዲህ አጋርቶናል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

ውብ ቅጥር፤ ገና ሲደርሱ ሞገሱ የሚቀበል፡፡ ገና ሲገቡ ታሪኩ እንደ ጋቢ የወረኢሉን ብርድ ገፍፎ የሚጥል፡፡ ደብረ ሰላም ወረኢሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ፡፡

ወደ ውስጡ ስገባ ደጃፉ ላይ አንድ ቀደምት የድንጋይ ቤት በስተግራ በኩል አይቼ ነበር፡፡ አናቱ ላይ “የታላቁ ደብር የወረኢሉ ቅዱስ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን” ይላል፡፡ ከስሩ ደግሞ “የተመሰረተበትም ዘመን ፲፪፻፳ 1220 ዓመተ ምህረት በንጉሥ ነአኩቶ ለአብ ዘመነ መንግሥት ነው” ይላል፡፡

የድንጋይ ቤቷ ከቤተክርስቲያኑ ቅጥር ከውስጥ በኩል የበለጠ ደምቃ ትታያለች፡፡ የዐፄ ምኒልክ የጸሎት ቤት ነበረች፡፡ ባለ ደርብ ናት፡፡ ከላይ የንጉሡ ማረፊያ፤ ከታች የመስተንግዶ ክፍሎች፡፡ ፊቷን ከደብሩ ትይዩ የምታሳይ መስኮት አለች፡፡ ከፍርድ አውዱ ጋር ንጉሡ የሚተያይባት እንደሆነች ሰማሁ፡፡ ወረአሉ የምኒልክ ስስት፤ 

ቤተክርስቲያኑ ግዙፍና ክብ ነው፡፡ ዙሪያውን እድሜ ጠገብ እጽዋት ዘብ ቆመውለታል፡፡ ሲተከል እርስቱም ታሪኩም ብዙ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን እንኳን ልተርክ ብል ጊዜ አይበቃኝም፡፡ ዐፄ ገላውዴዎስ ከምስራቁ ኃይል ጦርነት ድል በኋላ ድርማን ለመቀመጫነት የመረጡበትና ወረኢሉን ቤተ መንግስታቸውን ለማነጽ አንድ ምክንያት የሆናቸው ይህ ታሪካዊ ስፍራ ሳይሆን እንደማይቀር ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ወደ ውስጡ ገባሁ፡፡ በርና መስኮቶቹ በጣም ይገርማሉ፡፡ ከአዲስ አበባ የመጣው የወረኢሉ ተወላጅ፤ የወረኢሉ ታሪክ አርምሞን ሰባሪው፤ ትጉሁ አስጎብኚ መምህር መታሰቢያ እያስጎበኘኝ ነው፡፡ እንደ ቤተክርስቲያን ልጅም እንደ ታሪክ አንባቢ እና አድማጭ ምሁርም ከሚነግረኝ የሚጎድልብኝ እንደሌለ ተረድቻለሁ፡፡

የቆምኩበት የማየው የድል ብሥራት ውጤት ቅርስ ነው፡፡ እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ ብለው ንጉሠ ነገሥቱ የጠሩት ሰራዊት ዛሬ ከያኒው እንዳለው ወይ ሳይባሉ ቢቀሩ ያኔ “እኛ እኛን አንሆንም ነበር” ብለው የከተቱት እዚህ አረፉ፡፡

በሠራዊቱ ብዛት፤ በዝግጅቱ ድምቀት ያልተመኩት ምኒልክ ቅዱስ ጊዮርጊስን አደራ ብለው ተሳሉ፡፡ ከድል በኋላ ይህ ቤተክርስቲያን አምሮ እንዲሰራ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የኩራት ምክንያት የሆነው አድዋ ምክንያት ሆነ፡፡፡ አድዋና ወረኢሉ የአንድ ሳንቲም አንድ ገጽታ የሚባሉ፤ ሊነጠሉ የማይችሉ ናቸው ይላል፡፡ አስጎብኚዬ መታሰቢያ፡፡

ሦስት ግዙፍ በሮች ያሉት ቤተ ክርስቲያን የግንባታ እንጨቶቹ ከተመረጠ ቦታ ከአልብኮ ሳልመኔ የመጡ ናቸው፡፡ አቤት የበርና የመስኮቱ ቅርጾች፡፡ አቤት አሰራርና ጥበብ፡፡ ይሄ ይታያል እንጂ አይተረክም፡፡ 

ከድሉ በኋላ የድሉ ክብር ለፈጣሪ የሰጡት ንጉሥ ምኒልክ ሀገሬን ሰላም አድርገሃል፤ ድል ሆኗልና ታቦቱም ደብረ ሰላም ይባል ያሉት ነው፡፡ 

መታሰቢያና አገልጋዮቹ ወደ ፊት ቀደሙ፡፡ ቅድስት ውስጥ ነን፡፡ መቅደሱን ተደግፎ የቆመውን ሥዕል አወረዱት፡፡ ተገለጸ፡፡ ውብ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕል ነው፡፡ “ይሄ ወደ አድዋ የዘመተው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕል ነው” አለኝ መታሰቢያ፡፡

በምናብ ወደ አድዋ ሄድኩ፡፡ ነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ለጥቁሮቹ ያግዝ ነበር ብለው ነጮቹ ስለመሰከሩለት ፈረሰኛ እያሰብሁ ነው፡፡ ወረአሉ፤ ደብረ ሰላም፡፡ የድሉ መጀመሪያ፡፡ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡  

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top