በአዲስአበባ ከፍተኛ የሽብር ጥቃት ቡድን ተያዘ
~ የቡድኑ ዓላማ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኢምባሲን ለማጥቃት ነበር
ከውጭ የሽብር ቡድን አባላት ተልዕኮ በመቀበል አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት በመፈጸም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ እንዲሁም የአፍሪካና የዓለም አቀፍ የዲፖሎማሲ ተቋማት መቀመጫ የሆነቸውን የአዲስ አበባን በጎ ገፅታ ለማበላሸት በዝግጅት ላይ እንዳሉ የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን 15 የሽብር ቡድኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የተደራጀ የህቡዕ ቡድን መስርተውና ከሽብር አቀነባባሪዎች የውጭ ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የቆዩት አሸባሪዎች ለጥቃት ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጇቸው ከፍተኛ የጦር መሣሪያዎችና ለፍንዳት ስራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቄሳቀሶችና የተለያዩ ሰነዶች ተገኝተዋል።
የህቡዕ ቡድኑ በአዲስ አበባው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት፣ የጥናትና የመረጃ ማሰባሰብ ስራ ሲያካሂድ እንደቆየ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች መገኘታቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከህዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከሌሎች የሀገር ውስጥና የውጭ መረጃ ተቋማት ጋር በመሆን ጥብቅ ክትትልና የመረጃ ልውውጥ በማድረግ የታቀደውን የሽብር ጥቃት ማክሸፍ ችሏል።
በአዲስ አበባ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ በህቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል ጥቂቶቹ ከመያዛቸው በፊት በኤምባሲው ህንጻ አካባቢ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ይዘው ለድብቅ ሴራቸው ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም በክትትል መታወቁን መግለጫው አትቷል።
የሽብር ጥቃቱን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል የቡድኑን አባላት ሲመራ የነበረው የ35 ዓመቱ አሊ አህመድ አርዳይቶ ከፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመር ቢሮ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።
ለአሊ አህመድ አርዳይቶ ለሽብር ጥቃቱ ማቀነባበሪያነት እንዲውል በአሥር ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር እንደተላከለት ከተሰበሰቡ መረጃዎች ማረጋገጥ እንደተቻለ የጠቆመው መግለጫው፤ ከዚህ ግለሰብ ጋር ግንኙነት የነበረውና የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በህቡህ ሲያሴር የቆየው መሃሙድ አብዱልቃኒ የተባለ ሌላ ተጠርጣሪም ከቀናት በኋላ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት በመኖሪያ ቤቱ የጦር መሣሪያዎች፣ ለፍንዳት ስራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቄሳቀሶችና ሰነዶች መያዛቸውን አስታውቋል።
ሌላ ተመሳሳይ ተልዕኮ የተሠጠው ህቡዕ ቡድንም በሱዳን ካርቱም በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ ተመሳሳይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆመው መግለጫው፤ መረጃውን ቀድሞ ያገኘውና ክትትል ሲያደርግ የቆየው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የግንኙነት መረቡን ለመበጣጠስ እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝም ከሱዳን የመረጃና የደህንነት ተቋም ጋር በቅንጅት መሰራቱን ጠቁሟል።
ለህቡዕ የሽብር ቡድኑ መሪ ከውጭ አመራር የሚሰጠው ኑሮውን በስውዲን ያደረገው አህመድ እስማኤል የተባለ ግለሰብ ሲሆን፤ የሽብር ጥቃት ዕቅድ በማውጣትና ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በአዲስ አበባ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኤምባሲ የደህንነት መረጃዎች እንዲሰበሰቡ አቅጣጫ ሲሰጥ ቆይቷል። የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በህቡዕ የተደራጀው የሽብር ቡድን እንቅስቃሴን በተመለከተ ከአውሮፓ፣አፍሪካና እስያ የመረጃና ደህነንት ተቋማት ጋር የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥና ብርቱ ክትትል በማድረግ አህመድ እስማኤል በስውዲን ሀገር በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ሊቃጣ የነበረው የሽብር ጥቃት የከሸፈው አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከውጪና ከሀገር ውስጥ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ጋር የተቀናጀ ክትትልና የመረጃ ልውውጥ በማደረጉ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀነባበረው የሽብር ሴራ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያና ከስዊድን በተጨማሪ በሌሎች ሀገራትም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክቷል።
ሌሎች ከሴራው ጋር ግንኙነት ያለቸውና በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ 21 ተጠርጣሪ ግለሰቦችንም በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን መግለጫው አመልክቷል። በአገር ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ የሽብር ቡድኖቹ አባላትና ግብረ አበሮቻቸው በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርምራ ቢሮ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እንደሚገኝ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ አባላትን በመመለመል፣ የሽብር እቅድ በማውጣትና ኢላማዎችን በመለየት አዲስ አበባና ሱዳን በሚገኙት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲዎች ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም ስምሪት ወስደው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበሩ ተጠርጣሪ የሽብር ቡድኖቹ አባላት እንዲያዙ ሲደረግ፤ህብረተሰቡ ያደረገው ተሳትፎም ከፍተኛ እንደነበር ጠቁሟል።
በቀጣይም ህዝባችን ይሄን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደረግና የተለየ ነገር ሲመለከትም በአካባቢው ላለ የፀጥታ አካል መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አገልግሉት መስሪያ ቤቱ ጥሪ ያቀርባል።(EBC)