ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ!
ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በአገራችን ውስጥ እስካሁን የተካደው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ተገቢውን እውቅና እንዲያገኝ፣ ዜግነት የፖለቲካችን ማዕከል እንዲሆን የሚያስችል መሰረታዊ የትርክት ለውጥና የመዋቅር ክለሳ እንዲደረግ በርካታ ጥሪዎችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ለአገራችችን የፖለቲካ ምስቅልቅል(crisis) መነሻ የሆነው የጥላቻ ትርክት በሕገ-መንግስትና በመዋቅሮች መስረፅ ምክንያት መሆናቸውን በመገንዘብ ሕዝባችን ከባድ መስዋዕትነትን የጠየቀ የለውጥ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህም ቀላል የማይባሉ እመርታዎችን ያስመዘገበ ቢሆንም በዋናነት የአፋኙ ስርዓት አካልና ወራሽ የሆነ ስብስብ የሕዝባችንን ቅን ልቦና ባጎደፈ መልኩ የፅንፈኝነት ባህሪውን ለጊዜው ደብቆና ስሙን ብቻ ቀይሮ የሕዝባችንን የለውጥ ሂደት አግቶት ይገኛል።
የአማራ ሕዝብና አብን በትሕነግ ላይ የነበረው አቋም የተፈተሸ፣ የጠራና የነጠረ ስለመሆኑ አስረጅ አያስፈልገውም። አብን ከሁለት አመታት በፊት ትሕነግ ሽብርተኛ ድርጅት መሆኑን በመጥቀስ ከሰላማዊ የፖለቲካ ፖርቲዎች ዝርዝር እንዲሰረዝና ጉዳዩ በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ እንዲታይ ማሳሰቡ ይታወሳል።
በወቅቱ መንግስት ከትሕነግ ጋር አብሮ በአንድ ጥምረት ውስጥ ሆኖ የሚሰራበት ነበር። አብዛኛው የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች በአብን መግለጫ ቢያንስ ተደናግጠው እንደነበር የሚታወስ ኃቅ ነው።
አብን የአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ ንቅናቄ አካል እንደመሆኑ መጠን ዝቅተኛው የፖለቲካ ስምሪቱ አገራችን በፅንፈኛ ኃይሎች ቅንጅት እጅ ዳግም እንዳትወድቅ መከላከል ነው። የኮሮና (COVID-19) ወረርሽኝ ስጋትን ተከትሎ በአገራዊ የምርጫ መርኃ ግብር ላይ በታየው የፖለቲካ ችግር ወቅት የወሰድነው አቋም አብን ኢትዮጵያን በተመለከተ ላለው የማያወላዳ አቋም አይነተኛ ጠቋሚ መሆኑ አያከራክርም።
ድርጅታችን አብን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ሊፈታ የሚችለው መሰረታዊ ለውጦችን በማድረግ እንጅ በስምና በቅብ ለውጥ ሊሆን እንደማይችል በመረዳት አገራችን በሽግግር መንግስት ምስረታ ሳይሆን በሽግግር ጊዜ ምዕራፍ ማለፍ እንዳለባት አሳውቆ ነበር።
በተያያዘ ሁኔታ በሽግግር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ እልባት ማስገኘት የሚችሉ አንኳር የለውጥ ተግባራት መፈፀም እንዳለባቸው ገልፆ ጥሪ ማስተላለፉም ይታወሳል። ነገር ግን በጥሬ የስልጣን ግብግብና በጥላቻ ባሕል የተቃኘው የአገራችን አጠቃላይ የፖለቲካ ስምሪት ዘላቂ ተግዳሮት ሆኖ በመቀጠሉ ተፈላጊው ለውጥ እውን ሊሆን ካለመቻሉም በላይ በሕዝባችን ላይ ተከታታይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት ጥቃቶች ተፈፅመዋል።
የዜሮ ድምር የፖለቲካ ዘይቤን የቀጠለ ሲሆን በአገራዊ መግባባትና ትብበር መሰራት ያለባቸውን ጉዳዬች በፉክክርና በጥላቻ ለመፍታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሊገቱ ባለመቻላቸው ምክንያት የሕዝባችን ትግል ገና ተቀናጅቶና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገንዝበናል።
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን እና የኢትዮጵያዊነትን ትሩፋቶች በብቸኝነት ለመበየንና ለማከፋፈል የቋመጡ ጽንፈኛ መንግስታዊ አካላት አገራችንን ተፈትሾ በወደቀው የሴራ ፖለቲካቸው አዙሪት ውስጥ ለማቆየት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። በርካታው የአገራችን ክፍል የደኽንነት ስጋት ያንዣበበት ሲሆን የሕዝብ በሰላም የመንቀሳቀስም ይሁን በሕይወት የመኖር መብት በመደበኛነት አደጋ ውስጥ ይገኛል።
አብን በዚህ አመት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን የጥላቻና የሴራ ፖለቲካ ግንባር ቀደም ተጠቂ ድርጅት በሆነበት አግባብ ነው። የምርጫ ትርጉም በአንድ ቀን ውስጥ ተከፍቶ በሚዘጋ ሳጥን ውስጥ በሚጨመሩ ካርዶች የታጠረ እንዳልሆነም ይገነዘባል። በአገራችን ውስጥ ያለው የቅድመ ምርጫ መደላድል ያለበት ሁኔታ ለሕዝባችን የተሰወረ አይደለም።
በተለይም የአማራን ሕዝብ ማገት የፖለቲካ ስልት ሆኖ የቀጠለ እውነታ ነው፤ አብን የአማራ ሕዝብ ኃቀኛና የማያወላዳ እንዲሁም ጸረ-ጭቆናና ጸረ-ዘረኝነት የትግል እንቅስቃሴ በቀጥታ የወለደው ድርጅት በመሆኑ አማራን የሚፈርጁና የሚያጠቁ ጽንፈኞች ዓይናቸውን ለአፍታ እንኳን ዘወር እንደማያደርጉለት ይታወቃል።
ከአማራ ክልል ውጭ በተለይም በኦሮሚያና በቤኒሻንጎል ክልል ውስጥ ባሉት የአብን መዋቅሮችና አመራሮች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈፀሙም ቆይተዋል፤ አሁንም ቀጥለዋል። በተለይም የክልሎቹ ባለስልጣናት በሆኑ የብልፅግና ፖርቲ አባላት የሚፈፀሙ ችግሮች መሆናቸውን መነሻ በማድረግ ከፖርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ ባለመሳካቱ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻ አቅርቦ በምርመራ ላይ ይገኛል።
ጉዳዮቹ በዚህ አግባብ በሚገኙበት ሁኔታ ጭምር «የኦሮሞ ብልፅግና» ከፍተኛ አመራሮች በማኅበራዊ ድረ-ገፅ በአብን፣ በአመራሮቻችን፣ አባላቶቻችን፣ ደጋፊዎቻችን እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ድርጅቶችና አመራሮች ላይ የሐሰት፣ የአፍራሽና የጥቃት ጥሪዎችን በተደጋጋሚ እያስተላለፉ ይገኛሉ።
የብልፅግና ፖርቲ እንደተቋም በሚፈፀሙ ጥሰቶች ላይ ምንም አይነት ተጨባጭ እርምት ለማድረግ ባለመፈለግ በቀጥታ የተቀበላቸውና የአማራን ሕዝብ በተመለከተ ያለውን አቋም በምግባር፣ በድርጊትና በቸልታ አረጋግጧል።
በዛሬው ዕለትም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተደረጉ ሰልፎች በዋናነት አብንን የሚያጠለሹና የሚያወግዙ እንዲሁም በሕዝባችን ላይ ቀጣይ ስጋትን የጋረጡ ድምፆች ከፍ ብለው ሲስተጋቡ ተሰምተዋል። አብንን «ከኦነግ ሸኔ» ጋር የሚያመሳስሉ መፍክሮች ተሰምተዋል።
ስለሆነም፦
1/ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ገደብ የለሽ የፖለቲካ ነውረኝነትና የዘረኝነት እንቅስቃሴ ለመቃወም በባልደራስ ፓርቲ ተጠርቶ የነበረውን ሕዝባዊ ሰልፍ በማንአለብኝነት የከለከለ መንግስት ለፖርቲ ፍጆታ ሲሆን ሰልፍ መጥራቱና መፍቀዱ፣
2/ በሰልፉ ላይ የጥላቻና የጥቃት ጥሪዎችን ሲመሩ የነበሩት በስምና በኋላፊነት የሚታወቁ የመንግስትና የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች መሆናቸው፣
3/ በዛሬው ሰልፍ ላይ ጎልተው የተሰሙት ድምፆች የክልሉ አመራሮች በማኅበራዊ ድህረ-ገጽ ሲፅፏቸው የነበሩ ኃሳቦች ቀጥተኛ ግልባጭ መሆናቸው፣
4/ በዚህም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአጠቃላይ ያለውን የፖለቲካ አፈና ወደተሟላ እርከን ለማሸጋገር በማሰብ አብን በክልሉ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታትና በክልሉ የሚኖረውን የአማራ ሕዝብና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በጭቆና ቀንበር ስር የማቆየት ዓላማ ያነገበ ተግባር መሆኑ፣
5/ በተለይም በዛሬው ሰልፍ ላይ በአማራ ሕዝብ ላይ በተደጋጋሚ የዘር ፍጅት ለመፈፀም ጽንፈኛ ኃይሎች መንደርደሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት «ነፍጠኛ» የሚለው ቃል በሰፊው ሲገለፅ የነበረና በግልፅም «ነፍጠኛ ይውጣ» የሚል ኃሳብ ሲሰማ የነበረ መሆኑ፣
6/ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ኃላፊነት የጎደላቸው ጽንፈኛ አመራሮች በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት ሽፋን በመስጠትና በቀጥታ በመሳተፍ እንደሚያስፈፅሙ የተረጋገጠ ጉዳይ ሆኖ እያለ በታየው ደረጃ የተላለፈውን የጥላቻና የጥቃት ጥሪ የመንግስት ሚዲያዎች መዘገባቸው እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም እርምት መስጠት እየተገባቸው ቡራኬ መስጠታቸው እጅግ አሳዛኝ የሆነና በቀጣዩ የአገራችን የፖለቲካ ኺደት ላይም ከፍተኛ ስጋትን እንደሚፈጥር መረዳት ይቻላል።
በአጠቃላይ የአገራችንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተለየ ፖለቲካዊ እይታ የማስተናገድ ዝንባሌና ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ በመንግስት በኩል እየታየ ያለው አቋምና አፍራሽ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም እየጠየቅን የአብን የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጉዳዬን በቀጥታ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በግልባጭ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ አሳውቋል።
በመጨረሻም መላው ኢትዮጵያውያን በተለይም የአማራ ሕዝብ ዛሬ የተስተጋባው የጥላቻና ዘር ፍጅት ቅስቀሳ በውጤት ደረጃ አገርና ሕዝብን ለኅልውና አደጋ የሚጥል መሆኑን በመረዳት የተፈፀመውን አስነዋሪ ድርጊት በጽኑ እንዲያወግዝና አብን ከሚያደርጋቸው የፍትኅ፣ እኩልነትና ነፃነት ትግሎች ጎን እንዲሰለፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የሴራ ፖለቲካ ምዕራፍ የሚዘጋበት፣ የጥላቻና የፍረጃ ፖለቲካ ላንቃ የሚዘጋበት ጊዜው አሁን ነው!
ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ!