Connect with us

አሁንስ በዛ!

አሁንስ በዛ!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

አሁንስ በዛ!

አሁንስ በዛ!

(ፋሲል የኔዓለም ~ ጋዜጠኛ)

ለታላቋ ኢትዮጵያ ተብሎ ዝም ቢባል አሁንስ በዛ። ታዬ ደንደዓ፣ የብልጽግናው ባለስልጣን፣ ስለማያውቀው ታሪክ እየጻፈ የአብይ አህመድን መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው ነው።  አብይ አህመድ ህወሃት የቀደዳትን ኢትዮጵያን እንቅልፉን አጥቶ ለመስፋት ይሞከራል፤ ታዬ ደንደዓና መሰሎቹ ደግሞ በጎን ይተረትራሉ። 

አብይ አህመድን ለማመስገን የኢትዮጵያን ታሪክ ማጠልሸት አይስፈልግም። አብይ በተደጋጋሚ እንዳለው ነው፣ ኢትዮጵያ ከሱ በፊት በነበሩ መሪዎች እየተገነባች እዚህ የደረሰች አገር ናት። 

ታዬ ስለ ቀድሞው ጠ/ሚ አክሊ ሃብተወልድ  የተሳሳተ ታሪክ ጻፈ። በዚህ ስህተቱ ሳያፍር ቀጥሎ ደግሞ የዛግዌንና የዶ/ር አብይን መንግስት አወዳድሮ ሌላ የማይሆን ታሪክ ጫረ። “ሞኝ  ባያፍር፣ የሞኝ ዘመድ ያፍር” ነው ነገሩ። 

ታዬ ከዛገዌ መጨረሻ እስከ አጼ ሃይለስላሴ ዘመን የነበረውን የነገስታቱን ዘመን ምንም ስራ እንዳልሰራ አድርጎ ረገመው። በአጭሩ የደርግን ፕሮፓጋንዳ ደገመው። አላማው እነሱ የአማራ መንግስት የሚሉት የሶሎሞናዊው መንግስት ምንም እንዳልሰራ በማሳየት አማራን መወረፍ  ነው። 

አላዋቂነት የወለደው ድፍረትና ስልጣን የወለደው ትዕቢት ታዬን እያቅበዘበዘው ነው።

 ከዛገዌ በኋላ ሸዋ ላይ የተመሰረተው ታላቅ ስልጣኔ በማን እንደፈረሰ ታዬ የሚያውቅ አይመስልም። አክሱም፣ ዛግዌና የሶሎሞናዊው ስርወ መንግስት ስልጣኔዎች የማይነጣጠሉ ተያያዥነትና ተደጋጋፊነት ያላቸው የኢትዮጵያ ታሪኮች መሆናቸውን ለማወቅ፣ የልብ ብርሃን ያስፈልጋል። 

 ደግሞ የታሪክ ሂሳብ ማወራረድ ውስጥ ከተገባ በማን እንደሚከፋ ታዬና ቢጤዎቹ ያወቁትም ያሰቡበትም አይመስልም። ደርግ እንዳስወራውና ታዬ እንደደገመው ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ነገስታት ለእደ ጥበብ ሰዎች አክብሮት ነበራቸው። በሄዱበት ሁሉ ይዘዋቸው ከሚዞሩ ሰዎች መካከል የእደ ጥበብ ባለሙያዎች የገኙበት ነበር። የኢትዮጵያ ነገስትታና የሙስሊም ነጋዴዎች ቁርኝት በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኝ ነው። ይህ ሲባል እንከን አልነበረም ማለት አይደለም። እንኳንስ ትናንት ዛሬም ብዙ እንከኖች አሉ። 

የመካከለኛው ዘመን ነገስታት የሰሩትን ስራ  ለማወቅ እኮ የዛሬዋን አዲስ አበባ ቆፈር ቆፈር ማድረግ ነው። አንቶን ዲ አባዲ የተባለው ፈረንሳዊው አሳሽ  ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የቆመበት ቦታ ላይ የነበረውን በመካከለኛው ዘመን የተሰራውን የቤተክርስቲያን ፍርስራሽ አይቶ አግራሞቱን እንዲህ ሲል ገልጾ እንደነበር Abba Emile Foucher እንዲህ ሲል ጽፏል፦

“ Who could have been the architect of such a building? … People who constructed such a building with well cut stone, linked with mere clay, must have been of another type of civilizations.”

 የረርን፣ በራራን፣ ፈጠጋርን፣ ጋሞን፣ ጉራጌን በአጠቃላይ የሸዋን የጥንት ታሪክ ያጠና ሰው፣ የኢትዮጵያ ነገስታት የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነት ለማጥናት እየዘመቱ፣ በጎን ደግሞ ታላቅ ስልጣኔ ገንብተው እንደነበር ይረዳል። ያው እነዚህ ስልጣኔዎች እንዴት እና በእነማን እንደፈረሱ ዝርዝር ውስጥ አልገባም። ታሪካችን ስለሆነ ከመቀበልና ወደፊት ከመጓዝ ውጭ በታሪክ እኘኘ ስንል አንገኝም። እንደ ታዬ አይነት አምቦጫራቂዎች ከበዙ ግን እውነቱን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም። 

ታዬ የዛግዌ መንግስትን ከ አብይ አህመድ መንግስት ጋር ሲያነጻጻር በተዘዋዋሪ መንገድ የአብይን መንግስት የኦሮሞ መንግስት አድርገን እንድንቀበለው እየነገረን ነው። አብይን የሚደግፈው አብዛኛው ሰው የአብይን መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት እንጅ የኦሮሞ መንግስት አድርጎ አያየውም። ከተሳሳትኩ እታረማለሁ። እንዲህ ከሆነማ አንዳንዶች  “ተረኝነት አለ ” የሚሉት ትክክል ነው ማለት ነው።

አብይ አህመድ የራሱን መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት እንጅ የኦሮሞ መንግስት ብሎ ሲጠራው ወይም ተራው የኦሮሞ ነው በሚል አስተሳሰብ ስልጣን እንደያዘ ሲናገር ሰምቼ አላውቅም።  አብይን የደገፉት ሰዎች ሁሉ አብይን በኢትዮጵያዊነት እንጅ በኦሮሞነት የሚስሉትም አይመስለኝም። አብይ ከኦሮሞ ነገድ ቢወጣም፣ ስልጣን የያዘው በኢትዮጵያዊነቱ እንጅ የስልጣን ተራው የኦሮሞ ስለሆነ አይደለም። ስልጣን በብሄር ተራ ተከፋፍሎ ከሆነማ  ኦሮሞ በየትኛው የእጣ ድልድል ነው ከሶማሊ፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላ፣  ከአማራ ወይም ከጉራጌ ቀድሞ ስልጣን የያዘው? እስኪ እጣው መቼ እንደወጣና እንዴት እንደወጣ ንገሩን?

የእነ ታዬ አመለካከት በጣም አደገኛ የሚሆነው፣ በምርጫ ቢሸነፉ፣ እንደ ህወሃቶች ሁሉ፣ “ኦሮሞ መሪ ካልሆነ ወይም በእጅ አዙር ካልገዛ፣ ስልጣን አንለቅም” የሚሉ መሆናቸው ነው። ስልጣንን በብሄር መንጽር ማየት ኢትዮጵያዊነትን ማዳከም ብቻ ሳይሆን፣ የብሄር አምባገነንነትም ይፈጥራል።  ዋ! 

የታዬ ደንደዓ አስተሳሰብ ያላቸው ብዙ የኦሮሞ ብሄርተኞች መንግስት ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል። ዶ/ር አብይ አህመድ ከእነዚህ በብሄር ከሚያስቡ ሰዎች በላይ ከፍ ብሎ የሚበር ስልጡን ሰው እንደሆነ በግሌ አስባለሁ። ስለኢትዮጵያ ታሪክ ያለው አመለካከትም ከብዙዎቹ የተለየና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ነው። አብይ እንደነ ታዬ ደንደዓ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አያላግጥም። በአላዋቂነት ድፍረትም ሆነ በስልጣን ግብዝነት የማያውቀውን ታሪክ ሲዘባርቅ ሰምቼው አላውቅም። አብይ ንባብ ከአላዋቂነት ድፍረት ነጻ ያወጣው ሰው ነው። 

 የኦሮሞ ብልጽግና ውስጥ እንደ አብይ አህመድ ንባብ ነጻ ያወጣቸው አርቀው የሚያዩ ስንት ሰዎች አሉ?  ስለአንድ አብይ ብለን የኦሮሞ ብልጽግናን ሁሉ ይቅር እንበለው ወይስ ስለኦሮሞ ብልጽግና ብለን አንድ አብይ አህመድን እንርገመው የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ከባድ እየሆነ ነው።

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top