ቡስካን እንደ ሜዳ፤ ወደ ሀመሩ የቡስካ ተራራው አቡነ ሙሴ ጸሊም ገዳም
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የቡስካ ተራራ አናት አደርኩ ሲል በሀመር ያደረገውን ቆይታ የመጨረሻ ክፍል እንዲህ ተርኮታል፡፡ በቡስካ ተራራ አናት የሚገኘውን የአቡነ ሙሴ ጸሊም ገዳምም እንዲህ ያስተዋውቀናል፡፡)
(ከሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ)
ነፋስ ሲዘንብ አድሯል፡፡ ብርዱ ከባድ ነው፡፡ የሀመርን ምድር ቁልቁል አየዋለሁ፡፡ ቡስካ ተራራ አናት ቆሜያለሁ፡፡ ገናናው ተራራ ከሀመር አይነጠልም፡፡ ሀመር የቀደመ ታሪኩ ካለሁበት ይቆራኛል፡፡ ቡስካ ማለት መሰብሰብ ማለት ነው፡፡ ሀመር እዚህ ነበር ተሰብስቦ የኖረው፤ የወረደውም ከዚህ ነው፡፡
ቡስካ ረዥም ሰንሰለት ነው፡፡ ደግሞ ደጋ፤ ብርዱን ቀኑ ተጋምሶም አያቆም፡፡ የወይራው ዛፍ ዥዋዥዌ የሚያሰማውን ድምጽ ንፋስ ይዞ ከየአቅጣጫው ያመጣዋል፡፡ እድሜ ጠገብ እጽዋቱ የተራራው ገላ ሸፍነውታል፡፡
ጥቅጥቅ ደን ነው፡፡ ቁልቁል ኦሞ ድረስ የሚመለከት፡፡ የአካባቢው እስትንፋስ ከዚህ የሚንደረደረው ንጹህ አየር ነው፡፡ እዚህ ደግሞ የቡስካ አቡነ ሙሴ ጸሊም ገዳም አለ፡፡ ያደርኩት ገዳሙ ጋር ነው፡፡
የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት፤ ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ህንጻ ቤተ ክርስቲያን አሰሪ ኮሚቴ የሚባለው አድራሻው አዲስ አበባ ነው፡፡ ህይወቱ ግን አርብቶ አደሩ የጠረፉ የሀገሬ ሰው ጋር፡፡ እነኚህ በጎ ፍቃደኞች በደቡብ ኦሞ ካሰሯቸው ከአርባ በላይ ቤተ ክርስቲያናት አንዱ ይህ የቡስካ አቡነ ሙሴ ጸሊም ገዳም አንዱ ነው፡፡
የሀመር ልጆች የአብነት ትምህርት ጀምረዋል፡፡ ገዳሙን በስስት ያዮታል፡፡ የገዳሙ እንግዳ እንግዳቸው ነው፡፡ ከምንም በላይ ቤተ ክርስቲያኗ ብዙ አደጋ ተጋርጦበት፣ ተፈጥሮው ለመውደም የተቃረበውን ቡስካ ተራራ እየታደገችው ነው፡፡ ቡስካ ታች ወርዶ ህይወቱን ለሚገፋው አርብቶ አደር የብዝሃ ህይወት ባንኩ ነው፡፡ ከተራራው አናት ያረፈችው ገዳም ተራራ የማልማት ስራውን ጠንክራበታለች፡፡
ሙሴ ጸሊም በሀገራችን የትም ሰምቼው የማላውቀው ገዳም ነው፡፡ በሀመር ብቻ የሚገኝ፡፡ ጻዲቁ ሙሴ ኢትዮጵያዊ ጥቁር ነው፡፡ በሀገረ ግብጽ የኖረ፤ በግብጻውያን ኦርቶዶክሶች ዘንድ ግዙፍ የቅድስና ስፍራ ያለው፡፡ በኢትዮጵያ በስሙ የተገደመው ገዳምና ቤተ ክርስቲያን በሚገኝበት ቡስካ በመምጣቴ ደስ ብሎኛል፡፡ ቡስካ የሀመር የታሪክ መነሻ ብቻ አይደለም፤ የእምነትና የተፈጥሮ ጥበቃ ባህል ማዕከልም ይሆናል፡፡ ይህ የሙሴ ጸሊም ገዳም ህንጻ ቤተ ክርስቲያን የፊታችን የካቲት አስራ አራት ቀን በድምቀት እንደሚመረቅ ሰምቻለሁ፡፡ ሀመሮች ለዚያ ቀን እየተዘጋጁ መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡ ከሻንቆ እስከ ቡስካ አናት ይሄንን ቀን ናፍቀውታል፡፡ የዲመካዎች ጉጉት ነው፡፡ እኔም እመኛለሁ፤ ያኔ አብሬ ከሀመሮች ጋር ከሆንኩ ያየሁትን እነግራችኋለሁ፡፡
ለፎቶው ብሩክ አሰፋና በሪሁን ታደለን አመሰግናለሁ፡፡