የአማራ ብዙኃን-የብዝኃነት መንገድ፤ደግሞም የአንድነት ሸማኔ፡፡አህዳዊ ከሚሉት ቀድሞ ብዝኃነትን ያስተናገደ ሚዲያ፤
ከሄኖክ ስዩም
የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት አዲስ አበባ ቀጥታ ስቱዲዮ ምረቃ ላይ ታድሜያለሁ፡፡ አዳራሹ ጥቂት ሰዎች ብቻ ተገኝተውበታል፡፡ አንዱ ነኝ፤ ይኽ በእድሜ ትንሽ በተግባር አንጋፋ የሆነ ሚዲያ የሰራው ይወደሳል፡፡ ዓይኔን ስልክ በራያና በሁመራ ግንባሮች ከሠራዊቱ ጋር ዘምተው የነበሩ የሚዲያው ባለሙያዎችን ተመለከትሁ፡፡ ደግሞም በመድረኩ በህግ ማስከበር ዘመቻው የሚዲያው ቀዳሚ ሚና ይወደስ ነበር፡፡
የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ የተቋሙን ጉዞ ዛሬ ድረስ እንደምን እንደደረሰ ለታዳሚው ገለጹ፡፡ የክልሉ መንግሥትና የሥራ ኃላፊዎች ከትናንት እስከ ዛሬ ለዚህ የመብቃቱ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸው አመሰገኑ፤ ቁርጠኛ የተቋሙ ቤተሰቦችንም ለዚህ መድረስ መስዋዕት መክፈልን ጭምር ሳይሸሹ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመሰገኑ፡፡
አንዱ የመንግስት አመራር እንዲህ አሉ፤ አማራ ብዙሃን ትህነግን የደፈረው ጥርሷ ሲረግፍ አይደለም፤ ገና ጥርስ እያላትና ሁሉም በሚፈራት ሰዓት የፈጸመችውን ለምን ያለ? የጎንደሩንና የባህር ዳሩን ሰልፍ ከነ አሰቃቂ ጭፍጨፋው የዘገበ፣ ቀድሞ የነቃ ሚዲያ ነው፤ ሲሉ የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ምስክርነታቸውን ሰጡ፡፡
አማራ ብዙሃን ብዙ የሚወደስበት ነገር አለ፡፡ ብዙ ነገር ቢቀረውም፤ ሁሉም ነገር በሚቀራቸው ሚዲያዎች መካከል እንደ ጧፍ ጨለማውን ያበራ ባለውለታ ነው፡፡ እርግጥ ነው ያሙታል፡፡ አቶ ዘርዓይ አስገዶምም አሃዳዊ ብለው ብሮድካስት ባለስልጣንን ሲመሩ አምተውት ነበር፤ ከእሷቸው በርሃ ለብሔር መብት ታግያለሁ ከሚሉት በላይ ግን ለብዝሃ ቋንቋ ቀዳሚው ሚዲያ ነበር፡፡
አሁን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ብሔረሰብ ቋንቋዎች ተደራሽ ሆኗል፡፡ ልዩነትን የሚጠየፍ ሚዲያ አይደለም፡፡ ደግሞ በዚህ የአዲስ አበባ ስቱዲዮ ምረቃ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርና የሚዲያው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አገኘሁ ተሻገር በሌሎች ቋንቋዎች ሊመጣ እንደሆነ አብስረዋል፡፡
አማራ ብዙሃን መንገድ ላይ ነው፡፡ አፋርኛ፣ ሱማሊኛ፣ አረብኛና ትግርኛ ቋንቋዎችን ቋንቋው አድርጎ ስርጭቱን ይጀምራል፡፡ አንድ ነው እያሉ በአንድ ቋንቋ የሚያሙትን ብዙ ነኝና ብዝሃነትን አከብራለሁ ብሎ የሚነግራቸው በብዙ ቋንቋ ነው፡፡
ከሀገር ውስጥ ሚዲያ ጋር በመተባበር ከዓለም ሚዲያ ጋር በመፎካከር ሩቅ ስለመጓዝ አስቡ ሲል ሙሓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በመርሐ ግብሩ ላይ ሀሳቡን ሰንዝሯል፡፡ የሚዲያው የቦርድ ሰብሳቢም ሀሳቡን ሀሳባችን አድርገን እየሰራን ነው ሲሉ ሩቅ ስለመጓዝ ውጥናቸው ገልጸዋል፡፡ በሀገራችን ዋና ዋና ከተሞች ዘጋቢ እንደሚኖረው የተናገሩት ክቡር አቶ አገኘሁ፤ ደግሞም በዓለም ዋና ዋና ከተሞች ጭምር አማራ ብዙሃን ዘጋቢ እንደሚኖረውና በአጭር ጊዜ ተወዳዳሪነቱን ወደ አህጉር አቀፍ አቅም እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡
የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአማራ ብዙሃን የነጻነት ዘገባ ጋር ስማቸው የሚጠራ የሙያ ነጻነቱ አባት የሚባሉ ናቸው፡፡ የክልሉን መሪዎች ሳይቀር የሚሞግት ተክለ ቁመና እንዲኖረው በማድረግም ይመሰገናሉ፤ እሳቸውም የአማራን ህዝብ ከፍታ በሚመጥን መልኩ ሚዲያው ራሱን አብቅቶ እንዲሰራና እንዳይወርድ ጭምር አሳስበዋል፡፡
የአማራ ብዙሃን አዲስ አበባ ስቱዲዮ መንደርደሪያ እንጂ የማቆሚያው ሪቫን አይደለም፡፡ በእኔ ምልከታ ሚዲያው የብዝሃነት መንገድ ነው፡፡ ልዩነት ይስተናገድበታል፡፡ ከሀገሪቱ ብሔራዊ ጣቢ ቀጥሎ ብዙ ቋንቋን የሚጠቀም፤ ገና ብዙ ቋንቋን መጠቀም የሚሻ የብዝሃነት አክባሪ ነው፡፡ ደግሞም የአንድነት ሸማኔ፤ ልዩነታችን የሚፈጥረውን አንድ ውበት የሚያሳይ፤ የአቶ ገዱን ሀሳብ እኔም እጋራዋለኹ፤ “ከከፍታችሁ እንዳትወርዱ!”