Connect with us

<<ኢትዮጵያ ለምን?>>

ባህልና ታሪክ

<<ኢትዮጵያ ለምን?>>

<<ኢትዮጵያ ለምን?>>

-የሚስጥር ማህበራት ኢትዮጵያን ለምን አጥብቀው ይፈልጓታል?

-የ“መጽሃፈ ራሴላስ” ምስጢሮች!

-አብርሆት/ኢንላይትመንት ምንድን ነው?

“አብርሆት” የሚለው ቃል “ብርሀን” ከሚለው ስርወ ቃል ተሸሞንሙኖ የተገኘ ውብ ቀል ነው፡፡ እኔ በግሌ ቃሉን እነዲሁ እወደዋለሁ፡፡ ብርሃን ማግኘት፣ መታወቅ፣ በገለጥ፣ ጸሃይ ላይ መውጣት፣ ይፋ ማድረግ የሚል አንድምታ አለው፡፡ “ይሄኮ ምስጢር ሳይሆን ጸሃይ ሞቀው እውነታ ነው” እንል የለ? ለመሆኑ የሚገለጠው፣ ይፋ የሚሆነው፣  ብርሃን የሚያገኘው ምን አይነት ጉዳይ ነው? መቼም ቀድሞውንም ግልጽ ሆነ ነገር በድጋሜ አይገለጥም፡፡ የሚገለጠው ተደብቆ፣ ተሰውሮ፣ ተዳፍኖ የነበረ ነገር ነው፡፡ 

ለምሳሌ አንድ ነገር በቅጡ ሳይገባን ሲቀር “አብራራልኝ” እንላለለን፡፡ ፍንትው አድረግልኝ፣ አብራራልኝ፣ ግልጽ አድርግልኝ እንደማለት ነው፡፡ ነጮቹ “illuminate me!” እንደሚሉት፡፡ “ኢሉሚናቲ” ያልኩ መስላል አደል? እሱን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡ 

አብርሆት/ኢንላይትመንት መነሻው ያው ያው አውሮፓ ነው፡፡ የመካከለኛው ክፍለ ዘመን ተሃድሶ (ሬኔሳንስ) መዳረሻው አብርሆት ነበር፡፡ የዛሬ አምስት መቶ አመት ገደማ በጣሊያኗ ፍሎረንስ ከተማ በስዕል ተሃድሶ (እዚህ ጋር የኢትዮጵያ ህዳሴ፣ ህዳሴ ግድብ የምልለው ነገር ትዝ አለኝ) የተጀመረውና በሪዝኒንግ (ምክነያታዊነት) ዘመቻ ማለስለሻ ዘይት እየተፍታታ፣ የሳይንስ አቢዮትን፣ የምድር አሰሳን፣ ምርምርን፣ ፈጠራን አስከትሎ ወደ ኤጅ ኦፍ ሪዝኒንግ የገሰገሰው የአውሮፓ ተሃድሶ ጉዞ አለምን ሙሉ በሙሉ ቀይሯል ማለት ይቻለል፡፡ 

ይሄንን ጦማር ከምጽፍበት ኮምፒውተር ጀምሮ ሰሞኑን እያወዛገቡ እስካሉት ሰው አልባ ተዋጊ ድሮኖች ድረስ ሁሉም የተሃድሶው ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ታዲያ ተሃድሶው ቴክኖሎጂያዊ ብቻ አይደለም፡፡ ፍልስፍናዊ፣ መዋቅራዊ፣ ስነ ልቦናዊና ህቡዕም ጭምር እንጂ፡፡

አብርሆት ስንል በአይን የማይታየውን ነባር አውነታ (Objective truth) ፈልጎ ማግኘትና ማየት መቻል ነው፡፡ “ኤጅ ኦፍ ሪዝኒንግ (የምክነያታዊነት ዘመን)” ለምክነያታዊነት ራስን መስገዛት፣ የነገሮችን እውነተኛ ምንነት ማጠየቅ ማለት ነው ብሎ በደፈናው መበየን ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን “አብርሆት” ለብዙዎች በቀላሉ የማይደረሱ ምስጢሮች ያሉት ሀሰብ ነው፡፡ ተሀድሶ መነሻ ነው፡፡ ምክነያታዊነት መስፈንጠሪያ፣ አብርሆት ደግሞ መዳረሻ ናቸው፡፡ 

ለመሆኑ የት ነው ሊደረስ የታሰበው? መንገደኞቹ ወደ “ዩቶፒያ” ነው ይላሉ፡፡ ልብ በሉልኝ “ኢትዮፒያ” አላልኩም! ወደ “ዩቶፒያ”! ለመሆኑ ዩቶፒያ የት ናት? እንኳን እኔ ለብዙ ሺህ አመታት እሷን ለማግኘት የኳተኑት ከግሪካውን ጀመሮ እስከ አውሮፓውያን አሳሾችም አላገኟት፡፡ ደግሞኮ አሁንም እየፈለጓት ነው፡፡

ብቻ “ዩቶፒያ” ማለት ሁሉ ሙሉ፣ ሁሉ ዝግጁ ሆነባት፣ ሀዘን መከራ የማይታወቅባት፣ ደስታ የሰፈፈባት ተምኔታዊ ምድር ማለት ነው፡፡ ‹ተምኔታዊ› የሚለው ቃል ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም ፍለጋው ግን አላበቃም፡፡ ምናልባት “ዩቶፒያ” እና “ኢትዮጵያ” የሚያገኛኛቸው ቋጠሮ ይኖር ይሆን? ‹ዩቶፒያ› የሚለውን ቃል  “ገነት” የሚለው ሀሳብ በገደምዳሜ ሊተካው ይችላል፡፡ “ገነት”?! ለመሆኑ ሀገራችንን አንዳንዶች ‹ገነት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበረች›፣ ‹አዳምና ሄዋን ኢትዮጵያ ወስጥ ነበሩ›፣ ‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች›፣ ‹ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት ነች› ፣ ‹ኢትዮጵያ ምድራዊ ገነት ነች› የሚሉት ከየት አምጥተውት ነው? ኢትዮጵያ አሁን ከገነት ይልቅ ለሲኦል አትቀርብምና ነው? የሚል አይጠፋም፡፡ እውነት አለው፡፡

ዳሩ ግን ልንገምተው ከምንችለው በላይ የተሰወረብን ምስጢር ያለ ይመስለኛል፡፡ ያልተብራራልን፣ የተሰወረብን፣ አብርሆት የሚያሻን ጉዳይ፡፡ መጽሀፈ ራሴላስ በአመስጥሮ ኢትዮጵያን የገነት ምሳሌ፣ ልዑል ራሤላስን የአብርሆት መንገደኛ አድርጎ ጭላንጭል ምስጢር አጮልቀን እንድናይ ጋብዞናል፡፡ 

ከተጻፈ 260 አመቱን የደፈነ ቢሆንም ዛሬም በአውሮፓ የሬኔሰንስ የፍካት ዘመን ውስጥ ከተጻፉ የምንጊዜም ምርጥ መጽሀፎች አንዱ ነው፡፡ ጸሃፊው ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን እንደ ሌላኛው ዝነኛ እንግሊዛዊ ጸሀፊ ቶማስ ሙር “ዩቶጲያ”ን አግኝቻታለሁ የሚል መስላል፡፡ እሯ!…ኢትዮጵያ ውስጥ? እንዴት ሆኖ? በተከታታይ የምናየው ይሆናል፡፡

መቼም የፍሪማሶኖችና የሌሎችም አያሌ የሚስጥር ማህበራት መነሻ ነጥብ ሰለሞን መሆኑ እሙን ነው፡፡ ንጉሱ ሰለሞን፡፡ የኛው ነገስታት የዘር ሀረግ መነሻ ነቁጥ፡፡ የሰለሞናዊ ዳይናስቲ ምንጭ፡፡ በጥበቡ ዝና የኛዋን ንግስት ጨምሮ የአለም ነገስታትና ንግስታት አይን እየሩሳሌም ላይ እንዲያርፍ ያደረገው ሰለሞን፡፡ ለሙሴ ጽላት ማረፊያ የሚሆነውን ታለቁን ቤተ መቅደስ ያነጸው ታላቁ ገንቢ፡፡ በአለም ላይ እነደሱ አይነት ንጉስ ከእሱም በፊት ከእርሱም በኋላ አልተነሳም የተባለለት፡፡

ክርስቶስ ራሱ ከሰለሞን የሚበልጥ በዚህ አለ ብሎ የመሰከረለት ጥበበኛ ንጉስ፡፡ በዚህ ጥቅስ መሰረት በጥበብ ተዋረድ ከክርስቶስ ቀጥሎ ንጉስ ሰለሞን ነው ማለት ነው፡፡

በክብረ ነገስቱ ትረካ አማካኝነት ንግስተ ሳባ ከሰለሞን የወለደችው ልጅ ስሙ “ምኒሊክ” ነው፡፡ ምኒሊክ ማለት “የጥበብ ልጅ” ማለት ነው፡፡ ወይም በተዘዋዋሪ “የሰለሞን ልጅ” አንደማለት ነው፡፡ በተለይ በምስጢር ማህበራት ዘንድ ሰለሞንን ራሱን እንደ ጥበብ መጥራት ተለመደ ነገር ነው፡፡ ምናልባት ከኢትዮጵያውያን ወርሰውት ይሆናል፡፡ የሰለሞን ስርወ መንግስት መስራች ቀዳማዊ ምኒሊክ ነው፡፡

ከዚያ በኋላ ለሶስት ሺህ አመታት “የጥበብ ልጆች” ኢትዮጵያን ነጻ ምድር አድርገው መርተዋታል፡፡ እስራኤል ስትጠፋም “እስራኤል አልጠፋችም፣ የጠፋንም እኛ፣ ያለንም እኛ” ብለው ዘልቀዋል፡፡ ዳግማዊት እሩሳሌምንም ላሊበላ ላይ አንጸዋል፡፡ ሰለሞን ለሙሴ ጽላት የሰራው ቤተ መቅደስ በባቢሎኖች ቢፈርስም ወራሾቹ አክሱም ላይ ሌላ ቤተ መቅደስ ሰርተውለታል፡፡

“እስራኤል” ማለት በእብራይስጥ “የእግዚአብሄር ወታደር” ማለት ነው፡፡ እስራኤል ስትበተን ሰለሞናውያን ነገስተት “እግዚአብሄር ወታደሮች ነነ” ብለው ሮማውያንንና በኋላም ቱርኮችን ከቅድስቲቷ ምድር ለማስወጣት እቅድ ነበራቸው፡፡ “ታጠቅ ብሎ ፈረስ፣ ካሳ ብሎ ስም፤ አርብ አርብ ይሸበራል እሩሳሌም” መባሉ ብዙ ምስጢር አለው፡፡ “እኔ መዩ ቱርክ ባይ፣ የምሸሽ ነኝ ወይ” ሲሉም እስከ ሜዲትራኒያን ማዶ ድረስ ይሰማ ነበር፡፡ 

እነዚህ ነገስታት ክብር መጠሪያቸው “ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ” ነበር፡፡ ያው የይሁዳው ነገድ አሸናፊ አንበሳ ማለት ነው፡፡ ምልክታቸውም የዳዊት ኮከብ ወይም የሰለሞን ማህተም የሚባለው ባለ ስድስት ክንፍ ኮከብ ነው፡፡

ታዲያ ሰለሞናውያን ነገስታት አባታችን የሚሉት ሰለሞን ተጽእኖው በመላው አለም እስከዛሬ ድረስ የዘለቀ ንጉስ ነው፡፡ በተለይ የምዕራቡን አለም ፈጥሮታል ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ የምዕራብ ስልጣኔ በሁለት ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነው፡፡

በግሪክ ፍልስፍናና በሰለሞን ምስጢራዊ ትምህርት፡፡ ፍሪማሶኖች ብትል፣ ቴምፕላሮች ብትል፣ ኢሉሚናቲዎች ብትል ሁሉም የሰለሞን ቤተ መቅደስ ተማላዮች ናቸው፡፡ ለመሆኑ የሰለሞን ቤተ መቅደስ እንደዚህ የአለምን “ጠቢባን” ትኩረት የሳበው ለምን ይሆን? ባማረ አሰራሩ? በውስጡ የተቀመጠበት ጽላተ ሙሴ? በወጣበት ወጪ? በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት ሰለሞን ያንን በከበሩ ድንጋዮች ያጌጠ ቤተመቅደስ ለመስራት በአሁኑ ምንዛሬ ከአራት ትሪሊዮን ዶላር በላይ አውጥቷል ይላል፡፡ አራት ትሪሊዮን ዶላር! በመጨረሻው ዘመን(ምናልባት በቅርቡ) እሩሳሌም ላይ መሲሁ ከመምጣቱ በፊት ይሰራል የሚባለው ሶስተኛው ቤተ መቅደስ እንኳን አንድ ትሪሊዮን ዶላር ነው የተበየነለት፡፡

ለማንኛውም የአራት ትሪሊየኑ ቤተ መቅደስ ዋና መሃንዲስ ሂራም አቢፍ ይባላል፡፡ በእብራይስጥ አባ ሂራም እንደማለት ነው፡፡ ጢሮሳዊ ነው፡፡ ታሪኩ መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ በአንደኛ ነገስትና ሁለተኛ ሳሙኤል ላይ ይገኛል፡፡ በእኛ ቋንቋ “ኪራም” ነው የምንለው፡፡ የአለማችን የምን ጊዜም ምርጡ ገንቢ ነው ይሉታል ፍሪማሶኖች፡፡ ራሱ “ፍሪ ማሰን” ማለትስ “ነጻ ገንቢ” ማለት አደል? ብቻ ጠቢቡ ኪራም የሰለሞንን ቤተመቅደስ በዋና ገንቢነት ገንብቶ ለመጨረስ አስራ ሶስት አመት ፈጀበት፡፡ 

ይህ ፕሮጀክት በአለም ታሪክ ትልቁ ፕሮጀክት ነው ይባላል፡፡ የራሱ የእግዚአብሄር ፕሮጀክት ነዋ! በመጽሃፈ ነገስት ቀዳማዊ ምዕረፍ 9 ቁጥር 1 ላይ የቤተመቅደሱ ስራ እንዳለቀ እግዚአብሄር ለሰለሞን እንደ ‹እንደተገለጠለት› ይናገራል፡፡ ኪራም ግን ቤተ መቅደሱ ከማለቁ በፊት ሞቶ ነበር፡፡ ይህ አሳዛኝ ፍጻሜ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ባይገኝም በሌሎች ታሪኮች ላይ ግን ሰፊ ትንታኔ አለው፡፡

ለመሆኑ የሂራም አቢፍ አሟሟት እንቆቅልሽ ከኢትዮጵያችን ጋር ምን ያገናኛኘዋል? ለምንስ ፍሪማሶኖች(ነጻ ገንቢዎች) ኢትዮጵያን አጥብቀው ይፈልጓታል? ጽላተ ሙሴ ኢትዮጵ ውስጥ ነው የምንለው ከዚህ ታሪክ ጋር ይገናኝ ይሆን? ምናልባትም ገነት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበረች ከሚለው ትርክት ጋር ይገኛኝ ይሆን? ወይ ደግሞ ፍሪማሶኖች ክፉኛ የሚሿት “ዩቶፒያ” እዚሁ እኛ “ሲኦል ናት” የምንላት “ኢትዮጵያ” ውስጥ ትሆን? “ኢትዮጵያ ለምን”?

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የሰለሞን የግንበኞች አለቃ (ሄድ ማሰን) ሂራም አቢፍ ቤተመቅደሱን ሰርቶ ከመጨረሱ በፊት ሶስት የራሱ የበታች ሰራተኞች የታላቅ ጥበቡን “ምስጢር” እና “ቁልፍ” እንዲሰጣቸው ያስፈራሩታል፡፡ እሱ ግን እንቢ አላቸው፡፡ ካልነገራቸው እንደሚገድሉት ነግረው አስፈራሩት፡፡ 

አሁንም በእንቢታው ጸና፡፡ ገደሉት፡፡ አገዳደላቸው ራሱ ብዙ ዝርዝር አለው፡፡ ዛሬም ድረስ የሂራም አቢፍ አገዳደል አንድ ጀማሪ የፍሪማሶን አባል ደረጃ አንድ አባልነት ሲገባ እንደ ክርስቲያኖች ጥምቀት ሁሉ በተምሳሌትነት ይከውኑታል፡፡ ድራማው ማንኛውም አባል ወደ ምስጢር ማህበሩ ሲገባ ለማህበሩ ምስጢር ነፍሱን እንኳን የሚሰጥ መሆኑን ለማመስጠር ነው፡፡ የማሶኖችን ቴምፕል ኢንሺየሽን ሴረሞኒ ዩቱዩብ ላይ በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡

የቴምፕሉ ዋና ካህን የሚያስፈጽመው ይህ ስነ ስርዓት ለዓመታት ሲያወዛግብ የኖረ ነው፡፡ ምክነያቱም አንድ የፍሪማሶን አባል ለማህበሩ ምስጢር የማይታመን ከሆነ ራሱ እንኳን ለማህበሩ ባይታመን እነሱ ይገሉታል፡፡ በዚህ ሁኔታ የማህበሩን ምስጢር ለማውጣት የሞከሩ፣ መጽሃፍ ለመጻፍ የጀመሩ፣ ምስጢር አውጥተዋል ተብለው የተጠረጠሩ አያሌ አባላት ወይ ተገለዋል፣ ወይ ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡

ሂራም አቢፍ ግን ለምስጢሩ ታምኖ ሞተ፡፡ ነፍሱ ከመውጣቷ በፊትም “ለመበለቲቱ ልጅ እርዳታ የለውምን?” ብሎ እንደሞተ ማሶኒክ ጽሁፎች ይናገራሉ፡፡ ይህ በራሱ ሌላ ብዙ ዝርዝር ጉዳይ የያዘ ስለሆነ ለጊዜው እንለፈው፡፡ ብቻ ሶስቱ ወንጀለኞች ታላቁን ገንቢ እዚያው ቤተመቅደሱ ውስጥ ከገደሉት በኋላ ንጉሱ ሰለሞን ይዞ እንዳይቀጣቸው ወደ ሌላ ሀገር ለማምለጥ ፈለጉ፡፡ ወዲያው ወደ ጆፋ ወደብ ሲሄዱ አንድ መርከበኛ ያገኛሉ፡፡

“ወዴት ነው ምትቀዝፈው” አሉት፣ እየተቻኮሉ፡፡

“ወደ ኢትዮጵያ!” ካፒቴኑ መለሰ፡፡

“መሄድ የምንፈልግበት ትክክለኛው ሀገር፡፡ ሶስታችንም ከአንተ ጋር መጓዝ እንፈልጋለን፡፡”

“በጣም ጥሩ፡፡ አብራችሁኝ መጓዝ ትችላላችሁ፡፡ እንደማያችሁ የቤተመቅደሱ ሰራተኞች ትመስሉኛላችሁ፡፡”

“አልተሳሳትክም”

“አብሬያችሁ ልጓዝ በመሆኔ ደስታ ይሰማኛል፡፡ መቼም ከንጉሱ የይለፍ ፈቃድ እንደያዛችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡”

ገዳዮቹ ተደናገጡ፡፡ “የይለፍ ወረቀት አልያዝንም፡፡ አስፈላጊ መሆኑን አላወቅንም ነበር፡፡ ለአስቸኳይ ስራ ተልከን ነው፡፡ የላኩን ሰዎች ምናልባት ዘንግተውት ይሆናል፡፡ ወይም አስፈላጊ አልመሰላቸውም፡፡”

“ምን! የይለፍ ወረቀት የላችሁም? እንደዚህ ከሆነ በእኔ መርከብ መጓዝ አትችሉም፡፡ ይሄ በጥብቅ የተከለከለ ነገር ነው፡፡”

“ጉዳዩ እንደዛ ከሆነ ተመልሰን የይለፍ ወረቀቱን ማምጣት እንችላለን፡፡”

“ብትፈጥኑ ይሻላል፣ እናንተ አጠራጣሪ ሰዎች…”

ይህ እንግዲህ በማሶኖች ቤት ውስጥ “የምንጊዜም ተወዳጁና ምስጢራዊው ምልልስ” ነው ይሉታል፡፡ በተለይ ከዚህ ታሪክ ውስጥ ለብዙ ሺህ አመታት ያልተፈታ እንቆቅልሽ ሆኖ የኖረው “Why Ethiopia?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ማሶኖች በጉዳዩ ላይ አያሌ ምርምሮችን አድርገዋል፡፡ ጀማሪ ማሶኖች በዚህ ጥያቄ ላይ መርምር አድርገው ግኝታቸውን እንዲያቀርቡ ይታዘዛሉ፡፡ ጥያቄው በምስጢር ማህበሩ አባላት ዘንድ የአዕምሮ ልህቀት መለኪያ እንቆቅልሽ (Riddle) ሆኖ ኖሯል ኢትዮጵያ ለምን? ኢትዮጵያ ለምን? ኢትዮጵያ ለምን? ከመላምት በስተቀር መልስ የለም!

የዚህን ጥያቄ መልስ ከጽላተ ሙሴ ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡ ከአባይ ጋር የሚያይዙትም እንዲሁ፡፡ በጊዜው ከነበሩት ኢትዮጵያውያን ነባራዊ ሁኔታ ጋርም አያይዘው ለመፍታት የሚሞከሩ አሉ፡፡ ብቻ ኢትዮጵያ ከጥንት ግሪካውያን የዩቶፒያ ፍለጋ በኋላ ሁለተኛው የፍለጋ መስመሯ በዚህ እንቆቅልሽ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ 

ጥንታዊ ግሪካውያን ፈላስፎች በሩቅ ምድር የምትገኝ፣ እጅግ የተዋበች፣ ንገሷ ገናና፣ ህዝቦቿም ልዩ የሆኑ “ዩቶፒያ” የምትባል ሀገርን ለማግኘት ይሹ ነበር፡፡ የግሪክ ታላላቆቹ አማልክት እነ ዜውስ ከኦሊምፐስ ተራራ ተነስተው እዚች ሀገር ተራሮች ላይ ለተዝናኖት ይሄዱ እንደነበር እነሆሜር ሳይቀሩ ጽፈዋል፡፡

ይህ ተምኔታዊ የሆነች ሀገር ፍለጋ “ሀ” ብሎ የጀመረው እንግዲህ እዚህ ጋር ይመስለኛል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የፍሪማሶኖቹ ታሪክ ይከተላል፡፡ ሶስተኛው የመካከለኛው ዘመን የአውሮፓውያን “የቄሱ ንጉስ/Prester John) ሀገር ፍለጋ ነው፡፡

የቄሱ ንጉስ ሀገር “ዩቶፒያ”ን ፍለጋ ጉዳይ አውፓን ያመሰ፣ አለምን የነቀነቀ ነው ይባልለታል፡፡ አውሮፓውያን እንደአሁኑ እንደ አፍሪካ ድሆች፣ ወርሺኝ የሚያዘወትራቸው፣ በጦርነት የሚታመሱ፣ በበጎቻቸው ኑሮ እንኳን የሚቀኑ ምንዱባን ነበሩ፡፡ ዘመኑም አውሮፓውያን የጨለማው ዘመን በመባል  ይታወቃል፡፡

ከሮም ውድቀት በኋላ ኦቶማን ቱርኮች ከበው እያስጨነቋቸው ስለነበር፣ የእርስ በርስና የሃይማኖት ጦርቶች አሰልችተዋቸው ባለበት ሰዓት፣ አንድ ንጉሷ ካህን የሆነ ገናና የክርስቲያኖች ሀገር ከአውሮፓ ርቃ እንዳለች ወሬው ይናኛል፡፡ ይባስ ብሎም እነሱ ፕሬስተር ጆን ወይም ቄሱ ዮሃንስ የሚሉት ንጉስ የሀገሩን ገናናነት፣ የግዛቱን ሰፊነት፣ የህዝቡን ዝና ጠቅሶ ወደ አውሮፓ ደብዳቤ እንደላከ ይወራ ጀመር፡፡ ይህም የብዙ አውሮፓውያንን ጆሮ ሳበ፡፡

 የቻሉት ሁሉ የቄሱን ንጉስ ሀገር ፍለጋ መልህቃቸውን ፈቱ፡፡ በዚያው የአውሮፓ የአሰሳ፣ የህዳሴ ዘመን ተጀመረ ይላሉ የታሪክ አዋቂዎች፡፡ ይህ አዲስ መሬት ፍለጋ አሜሪካ ሳትቀር የተገኘችበት ፍለጋ ነው፡፡ ከህንድ እስከ ላቲን አሜሪካ፣ ከሩቅ ምስራቅ እስከ አፍሪካ ድረስ የኦቶማን ቱርኮችን ከበባ እየበጣጠሱ ብዙዎች የፕሬስተር ጆንን ሀገር ፍለጋ ኳተኑ፡፡

የሚገርመው ደግሞ የቄስ ዮሃንስ ዝና በአውሮፓ በናኘበት ጊዜ ኢትዮጵያ በዛጉዌ ዳይናስቲ ላይ ነበረች፡፡ እንደሚታወቀው ብዙዎቹ የዛጉዌ ነገስታት ካህንም፣ ቅዱስም ጭምር ነበሩ፡፡ ለዚያ ነው እነላሊበላና ይምሃረነክርስቶስ “ቅዱስ” የሚባሉት፡፡ 

ቅዱስ ላሊበላ ሲባል መቼም ይገርማል፡፡ ንጉስ ሆኖ ቅዱስ፡፡  በዚያ ላይ ታላላቅ ገንቢዎች ናቸው፡፡ ዛሬም ድረስ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ የፍሪማሶኖች መነሻ ናቸው ተብለው ከሚታሙት ቴምፕላሮች (የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች!) ምልክቶች በብዛት ይገኛሉ፡፡

የሆነ ሆኖ የአሰሳው ዘመን ከአውሮፓ የጨለማው ዘመን ማብቂያና የህዳሴ ጅማሮ ቀደም ብሎ እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የዘለቀ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ፖርቹጋልና ስፔን የአውሮፓ ልዕለ ሀያሎች በነበሩበት ጊዜ ከነዚህ ሀገራት በዛ ያሉ ተጓዦች ወደ ሀገራችን መጡ፡፡ የፕሬስትር ጆንን ሀገር አገኘነው ብለው ጻፉ፡፡ ነገር ግን እነሱ ኢትዮጵያ በደረሱበት ጊዜ የዛጉዌ ስርወ መንግስት ወድቆ የሰለሞናዊው ስርወ መንግስት በድጋሜ በሸዋ ስልጣኑን ይዞ ነበረና “ቄስም ንጉስም” የሆነ መሪ አላገኙም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን ታሪክ መርምረው፣ ከአክሱም ጀምሮ እስከ የሃ፣ ከላሊበላ እስከ ሸዋ ድረስ ያገኟቸውን ድንቅ የግንባታ ውጤቶች ሲያዩ እውነትም የቄሱ ዮሃንስን ሀገር አግኝተናታል ብለው ለአለም አሳወቁ፡፡

በተለይ በጊዜው ሀገሪቱ የስልጣን ማዕከል ሸዋ ስለነበር በአካባቢው የነበሩትን እንደ ቤተ አምሃራ፣ አንጾኪያ፣ በራራና ሌሎች ከተሞችንም ሲጎበኙ በጊዜው የጨለማ ዘመን ላይ የነበረቸው አውሮፓ ውስጥ እንኳን ሊገኙ የማይችሉ የስነ ህንጻ ስራዎችን ማግኘት ችለው እንደነበር አያሌ ጽሁፎች አሉ፡፡ ወቅቱ የፍሪማሶኖች (ነጻ ገንቢዎች) እንቅስቃሴ የተሟሟቀበት ጊዜ እንደመሆኑ አብዛኞቹ ወደ ሀገራችን የሚመጡት ጎብኚዎች የእነሱ አባላትና ተጽዕኖ ያረፈባቸው እንደመሆናቸው ያገኟቸው “የግንባታ ውጤቶች” ዋና የጥበብ መለኪያዎች ነበሩ፡፡

በተለይ በቤተ አማራ (ወሎ) አካባቢ ይገኝ የነበረው (በኋላ በግራኝ የወደመው) ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠው መካነ ስላሴ ቤተክርስቲያን ህንጻው፣ አሁን አራዳ ጊዮርጊስ የሚገኝበት ቦታ ለይ በጥንቷ በራራ ጊዜ ተሰርቶ ነበረው አስደናቂ አራት ማዕዘን ካቴድራል፣ እንዲሁም በበራራና አካባቢዋ የነበሩ እንደ ሽንቁሩ ሚካኤል ያሉ ውቅር አቢያተክርስቲያናትና ህንጻዎች ለአውሮፓውያኑ አይኖች ድንቅ ነበሩ፡፡ 

በጊዜው የጎንደር አብያተ መንግስታት ገና ባይታነጹም በመላው ሀገሪቱ ከፍተኛ ጥብብና ቅንጦት ያለባቸው በወርቅና በብር የተለበጡ ትላልቅ የግንባታ ውጤቶች ነበሩ፡፡

ፍሪማሶኖች ገንቢዎች ናቸው፡፡ ስረ መሰረታቸው የኢትዮጵያ ሰለሞናዊ ስርወመንግስት ነገስታት ስር የሆነው ሰለሞን ነው፡፡ በጊዜው ብዙ አውሮፓውያን ተጓዦች የሰለሞን ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረው ጽላተ መሴ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ያምኑ የነበረ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የሆነ የግንባታ ጥበብ (ቀስ በቀስ እየቀዘቀዘ ቢመጣም) እንደነበራቸው ተረድተዋል፡፡ 

ሌላው አስደናቂው ነገር የሙሴ ጽላት በግብጽ በኩል አባይን ተከትሎ መጀመሪያ ወደ ጎንደርና ጣና ገዳማት፣ ከዚም ወደ ሸዋ ቀጥሎ ወደ አክሱም መሄዱ ድንቅ ግጥጥሞሽ ነበር፡፡ የሰለሞናውያን ነገስታት የስልጣን ማዕከል ደግሞ በተቃራኒው ከአክሱም ጀምሮ ወደ ሸዋ፣ ከዚያም ከግራኝ ወረራ በኋላ ከሸዋ ወደ ጎንደር ነበር የተንቀሳቀሰው፡፡ እዚህ ጋር ከዛሬ ሶስት ሺህ አመት በፊት ሂራም አቢፍን ገድለው ወደ ኢትዮጵ ሊኮበልሉ አስበው የነበሩትን ነፍሰ ገዳይ ጥበብ ፈላጊዎች እናስታውስ፡፡

የእነሱም ጉዞ እቅድ ያው ከሜድትራኒያን ባህር በግብጽ በኩል አባይን ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ መግባት ነበር፡፡ አብዛኛው የውጪ ተጽዕኖ ወደ ሀገራችን ገባው አባይን ተከትሎ ነበር ማለት እንችላለን፡፡

ከጥንት ግሪካውን ጀምሮ፣ የሙሴ ጽላት፣ ክርስትና (አንዳንዶች ክርስትና ወደ ኢትዮጵ የገባው እንደ እስልምና ሁሉ በቀይ ባህር በኩል ነው ይላሉ)፣ የአውሮፓ አሳሾች በሙሉ አባይን ተከትለው ነበር ወደ ኢትዮጵያ የገቡት፡፡ እንደ ጀምስ ብሩስ ያሉ አያሌ ተጓዦች የአባይን ምንጭ ፍለጋ ብለው ወደ ሀገራችን እንደገቡ የሚታወቅ ነው፡፡ 

የሆነው ሆኖ የዚህ ሁሉ ገመድ ማሰሪያ አባይ  ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በመጽሃፍ ቅደስ ላይ ጊዮን ተብሎ የተጠቀሰው የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ የሚከበው የተባለለት አባይ በፍሪማሶኖች ምስለት ከገነት እንደሚፈሰው የህይወት ውሃ የሚነጸርበት ምስጢሩ ይህ ነው፡፡

የአባይን ምንጭ ማግኘት ገነትን/ዩቶፒያን/ታላቋን የፕሬስተር ጆን ሀገር/ኢትዮጵያን ማግኘት ይሆን? የመጽሐፈ ራሴላስ የታሪክ ፍሰት በአንጻሩ አባይን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ወደ ግብጽ የሚፈስ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክነያት አለው፡፡ 

ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን ገነትን የሚመስል “የደስታ ሸለቆ” እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ስሎ “የቶፒያን” አግኝቻታለሁ የሚል ይመስላል፡፡ ነገር ግን ይህ በግልጽ አይታይም፡፡ ምክነያቱም ሳሙኤል ጆንሰንን ጨምሮ፣ የ”ዩቶፒያ” መጽሃፍ ደራሲው ሰር ቶማስ ሙር፣ ስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስና ሌሎችም የዚያ ዘመን ዝነኛ ጸሃፊዎች አብዛኞቹ  ፍሪማሶኖች ናቸው፡፡ የቀሩት ደግሞ የፍሪማሶን ትምህርት ተማላዮች፡፡ ፍሪማሶን ደግሞ የምስጢር ማህበር ነው፡፡ መልዕክቱን የሚያስተላልፈውም በምስጢር ነው፡፡

ስለዚህ ወደፊት የማካፍላችሁ እውነታዎች ምናልባት መጽሃፉን ስታነቡ በግልጽ ላታገኟቸው ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን መልዕክትን በምሳሌ፣ ሀሳብን በምልክት፣ ቁምነገርን ደስውር የማስተላለፍ ጥበብ ከእኛ ከኢትዮጵውያን በላይ የተካነበት የለምና ስረ ምስጢሩን እንደርስበታለን፡፡ የቅኔ ሀገር፣ የጠልሰም ሀገር፣ የምልክቶች ሀገር ውሉዶች ነንና፡፡

እስካሁን ያየነው የመጽሃፈ ራሴላስ የኋላ ታሪክ ነው፡፡ መጽሃፉን መዳሰስ ገና አልጀመርንም፡፡ የኋላ ታሪኩን ካልተረዳን መጽሃፉን በአለም ላይ ባለው ዝና ልክ ላንረዳው እንችላለን በሚል ነው ወደኋላ ሄድኩት፡፡ ይህንን በማድረጌ አንባቢዎች ወደፊት ያመሰግኑኝ ይሆናል፡፡ ለአሁኑ ግን የመስጢራዊ መልዕክትን ሀይል እያሰላሰልንበት እንድንቆይ ባለቅኔዋ ጂጂ ለአባይ የተቀኘችለትን ብርቱ ስውር ቅኔ ነጠላ ስንኝ ተቋድሰን እንለያይ፡፡

…. “ከጥንት ከጽንሰ አዳም ገና ከፍጥረት፣

    የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት…”

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top