የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሽያ በፈቃደኝነት እጃቸውን እየሰጡ ነው
የህወሃት ጁንታ አስገድዶ ለውጊያ አሰልፏቸው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ትጥቃቸውን እየፈቱ ለሰራዊቱ እጃቸውን በሰላም መስጠታቸውን የሰሜን ምዕራብ ግንባር የመገናኛ ብዙሃን አስተባባሪ ኮሎኔል አባተ ንጋቱ ተናገሩ።
የህወሃት ጁንታ ከሀሰት ፕሮፓጋንዳ ያለፈ የመከላከያ ሰራዊቱን እርምጃ የሚቋቋም አለመሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሎኔሎ እንደተናገሩት የአገር መከላከያ ሰራዊት ህግ እያስከበረ ባለበት የትግራይ ክልል የጁንታው ታጣቂ ሃይል መሰረተ ልማቶችን በማጥፋት ወደ መቀሌ ሸሽቷል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት እስካሁን ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ በድል በመገስገስ አካባቢውን ተቆጣጥሯልም ነው ያሉት።
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የህወሃት ጁንታ የሚያናፍሰው ፕሮፓጋንዳ ግን ፍፁም እውነታ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት በህግ ማስከበር ሂደቱ በህወሃት ቡድን ላይ እርምጃ እየወሰደ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ላይ መሆኑንም ኮሎኔል አባተ ተናግረዋል።
የህወሃት ጁንታ በግዴታ ለውጊያ አሰልፏቸው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ትጥቃቸውን እየፈቱ ለሰራዊቱ እጃቸውን በሰላም መስጠታቸውንም ገልጸዋል።
በህግ ማስከበር ሂደቱ እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ስናይፐር፣ ክላሽ፣ ሽጉጥና መሰል የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋሉንም ጠቁመዋል።
“በተጨማሪም ከ5 ሺህ በላይ የቡድን መሳሪያዎች እንደ አርቢጂ፣ ብሬን፣ ዲሽቃና ሎሎችም በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል” ብለዋል።
በትግራይ ክልል ህዝብ ላይ የህወሃት በጁንታ ይፈፅም የነበረውን ግፍ፣ በደልና አፈና ህዝቡ በምሬት እየገለጸ መሆኑን ኮሎኔል አባተ አብራርተዋል።
በዘመቻው ሰራዊቱ በደረሰባቸው የትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የህዝቡ ድጋፍና እገዛ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
የህወሃትን የጥፋት ዓላማና እቅድ እንዲሁም የሀሰት ትርክት የትግራይ ህዝብ ሊቀበለው ባለመቻሉ የጁንታው ማብቂያ እየተቃረበ መሆኑንም ኮሎኔሉ ገልጸዋል።
ጁንታው አሁን ላይ “ስልታዊ ማፈግፈግ አድርገናል” በማለት እያወናበደ መሆኑን ህዝቡ ሊገነዘብ እንደሚገባም ጠቁመዋል።