የህወሃት ጁንታ አባላት በመንግስት የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው እጅ እንዲሰጡ የአቶ ጌታቸው ረዳ እህት ጠየቁ
የህወሃት ጁንታ ቡድን አባላት በመንግስት የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው እጅ በመስጠት የትግራይ ህዝብ ከተጋረጠበት አደጋ ሊታደጉት እንደሚገባ የህወሃት ጁንታ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት የአቶ ጌታቸው ረዳ ታናሽ እህት ዋና ሳጅን ትዕግስት ረዳ ገለጹ።
“እኔ የአቶ ጌታቸው ረዳ እህት ብሆንም የፖለቲካ አመለካከት በዘር አይተላለፍም” የሚሉት ዋና ሳጅን ትግስት፤ “በበኩሌ በአፍላነት እድሜዬ ህብረ-ብሄራዊ ለነበረው ኢህዴን የታገልኩና ለሰንደቅ ዓላማዬ ዘብ የምቆም ህዝባዊ ፖሊስ ነኝ” ብለዋል።
በሰቆጣ ከተማ ለ22 ዓመታት የኖሩት ዋና ሳጅን ትዕግስት ከአሁኑ የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ገልጸው፤ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዙት ለኢዜአ ተናግረዋል።
“መከላከያ ሀገር ነው፤ ብሔር የለውም ዘር የለውም እሱ እንዲበተን አልፈልግም፤ ሀገርን የሚጠብቅ ሰው ሲሞት በጣም አዝኛለሁ” ያሉት ዋና ሳጅን ትዕግስት ረዳ፤ መንግስት እያካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የትግራይን ወጣት ለጦርነት መማገዳቸው ለትግራይ ህዝብ ደንታ እንደሌላቸው ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
“በወንጀል የሚፈለጉ የህወሃት አመራሮች በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ለሁለተኛ ጊዜ በመንግስት በኩል የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ህዝባቸውን ከተጋረጠበት አደጋ ሊታደጉት ይገባል” ብለዋል።
ወንድማቸው አቶ ጌታቸው ረዳ የህወሃት ጁንታ አመራር በመሆናቸው እንደሚያዝኑ የሚናገሩት ዋና ሳጅን ትዕግስት ረዳ፤ እሳቸው የአፍላነት እድሜያቸውን በትግል ያሳለፉት ለሀገር አንድነት ባላቸው ጽኑ እምነት መሆኑን ገልጸዋል።
ለግል ጥቅም ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥለው የህወሃት ጁንታ አመራር አባል በሆኑት ወንድማቸው ድርጊት እንደሚያዝኑም ገልጸዋል።
ወንድማቸው ሁሉም ህዝብ የራሳቸው መሆኑን በመረዳት ዘብ ሊቆሙለት ይገባ እንደነበረም በመጥቀስ ወቅሰዋል።
እሳቸው በትግል ቢያሳልፉም ቀድሞውኑ የትግል ተሞክሮ የሌላቸውና መምህር የነበሩት የጁንታው አመራር ወንድማቸው እስከ አሁን ለሰሩት ጥፋት ህግ እንደሚዳኛቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። (ኢዜአ)