የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ስለሚዲያዎች ምን አለ?
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ጥራቱ የተጠበቀ፣ በኃላፊነት ስሜት የሚንቀሳቀስ እና ነፃነቱ የተረጋገጠ አስተማማኝ የመገናኛ ብዙሃን የመገንባት እና የመቆጣጠር ዓላማን ይዞ የተቋቋመ አካል ነው፡፡
የውጭ ሚዲያንም በተመለከተ የዘገባ ፈቃድና ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ ከዘገባዎቻቸው በመነሳት የአዝማሚያ ትንተና (trend analysis) በመሥራት ዘገባዎቻቸው እውነትን መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ፤ ሚዛናዊና ታአማኒነት ያላቸው ብሎም ሙያዊ ሥነ ምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚረዳ ግብረ መልስ ይሰጣል፤ የእርምት እርምጃ ይወስዳል፡፡
ይህ ሙከራም መሻሻሎችን ለማየት አስችሏል፡፡ይሁንና የተሰጣቸውን ሙያዊ አስተያየት ችላ በማለት የተሳሳቱ ወይም ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎችን በመሥራት የቀጠሉ አንዳንድ የውጭ የመገናኛ ብዙኃን አልጠፉም፡፡ ለምሳሌ ሮይተርስ፤ ቢቢሲ (አማርኛና እንግሊዝኛ ፕሮግራሞች)፤ የጀርመን ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም፤ እና አልጀዚራ (እንግሊዝኛ) ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነኚህ ሚዲያዎች በአገራችን ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው እንደ አዲስ ስታንዳርድ ያሉ ድረ-ገፆች እንዲሁም የጋዜጠኝነት ዕውቅናና ፈቃድ የሌላቸው እንደ ዊሊያም ዴቪሰን (William Davison) ያሉ ራሳቸውን የኢትዮጵያ ጉዳይ ተንታኝ አድርገው ያስቀመጡ ግለሰቦች በቅርቡ የፌዴራል መንግስትና የሀገር መከላከያ ሰራዊት በህወኃት ጁንታ ላይ ህግን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ አስመልክቶ ከሀቅ የራቁ መረጃዎችን የማሰራጨት፤ የኢትዮጵያ መንግስትን አስተያየት ያለማካተት እና ውጊያው የእርስበርስ ጦርነት እንደሆነ አስመስሎ የማቅረብ እንዲሁም እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ከክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊነት ጋር በማያያዝ ፌዴራል መንግስቱ ተገዶ የገባበት ሳይሆን ችግሩን በሰላምና በድርድር የመፍታት ፈቃደኝነት የጎደለው በማስመሰል እንዲሁም ሊፈጠር የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ በተጋነነ መልኩ በመሳል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር የማድረግ አዝማሚያ አስተውለናል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን እየወሰደ ያለውን ማስተካያዎች እንደሚከተለው ይገልፃል፡፡
#ሮይተርስ
ሮይተርስ ፈቃዱ ተሰርዞ ከኢትዮጵያ እንደተባረረ በተለያዩ ሚዲያዎች የተገለፀው ስህተት ነው፡፡እውነታዉ በኢትዮጵያ የሮይተርስ ቋሚ የዜና ወኪል የሆኑት ጋዜጠኛ Giulia Paravicini ተቋማቸው የሠራውን ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ አስመልክቶ ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገው ውይይት ወቅት ባሳዩት የመታረም ፈቃደኝነት ጉድለት እና ያልተገባ ባህሪ ብሎም የሀገሪቱን ህግ አክብረው ለመንቀሳቀስ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የድርጅታቸው የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ጋር በተደረገ ውይይት በ Giulia Paravicini ምትክ ሮይተርስ ሌላ ቋሚ የዜና ወኪል እንዲመድብ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
በምሳሌ ለማሳየት ያህል፡- Nov.08/2020 “Ethiopia’s PM seeks to regain control over restive Tigray region” በሚል ርዕስ ሮይተርስ ባወጣዉ ዘገባ ግጭቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊለወጥ እንደሚችል እና የብሄር መልክ የመያዝ ዕድል እንዳለዉ ጠቅሶ እንዲሁም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በየብሄር ተከፋፍሎ የመበተን ከፍተኛ አደጋ እንደተደቀነበትና ምልክቶችም እየታዩ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ሆኖም በጋዜጠኛ Giulia Paravicini በኩል የመንግስትን አስተያየት ለማካተትም ይሁን ከገለልተኛ ወገን ለማጣራት ሙከራ አልተደረገም፡፡
#William_Davison
William Davison የጋዜጠኝነት ዕውቅናና ፈቃድ የሌለዉ እንዲሁም በራሱ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተንታኝ አድርጎ ያስቀመጠ ግለሰብ ነዉ፡፡ ሆኖም ለበርካታ አመታት በኢትዮጵያ የBloomberg ሚዲያ ቋሚ የዜና ወኪል ሆኖ የሰራ ቢሆንም ከባለፉት ሶስት (3) አመታት ወዲህ ግን የዘገባ ፍቃዱን በራሱ ተነሳሽነት መልሶ የተሰናበተ መሆኑን እያረጋገጥን በተለያዩ የሚዲያ አዉታሮች በጋዜጠኝነት ስራዉ ምክንያት ከሃገር እንደተባረረ ተደርጎ የሚሰራጨዉ መረጃ ፍጹም ሃሰት መሆኑን ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
#አልጀዚራ (English)
አልጀዚራን በተመለከተ በEnglish ዘገባዎች ውስጥ በኢትዮጵያ መንግስት ወገን ያለን ምልከታ ሳያካትት በህውሓት ጁንታ ላይ የሚደረገውን የህግ ማስከበር ሂደት በአንድ ሃገር ብቻ የማያበቃ ነገር ግን መላ የአፍሪካ ቀንድን ሊያዳርስ የሚችል ጦርነት አድርጎ በመዘገብና በድርድር ጥያቄ ዙሪያ መንግስት እምቢተኛ መሆኑን በማጉላት በሃገሪቱ ላይ የአለም አቀፍ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲበረታ ሊያደርጉ የሚችሉ ሃላፊነት የጎላቸው ዘገባዎች ይታያሉ፡፡
ይህም በዋናነት Doha በሚገኘዉ የአልጀዚራ ዋና ማሰራጫ የእንግለዝኛ ስርጭት ክፍሉ የሚታይ ግድፈት መሆኑን በመረዳት በቀጣይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ ሪፖርት ተደርጎላቸዋል፡፡
#የጀርመን_ድምፅ (DW) አማርኛ
ለማሳያ ያህል፡-
‹‹የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት እንዳሳሰባቸው ገለጹ። ውጥረቱን ለማርገብ እና ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ዋና ጸሐፊው አሳስበዋል።‹‹ በሚል ኖቬምበር 5/2020 ባሰራጨዉ ዘገባ በትክክል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል መሆን ያለመሆኑን ማረጋገጥ በማያስችል መልኩ የቀረበ ከመሆኑም ባሻገር የህግ የበላይነትን ማስከበር ሳይሆን የእርስበርስ ግጭት እንደሆነ የሚያስመስል ዘገባ በመሆኑ ሊታረም የሚገባ መሆኑ ጀርመን ቦን ለሚገኙ ሃላፊዎች ተገልጾላቸዋል፡፡
#ቢቢሲ በአማርኛ
ቢቢሲም በአማርኛው ዘገባ ላይ ሰኞ ኅዳር 07/2013 ዓ.ም “ዛሬ ረፋዱ ላይ በትግራይ ክልል ርዕሰ ከተማ መቀሌ ውስጥ የአየር ጥቃት መፈጸሙን የከተማዋ ነዋሪዎችና የቢቢሲ ዘጋቢ ከስፍራው ገለጹ” በማለት ዘግቦ ሲያበቃ በሁለተኛው ቀን ቀደም ሲል ያስተላለፈው ዘገባ የስህተት መረጃ መሆኑን በአግባቡ ሳይገልጽ በሌላ ዘገባ“የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማዕከል ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ ከመቀሌ ከተማ ውጪ ባሉ በተመረጡ ህወሓትን ኢላማ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጿል” በማለት አሻሽሏል ። በሁለቱ ዘገባዎች መሃከል የሚታየው ልዩነት በትልቅ ሃላፊነትና ጥንቃቄ ሊሰራጭ የሚገባውና በሃገር ሰላም ዙሪያ ከፍተኛ እንደምታ ያለው ጉዳይ ላይ የሃሰት መረጃን በማን አለብኝነት ማስተላለፍ የውጪ ሚዲያዎች ልምድ እየሆነ መጥቷል፡፡
ይህም ሃገሪቱን በውጪው አለም ዘንድ ትክክል ያልሆነ የነበራዊ ሁኔታ ምስል እንዲኖር ስለሚያደርግ ሃገሪቱ በጥንቃቄ ልትይዘው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ቢቢሲ አማርኛ በአፋጣኝ ማስተካከያ እንዲያደርግ ሪፖርት ተደርጎለታል፡፡
እንደ ማጠቃለያም ከላይ የተጠቀሱት ዘጋቢዎች የሚያስራጯቸው መረጃዎች አለም አቀፍ የዳዜጠኝነት መርሆዎችን ያላገናዘቡ እና የግል አቋም የመያዝ አዝማሚያ የሚታይባቸው ናቸው፡፡ በሁሉም በመገናኛ ብዙሃኑ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚታዩ ግድፈቶች፡-
~ ሚዛናዊነትን አለመጠበቅ፣
~ እውነትን መርህ ያላደረጉ ዘገባዎች፣
~ በርዕሰ- አንቀጾቻቸው ላይ ግነትን መጨመር፣
~ የመንግስት አስተያየትን አለማካተት፣
~ ሙያዊ ስነ ምግባር ያለመላበስ፣
ከህግ ማስከበር ሂደት ይልቅ የእርስ በርስ ጦርነት አንደምታ ላይ ማተኮርና የችግሩን ስፋት መለጠጥ ከብዙ ግድፈቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን
አዲስ አበባ