ህወሃት የአክሱም ኤርፖርትን በ26 የተለያዩ ቦታዎች በግሬደር አርሶታል
የህወሃት የጥፋት ቡድን አክሱም ኤርፖርትን በ26 የተለያዩ አካባቢዎች በግሬደር እንዳረሰው የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።
ቡድኑ በአገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ባይወሰድበት ኖሮ በአካባቢው ላይ የከፋ ጉዳት ያስከትል እንደነበርም ታውቋል።
የህወሃት ጁንታ አሁን ላይ ተስፋ እየቆረጠ በመምጣቱ በተለይ የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጥፋት እየፈፀመ ይገኛል።
የጥፋት ቡድኑ የአክሱም ኤርፖርትን ከ23 አስከ 26 የተለያዩ አካባቢዎች በግሬደር በማረስ የህዝቡ ጠላት መሆኑን ማሳየቱን ከሰራዊቱ አመራሮች መካከል ሻምበል አብይ ሩፋኤል ገልጸውልናል።
ጁንታው በሰራዊቱ አፋጣኝ አርምጃ ባይወሰድበት ኖሮ ኤርፖርቱን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም ቅርሶችን ሙሉ ለሙሉ የማውደም እቅድ ነበረውም ብለዋል።
የህወሃት ፅንፈኛ ሃይል በፊትም ለጥፋት የቆመ ሃይል ነው ያሉት ሻምበል አብይ፤ አሁን ደግሞ በይፋ የህዝብ ጠላትነቱን አሳይቷል ብለዋል።
በአክሱም ኤርፖርት የፈፀመውም የአውሮፕላን መንደርደሪያውን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በመቆፈር ጉዳት አድርሷል።
በኤርፖርቱ ህንፃ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ንብረቶችንና ቅርሶችንም መዝረፉን ገልጸው፤ በሰራዊቱ ፈጣን እርምጃ ባይወሰድበት ኖሮ አካባቢው ላይ ተጨማሪ ጥፋት ያደርስ ነበር ብለዋል።
የህወሃት ጁንታ እየፈፀመው ያለው ተግባር የህዝብ ግልፅ ጠላት መሆኑን በአደባባይ ያረጋገጠ መሆኑን ሌላው የሰራዊቱ አመራር ሌተናል ኮሎኔል ወልዴ ሃይሌ ገልጸውልናል።
የጥፋት ቡድኑ በአገር መከላከያ ሰራዊት ፈጣን እርምጃ ባይወሰድበት ኖሮ በአካባቢው ላይ ሌላም የከፋ ጉዳት ያስከትል ነበር ያሉት ደግሞ ሻምበል ባሻ ሙላት ናቸው ።
የህወሃት ጁንታ የተለያዩ የእምነት ተቋማትን እንደ መደበቂያ በመጠቀም ጉዳት እንዲደርስባቸው ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሌተናል ኮሎኔል ተመስገን ነጋ እንዳሉትም የህወሃት ታጣቂ ሃይል በተለይም ቤተክረስቲያናትን፣ መስጅዶችና ቅርሶች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በምሽግነት እየተጠቀማቸው ይገኛል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት ግን እስካሁን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ የኦፕሬሽን ስራውን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብ የህወሃት ፅንፈኛ ቡድን እኩይ አላማ እና የጥፋት ተልእኮ ተረድቷል ያሉት አመራሮቹ፤ ለአገር መከላከያ ድጋፍና እገዛ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
ህወሃት ለህዝብ የማያስብ፣ ሴረኛ፣ አጥፊና ለራሱ ህልውና ብቻ የሚያስብ የጥፋት ስብስብ መሆኑን የትግራይ ህዝብ አሁን ላይ በአግባቡ ተገንዝቦታልም ብለዋል።(ኢዜአ)