Connect with us

ሎዛ አበራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን ተቀላቀለች

ሎዛ አበራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን ተቀላቀለች
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስፖርት

ሎዛ አበራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን ተቀላቀለች

ሎዛ አበራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን ተቀላቀለች

 

በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ከሀገር ውጪ በሚገኝ ክለብ በመጫወትና ኮከብ ጎል አግቢ በመሆን የውድድር አመቱን ያጠናቀቀችው የመጀመሪያዋ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ሎዛ አበራ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ፈረመች፡፡

ሎዛ አበራ በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በሚሳተፉ የተለያዩ ክለቦች በመጫወት በተለይ የደደቢት እና አዳማ ከተማ የስፖርት ክለቦችን የዋንጫ ባለቤት ማድረግ የቻለችና በግሏም ለበርካታ ጊዜያት ኮከብ ጎል አግቢና ኮከብ ተጫዋች መሆን የቻለች የሀገራችን ታላቅ ተጫዋች ናት፡፡

በአጥቂ ቦታ የምትጫወተው ሎዛ አበራ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የሴቶች ቡድንም በመሰለፍ ለቡድኑ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ የምትገኝ ባለትልቅ ተሰጥኦ ተጫዋች ናት፡፡ ሎዛ ባለፈው ዓመት ለማልታው ቢርኪርካራ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በመሰለፍ በኮኮብ ተጫዋችነት እና ኮኮብ ጎል አግቢነት ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ 

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር በኩል ፊርማቸውን ያኖሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አሊ አህመድ በፊርማ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የባንኩ የሴቶች ስፖርት ክለብ ውጤታማ እንደነበር ገልጸው ይህን ውጤታማነት በላቀ ሁኔታ በማስቀጠል የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን እና በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ  የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ፈርጥ የሆኑትን ሎዛ አበራ፣ ሰናይት ቦጋለ እና አረጋሽ ካሳን የመሳሰሉ ድንቅ ተጫዋቾችን ማስፈረሙን ተናግረዋል፡፡ 

ሎዛ አበራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን በመቀላቀሏ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት አቶ አሊ ተጫዋቿ ከሌሎች የቡድኑ አባላት እና ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመስራት ቡድኑን ውጤታማ እንደምታደርግ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡ 

ባንኩ በሀገራችን በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚጫወተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በስፖርቱ ዘርፍ  እንዲደገም ሁሉም ጠንክሮ እንዲሠራ ያሳሰቡት አቶ አሊ ባንኩ በሁሉም ረገድ ድጋፉን ለማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ 

ተጫዋች ሎዛ አበራ በበኩሏ ቡድኑን በመቀላቀሏ መደሰቷንና ከሌሎች የቡድን አጋሮቿ ጋር በመሆን ውጤታማ ለመሆን እንደምትሠራ ገልፃለች፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ብርሀኑ ግዛው በበኩላቸው ለረጅም ጊዜ ሲከታተሏት የነበረችው ተጫዋች ሎዛ አበራ ቡድናቸውን በመቀለቀሏ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው ቡድኑን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራት አስረድተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር ለኢትዮጵያ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዘጠኝ ተጫዋቾችን፣ አንድ አሰልጣኝ እና አንድ የህክምና ሙያተኛ ማስመረጥ የቻለ ሲሆን፤ እንደ ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም፣ መሰረት ደፋርና መስታወት ቱፋን የመሳሰሉ ብርቅየ ስፖርተኞችን ለሀገራችን ያበረከተና በስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ያለ የስፖርት ማህበር መሆኑ ይታወቃል፡፡(የኢት. ንግድ ባንክ)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ስፖርት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top