ከወያኔ ተፅእኖ መላቀቅ የተሳናቸው የትግራይ ልሂቃን
(ፍቱን ታደሰ – ለድሬ ቲዩብ)
ወያኔ በአማራና በአፋር ክልሎች የከፈተውን ወረራ መንግስት ወራሪዎቹን በመደምሰስና ከፊሉን ቁስለኛ በማደረግ አክሽፎታል፡፡ ወያኔ በፌዴራል መንግስት ላይ ትግራይ ውስጥ የሚገኘውን የሰሜን እዝ በድንገት በማጥቃት የጀመረው ወረራ በ17 ቀናት የመልሶ ማጥቃት የወያኔ ቁንጮ አመራሮቹን ህይወት ገብሮ ተጠራርጎ ተምቤንና ተከዜ ዋሻ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡ ከተደበቀበት ዋሻ ሆኖ ቀድሞ በዘረጋው ዘረኛ አደረጃጀት ከወጣት እስከ አረጋውያን የትግራይን ህዝብ ለጦርነት ቀስቅሶታል፡፡ የህወሓት መሸነፍ የትግራይ ህዝብ መሸነፍ ነው በማለት ህዝቡ መቀሌ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ለማጥቃት እንዲነሳ አድርገውታል፡፡
በምዕራባውያን ከፍተኛ ድጋፍ የሚደረግላቸው ወያኔዎች በአማራና በአፋር ክልል ላይ ያደረጉትን ወረራ ህዝባዊ ጦርነት አድርገነዋል በማለት መላው የትግራይ ህዝብ በፈቃደኝነት ጦርነቱን እንደተቀላቀለ አድርገው የነዙት ፕሮፓጋንዳ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በቁጣ እንዲነሳ አድርገውታል፡፡ በተለይ በአማራና በአፋር ክልል በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የፈጸሙት የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ህዝቡ በሚሊሻ፣ በፋኖ፣ በልዩ ሃይልና በመከላከያ ውስጥ ተሰልፈው ወያኔን እስከመጨረሻው ለማጥፋት ተንቀሳቅሰዋል፡፡
በዚህ አይነት እልህና ቁጭት የሚካሄድ ጦርነት ደግሞ መቋጫ ካልተበጀለት የመጨረሻ ውጤቱ የማይሽር ፀፀት የምናተርፍበት ይሆናል፡፡ ምዕራባውያን ገለልተኛ ሆነው ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ ከማድረግ ይልቅ በህዝብ እምቢተኝነት ከስልጣኑ የተወገደውን ዘረኛውን ቡድን ወደ ስልጣን ለማምጣት እየጣሩ ነው፡፡ ይህንን ፍላጎታቸውን ለማሳካትም ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ተፅእኖዎችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በእነሱ ጥያቄ አቅራቢነት የመንግስታቱ ድርጅት በጥቂት ወራት ውስጥ ከአስር ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲሰበሰብ አድርገውታል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በሃገር ጉዳይ ያለምንም ልዩነት አንድ ላይ በመቆማቸው ውጫዊው ተፅእኖ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፡፡
መንግስት የትግሬን ወራሪ ቡድን ከሰሜን ወሎ ጠራርጎ ከደመሰሰ በኋላ የወያኔን እስትንፋስ ለመቁረጥ ወደ ትግራይ ይገባል ብለው የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት በዘር ማጥፋት ለመወንጀል ተዘጋጅተው የነበሩት የውጭ ኃይሎች በመንግስት በሳል ውሳኔ ለጊዜውም ቢሆን አላማቸው እንዳይሳካ ተደርጓል፡፡ ትግራይ ይገባል ሲባል የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ትግራይ እንደማይገባ መንግስት አስታውቋል፡፡
የወገን ጦር አሁን ላይ የያዘውን ቦታ አፅንቶ እንዲቆይ የታዘዘበት 3 መሰረታዊ ጉዳዮችም ከዚህ ቀደም መከለከያ ሰራዊቱ በትግራይ በነበረበት ጊዜ የተፈፀመበትን ክህደት መነሻ በማድረግና ካለፈው መማር ስለሚያስፈልግ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት በአስከሬን የመነገድ እቅድን እንዳሰበ ስለተደረሰበት ነው ተብሏል፡፡
ቡድኑ የተገደሉበትን ታጣቂዎች ሬሳ የቻለውን ሁሉ ጭኖ በመሸሹና የመንግሥት ኃይል ወደ ትግራይ ሲገባ መንግሥት በትግራይ ጅምላ ጭፍጨፋ ፈፀመ በሚል ዓለም ዐቀፍ ተቋማትን አሳስቶ በኢትዮጵያ ላይ ክስ እንዲመሰረት ለማድረግ ነው፡፡ መንግሥት የአገሪቱን የግዛት አንድነት የመጠበቅ ሙሉ ኃላፊነቱን ለመወጣት በየትኛው ጊዜ ወደ ትግራይ ክልል እየገባ እርምጃ መውሰድ እንደሚችል የሚታመን መሆኑም 3ኛው ምክንያት ተብሏል፡፡
ወያኔ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ላይ በፌዴራልም ሆነ በክልል ስልጣን ይዞ የመቀጠል እድሉ የተዘጋ ፋይል ሆኗል፡፡ ወራሪው ሃይል የትግራይን ህዝብ በተለይ ከአማራና ከአፋር ህዝብ ጋር ደም አቃብቶታል፡፡ ወያኔ እስከወዲያኛው ተወግዶ ይህ ቂምና የበቀል ስሜት ሊሽር ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የትግራይ ልሂቃን ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ቡድኑ ከማንም በላይ እየጎዳ ያለው የትግራይን ህዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ዘርፈው ቢሊየነር የሆኑ ጥቂት የወያኔ መሪዎችን ለመታደግ ተብሎ የትግራይ ህዝብ አላስፈላጊ መስዋእትነት መክፈል አይኖርበትም፡፡ የእነዚህን ሰዎች አጥፊነት የትግራይ ልሂቃን ሊገነዘቡና ህዝቡን ከጦርነት እንዲታቀብ ሊያደርጉት ይገባል፡፡
የሽብር ቡድኑ አላማ ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን በይፋ ተናግሯል፡፡ ይህንን ደግሞ የትግራይ ህዝብም አይቀበለውም፡፡ ለጊዜው ህዝቡን “አማራና አፋር ተባብረው ሊያጠፏችሁ ነው” በሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ህዝቡን ለጦርነት ማግደው እያስጨረሱት ይገኛሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የትግራይ ልሂቃን ይህንን ሁኔታ የመለወጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሠላም ያስፈልገናል፡፡ ሠላም ደግሞ በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ሊመጣ የሚችል አይደለም፡፡ ለትግራይ ህዝብ ጥቅም በተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የተደራጁ ተጋሩዎች፣ የትግራይ ባለሃብቶች፣ ምሁራንና የሃገር ሽማግሌዎች ከወያኔ ተፅእኖ ነጻ ሆነው ስለ ትግራይና በአጠቃላይ ስለአገራችን ዘላቂ ሠላም ሊመክሩ ይገባል፡፡ በጥቂት ቡድኖች ፍላጎት የማንፈልገው ጦርነት ውስጥ ገብተን ብዙ ተጎድተናል፡፡
በሃገራችን ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ በማናውቀው ሁኔታ በወያኔ አጋፋሪነት በአማራና በአፋር ህዝቦች ላይ ጄኖሳይድ ተፈጽሟል፡፡ ይህንን ወንጀል ያስፈጸሙና የፈጸሙ ሁሉ ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ መጀመሪያ ግን ጦርነቱ አብቅቶ የትግራይ ልሂቃን ከህዝባቸው ጋር ሊመክሩና የህዝቡን ሃሳብ ይዘው ከመንግስት ጋር ለውይይት ሊቀመጡ ይገባል፡፡