በውብ የአማርኛ ድርሰት በአማራዎች ሕይወት ላይ ቅጣት በይኖ ያለፈው ደራሲ
(አሳዬ ደርቤ.~ ድሬቲዩብ)
ተስፋዬ ገብረ አብን ግለጸው ብባል ‹‹ጦርን እንደ ብዕር፣ ደምን እንደ ቀለም፣ የፈጠራ ድርሰትን እንደ እውነተኛ ትርክት በመጠቀም በሚገርም አማርኛ በሚጽፋቸው የፈጠራ ታሪኮች አማራዎችን ለስቃይና ለሕመም ሲዳርግ ኖሮ ያለፈ ደራሲ›› በማለት ነው፡፡
አዎ ተስፋዬ ገብረ አብ በተሰጠው የጥበብ ዛር እርኩሱን ቅዱስ ሲደርግ፣ ቅዱሱን ደግሞ ማርከስ የሚችል ጸሐፊ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘም ፍቅርን የተለያዩ ደራሲዎች በተለያየ የአጻጻፍ ስልት ቢተርኳትም ጥላቻን ግን በተስፋዬ ገብረ አብ ልክ ጣፋጭ አድርጎ የጻፋት ደራሲ አገራችን ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ተስፍሽ ጥላቻን በውብ ቃል ተርኮ ድርሰት ብቻ ሳይሆን ሐውልትም ጭምር ማድረግ የቻለ ደራሲ ነው፡፡
ተስፋዬ ገብረ አብ ስለሚጠላው ግለሰብም ሆነ ሕዝብ ሲጽፍ አንባቢዎቹ ልብ ውስጥ ጥላቻውን የማውረስ አቅም አለው፡፡ በግለሰብ ደረጃ የሚጠላውን ወይም ደግሞ የተጣላውን አመራርም በሕዝብ የሚጠላ ማድረግ ይችልበታል፡፡ የሚንቀውን ማስናቅ፣ የሚያደንቀውን ማስደነቅ ተክኖበታል፡፡ ቡርቃ ወንዝን ማድረቅና ጸጥ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ተራራን ማንቀጥቀጥም ይችልበታል፡፡ በጥላቻ ትርክቱ ነጋ ጠባ በጨቋኞች በትር የሚቀጠቀጥ ትውልድ እንዳፈራው ሁሉ በአድናቆት ቃላቱ ደግሞ ተራራን የሚያንቀጠቅጥ ትውልድ ሕያው የማድረግ ችሎታ አለው፡፡
ያም ሆኖ ግን ተስፋዬ ድርሰትን እንጂ እውነትን አያውቃትም፡፡ አማርኛን እንጂ አማራዎችን አያውቃቸውም፡፡ ለአንድ ጸሐፊ ደግሞ ከጥበብ መክሊት በላይ እውነት ምሰሶው መሆን ይኖርባታል፡፡ የአንድን ማሕበረሰብ ቋንቋን ወርሶ በቃል ከመራቀቅ ባለፈ ሕዝቡን፣ ባሕሉን፣ ማንነቱንና ሐይማኖቱን ማወቅ ይገባዋል፡፡
ተስፋዬ ግን አማርኛን የሚራቀቅበትን ያህል ሕይወቱ እስካለፈችበት ቅጽበት ድረስ አማራዎችን ለማወቅ አልሞከረም፡፡ ድርሰቱን ሲያበረክት ያለፈውን ታሪክ ለማጥናትም ሆነ በገሃድ የነበረውን እውነት ለመመርመር አላሰበም፡፡ በእሱ የጥላቻ ድርሰት የተቀየሙትን ከመጥላት ባለፈ በእሱ ጽሑፍ ሲጨፈጨፍ የኖረውን ምስኪን ሕዝብ ይቅርታ ለመጠየቅ አልደፈረም፡፡
እናም ባንድ ወቅት ተስፍሽ አማራ ጠሉ ሥርዓት ውስጥ በኃላፊነት ስፍራ የመቀመጥ እድሉን ያገኘ ቀን አለቆቹ የሚጠሉትን ከመጥላት ባለፈ ሁለት ሕዝቦችን የሚያባላ ድርሰት ቢያበረክትም በዚያ ትርክቱ ግን አማራዎችን ሲጎዳ አለቆቹን እንጂ ኦሮሞዎችን አልጠቀመም፡፡
በጥላቻ ትርክት የጥላቻ ሐውልት አስተክሎ ከሁለቱ ሕዝብ የወጡ ኤሊቶችን እያባላ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ያበላው እንብርት የለሹን ቡድን ነው፡፡ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የእሱን ትርክት የሚያፈራርስና ልዩነትን እየዘራ ሥልጣኑን የሚያስቀጥለውን ሥርዓት የሚደመስስ የኦሮ-ማራ ጥምረት እስኪፈጠር ድረስ ህውሓቶችን እንጂ ኦሮሞዎችን አልጠቀማቸውም፡፡ ይልቅስ ተስፋዬ ያደረገው ብቸኛ ነገር ቢሆን በፈጠራ ትርክት ሥልጣን ላይ የሌለውን ሥርዓት ከመቃብር ቀስቅሶ በትውልዱ ልብ ውስጥ በመሰንቀር በጊዜው ወንበር ላይ የነበረው ሥርዓት የሚፈጽመው ግፍ እንዳይታወስ ማድረግ ብቻ ነበር፡፡
የቡርቃ ዝምታን ወደ ጎን ትተን የደራሲው ማስታወሻ የሚል መጽሐፉን ስንመለከትም የምናገኘው ተመሳሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ የቡርቃ ዝምታ ዋነኛ ዓላማው ጬቤ ብዕሩ የሆነ ሕዝብ ላይ ማነጣጠሩ ሲሆን እኒህኞቹ ማስታወሻዎች ደግሞ በግለሰብ ደረጃ የተጣላቸውን አመራሮችና ታዋቂ ሰዎች በሕዝብ የተጠሉ ማድረግን ታሳቢ አድርገው የተጻፉ መሆናቸው ነው፡፡ የሾሙት ቀን ‹‹ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ›› በሚል መጽሐፍቱ ካሞገሳቸው አመራሮች መሃከል በሆነ አጋጣሚ ያስቀየሙትና ከሥልጣኑ ያባረሩትን ለይቶ የሚቀጠቅጥባቸው መሆናቸው ነው፡፡ እነ ጄኔራል ጻድቃንንን የጦር መሪዎች አድርጎ የእነ ሌ/ጄ ባጫ ደበሌን ማዕረግ የሚቀማባቸው መሆናቸው ነው፡፡
የሆነው ሆኖ የጥላቻ አባት የሆኑት መምህር ገብረ ኪዳን ባለፉበት ወር ተስፋዬ ገብረ አብም ተከትሏቸው ሄዷል፡፡ በእነሱ የጥቻላ ትርክት የሚጨፋጨፈውን ሕዝብ ትተው በእነሱ ስብከትና ድርሰት በጠፉት ነፍሶች ወደሚከሰሱበት ዓለም ተጉዘዋል፡፡ እናም ፍርዱን ለአምላክ ትተን በልባችን ውስጥ የዘሩት የጥላቻ ሰብል ግን አብሯቸው ወደ መቃብር ይወርድ ዘንድ እመኛለሁ፡፡