Connect with us

በሰላም ጊዜ ለጦርነት መዘጋጀት

በሰላም ጊዜ ለጦርነት መዘጋጀት
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

በሰላም ጊዜ ለጦርነት መዘጋጀት

በሰላም ጊዜ ለጦርነት መዘጋጀት

(ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት)

“Si vis pacem, para bellum”  ጥንታዊ የሆነ የላቲን አባባል ነው።  “ሰላምን ከፈለግህ ለጦርነት ተዘጋጅ” ማለት ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካ መከላከያ ዋናው መርሕ መሆኑ ይነገራል። ጦርነት የተደረገበት ሀገር ምን እንደሚመስል ከአውሮፓ ያዩት አሜሪካውያን “ጦርነት ወደ አሜሪካ እንዳይመጣ፣ አሜሪካ ወደ ጦርነት ቀድማ ትሂድ” በሚል መርሕ ኖረዋል። የሀገራችን ገበሬም “የቅርብ ጠላት ያለው ሰው ጠመንጃውን አርቆ አይሰቅልም” ይላል። ወትሮ ዝግጁ መሆንን ሲያመለክት ነው።

የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መጪው ዘመን መቃኘት ያለበት  በዚህ መርሕ ቢሆን ጥሩ ነው። ሰላምን ፍለጋ ለጦርነት በመዘጋጀት።  ኢኮኖሚያችን፣ ዲፕሎማሲያችን፣ መከላከያችንና አኗኗሯችን ወትሮ ዝግጁነትን መሠረት ማድረግ አለበት። አጥብቆና አልቆ ለክፉ ቀን በመዘጋጀት።

ወጣቶቻችን በደኅና ጊዜ አምራች በክፉ ጊዜ ዘማች ሆነው በወታደራዊ ሰብእና መዘጋጀት አለባቸው። ኢኮኖሚያችን በክፉ ጊዜ ሊነቀነቅ የማይችል ሆኖ ዐቅሙን መገንባት አለበት። የምናመርተው ምርት መትረፍረፍ ያለበት ክፉ ጊዜን እንዲሻገር ሆኖ ነው። ብሔራዊ የውጭ ምንዛሬ ተቀማጫችንን ስናስብ ነገ በሩ ሁሉ ቢዘጋ እንድናስከፍትበት ሆኖ ነው። ሌሎችን ፈላጊ ብቻ ሳትሆን በሌሎችም ዘንድ ተፈላጊ ሀገር መገንባት ይገባናል።

ለስፖርት፣ ለእግር ጉዞ፣ ለአካል ብቃትና ለወታደራዊ ሥልጠና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ ማኅበረሰብ ሊኖረን ይገባል።  “ዓለም አቀፍ” የምንላቸው ሚዲያዎች በክፉ ቀን እንደ ሸረሪት ጥለውን መጥፋታቸውን ካየን ዓለምን የሚያዳርስ ሚዲያ መገንባት ነው አማራጩ።  በየሀገሩ የተበተነው ኢትዮጵያዊ ራሱን ለብቁ ዲፕሎማትነት ማሠልጠን አለበት። የየሀገሩ የኮሚኒቲ አደረጃጀቶች ለክፉ ቀን በሚሆን መልኩ ራሳቸውን ማዋቀር አለባቸው። የኢትዮጵያ ጉዳይ የአሜሪካና የአውሮፓ የምርጫ መወዳደሪያ መሆን ይገባዋል።

መከላከያችንን መገንባት ያለብን ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት እንዲያሸንፍ አርገን ነው። የራሳችንን መሣሪያ ማምረት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂ መፍጠር፣ ለመከላከያ የምንሰጠውን ክብርና ጥቅም ማሳደግ፣ መከላከያ የምርምርና የፈጠራ ማዕከል እንዲሆን ማድረግ አለብን።

አንድነት የሀገራችን የመልካም ጊዜ ማረፊያ የክፉ ጊዜ ማለፊያ ነው። ከአንድነታችን በላይ ኢትዮጵያን ከመከራ የሚያሻግር ዕሴት የለም። በማንኛውም ሁኔታ የሕዝቡን አንድነት የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ይሁነኝ ብለን መሥራት አለብን። አንድነት – ሰላምን ፍለጋ ለጦርነት የምንዘጋጅበት መርሕ ቋሚ ዓምድ ነው። ትምህርታችን እርስ በርስ እንድንተዋወቅና እንድንደናነቅ ማድረግ አለበት።  ከሶማሌ ተነሥቶ አፋር እየሞተ፣ ከሐመር ተነሥቶ አማራ እየሞተ፣ ከጎንደር ተነሥቶ ወለጋ እየተሠዋ አይተናል። ከባሌ ተወልዶ ጎንደር፣ ከሶማሌ ተወልዶ አፋር፣ ከዋግ ተወልዶ ወለጋ፣ ከወላይታ ተወልዶ ሶማሌ ያለ ችግር የሚኖርበትንና የሚሠራበትን መፍጠር ግን ይቀረናል። በሚሞትበት ቦታ እንዳይኖርበት መከልከል ለክፉ ቀን አያዛልቀንምና!

የጤና ተቋሞቻችን በዐቅምና በአደረጃጀት ክፉን ቀን እንዲሻገሩ ማብቃት አለብን።  የሕክምና መሣሪያዎችንና መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ለነገ አይባልም። ተንቀሳቃሽ ክሊኒክና ሆስፒታል ሊኖረን ይገባል። ባህላዊ ሕክምና ለክፉ ቀን ብቁ ሆኖ ዛሬ ቦታ ሊያገኝ የግድ ነው።

ብቻ ነገሩ ብዙ ነው፤ በጦርነት ጊዜ ለጦርነት መዘጋጀት ከባድ ነው። በሰላም ጊዜ ለጦርነት መዘጋጀት ግን ቢቻል ጦርነትን ያስቀራል፤ ባይቻል በአነስተኛ መሥዋዕትነት እና በፈጣን ጊዜ ለማሸነፍ ይጠቅማል። እሥራኤላውያን ተዘልለው በተቀመጡ ቁጥር መጠቃት ሰልችቷቸው ነው ወትሮ ዝግጁ የሆነ ማኅበረሰብ የገነቡት። አይመጣምን ትተን ይመጣልን አስበን፣ በሰዓታት ውስጥ ከአምራችነት ወደ ዘማችነት የሚቀየር ሕዝብና ሀገር እንገንባ። ከእንግዲህ ለእኛ ያለነው እኛው ነን። እንደ ሞኝ አንድ እባብ ሁለት ጊዜ ሊነድፈን፣ አንድ ዕንቅፋት ሦስቴ ሊመታን አይገባም። ሰላምን ከፈለግን ለጦርነት እንዘጋጅ።

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top