Connect with us

የደሴ ሙዚየም ዘረፋ፣ ውድመትና ጥፋት!!

የደሴ ሙዚየም ዘረፋ፣ ውድመትና ጥፋት!!
ሄኖክ ስዩም

ነፃ ሃሳብ

የደሴ ሙዚየም ዘረፋ፣ ውድመትና ጥፋት!!

የደሴ ሙዚየም ዘረፋ፣ ውድመትና ጥፋት!!

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

ስለደሴ ሙዚየም እየነገርኳችሁ ነው፡፡ እዚያ ስደርስ ለማመን አቃተኝ፡፡ ያ ውብ ቅጥር የቢራ ጠርሙስ ተከስክሶበታል፡፡ በዘር ጥላቻ በሰከረ ወራሪ ላይ የቢራ ስካር ተደምሮ የሚሆነውን ማሰብ ነው፡፡

ደሴ ሙዚየም የክፍለ ሀገሩ ነው፡፡ ከስምጥ ሸለቆው የከሚሴ ምድር እስከ ራያ መገለጫዎችን ይዟል፡፡ ሲደርሱ በጥርሳቸው የነከሱት፣ በጥፍራቸው የቧጠጡት ጠላት እስኪመስል አውድመውታል፡፡ ደጃፍ ላይ ላነደዱት እሳት ባቢሊያን የተጠበበትን ግንባታ ለማገዶ አፍርሰውታል፡፡

ደሴ ሙዚየም ሸዋ በር ራስጌ ይኑር እንጂ የሀገር ቅርስ የያዘ የስብስብ ሀብታም ነበር፡፡ ዛሬ እሱ ሁሉ የለም፡፡ ከመጀመሪያዎቹ ስልክ ቀፎዎች አንዱ የሆነው ታሪካዊ ማስታወሻ ከተቀመጠበት የለም፡፡

ደሴ ሙዚየም አፍሪቃዊ ነው፤ አፍሪቃ የሚኮራበት የአድዋ ድል የታሪክ ማስታወሻዎች በክብር ከተቀመጡበት መካነ ቅርስ አንዱ ነበር፤ አድዋ ጦርነት ላይ ያገለገሉ የጥቁር ድል አጋር የጦር መሳሪያዎች ተዘርፈዋል፡፡ ለምሳሌ የንጉሠ ነገሥቱ የምኒልክ የጦር ሜዳ መነጽር ተወስዷል፡፡ ያ ዐፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ያጠፉበት አይነት ሽጉጥ ደሴ ሙዚየም ከመሳሪያ ትዕይንት ክፍሉ ጋር ይታይ ነበር፤ ዛሬ የለም፡፡

ከሁሉም ያዘንኩት የአርኪዎሎጂ ቅርሶች ጋር ስደርስ ነው፡፡ እነኚህ የሸክላ ውጤቶች ናቸው፡፡ በቁፋሮ ነው የተገኙት፡፡ ፈረንሳዮች ባደረጉት ጥናት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር የተገኙ የአራት መቶ ሃምሳ አመታት እድሜ ያላቸው የታሪክ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ወራሪው ሰባብሯቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሀርቡ ከሚባለው አካባቢ የተገኙ መሰል የአርኪዎሎጂ ግኝት የሸክላ ውጤቶች እንዲሁ ሆን ተብለው እንዲበላሹ ተደርጓል፡፡  

በደሴ ሙዚየም የሚገኙት የቅርስ ስብስቦች ዓይነታቸው ይለያያል፡፡ አንዳንዱ የአካባቢውን እሴት ያሳያል፣ ለምሳሌ ባህላዊ አለባበስ፤ ወራሪው ከክፋቱ የተነሳ ለትዕይንት ከቆመ አሻንጉሊት ላይ ልብስ ገፎ ይቀዳል፡፡

እንደ ጥበበ ዕድ ምርትና እውቀት ማሳያዎቹን አውድሟል፡፡ ጋሻና ጦሮቹን ዘርፏል፣ አጥፍቷል፡፡ የሙዚየሙ ግድግዳዎች የተቀበረ ነገር ካለባቸው በሚል ቀባሪ መንፈሱ ነግሮት ምንም ነገር ላያገኝ አፍርሷቸዋል፡፡

ለምን ይሄ ሁሉ ሆነ ብሎ አሁንም የሞኝ ጥያቄ ማንሳት ሞኝነት ነው፡፡ ዞር ብዬ ስመለከት የንጉሥ ሚካኤል የፈረስ ኮርቻ ሜዳ ወድቆ አየሁ፡፡ የማይወድቅ ታሪክ ቢኖረንም በጣሉት ቅርስ የወደቀው የእነሱ ሰብዕና እንደሆነ ለማየት ቻልኩ፡፡

የሙዚየሙ ቅርሶች ብቻ ሳይሆኑ ንብረት ክፍሉ ቢሮዎቹና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ክፍሎቹም አብረው ተመዝብረዋል፡፡ ተዘርፈዋል፡፡ ወድመዋል፡፡

በሌላ በኩል ለወግ ዕሴቶች ማሳያ በሚል ለትዕይንት የቀረቡ ቅርሶች ተዘርፈዋል፣ የማይፈልጓቸውን ደግሞ ደግመን እንዳንፈልጋቸው አውድመዋቸዋል፡፡ የአፋርን ህዝብ የሚያሳየው የትዕይንት ክፍል ብዙዎቹ ስብስቦች ተዘርፈዋል፡፡

የሙዚየሙ መልካም መገለጫ ከሚባለው ክፍል አንዱ የነበረው የዱር እንስሳት ቅሪት ማሳያ ቢሞቱም እንኳን የአማራ ሀገር ቅርሶች በሚል ነብሩንና አዞውን ጭምር የማውደም ስራ ሰርተዋል፡፡ በታክሲ ደርሚ የደረቀ እንስሳ አንገት ቀንጥሰዋል፡፡

ቀና ብዬ ግድግዳዎቹን አየሁ፡፡ ጽፈውባቸዋል፡፡ የመሪያቸውን ስም ጽፈዋል፡፡ እውነት ነው፣ ጥፋት ካለ የመሪያቸው ስም አለ፡፡

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top