የአጎዋ ጉዳይ!..
(ሙሼ ሰሙ)
የባይደን አስተዳደር ለኢትዮጵያ ተፈቅዶ የነበረውን የአጎዋ ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚነት ሰርዟል፡፡ እ.ኤ.አ በ2020 ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶችን ወደ አሜሪካ በመላክ 238 ሚሊየን ዶላር አግኝታለች፡፡ ይህ ማለት ከአጠቃላይ የሀገራችን ኤክስፖርት ውስጥ 7 በመቶ ገደማ ሲሆን ወደ አሜሪካ ከምንልከው 525 ሚሊየን ዶላር ውስጥ 45 ነጥብ 34 በመቶ ነው፡፡ በተቃራኒው አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የምትልከው ምርት 868 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን የንግድ ሚዛኑ በ343 ሚሊየን ዶላር ወደ አሜሪካ ያጋደለ ነው
አሜሪካንን ከማማረር ይልቅ ከስራ ለሚሰናበተው በ100 ሺ የሚቆጠረው ሰራተኛ የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ማዕቀቡ የሚያስከትለውን ጉዳት በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለማካካስ የሚስችል አማራጭ እስክናገኝ ድረስ እቀባው በአጭር ጊዜ ሊደቅንብን የሚችለውን ፈታና እንዴት እንቋቋመው የሚለው ጥያቄ ዋነኛ መወያያችን መሆን አለበት፡፡
ለጊዜው ብዙ አማራጭ ያለን አይመስለኝም፡፡ ይህም ሆኖ፣ በመካከለኛ ጊዜ ሊሰሩ የሚችሉ አዳዲስ ገበያን የማፈላለግ፣ በረጅም ጊዜ ደግሞ የሚገነቡ የኤክሰፖርት አቅማችንን የማሳደግና በራስ አቅምና ምርት የመተማመን አማራጮች እስኪጎለብቱ ድረስ አንድ ሁለት ነገሮች ማመላከት ይቻላል፡፡
1) የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱን መሰረታዊ ለሚባሉ አቅርቦቶች ብቻ ማዋልና ጊዚያዊ ፍላጎቶቻችንን በመግታት የውጭ ምንዛሪ ፍጆታን መቆጠብ፣
2) ኢምባሲዎች፣ ቆንስላዎች፣ የተለያዩ የዲያስፖራ ኮሚኒቴዎችንና የኢትዮጵይ ተቆርቋሪ ማህበረሰቦችን በማስተባበር ከምንጊዜውም በላይ ገበያ የማፈላለጉን ስራ በስፋት፣ ተከታታይነት ባለው መንገድና በቁጭትና በተደራጀ መልኩ ማካሄድ፣
3) የኤክሰፖርት ገበያው ላይ ያለውን ውስብስብ ችግር በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍትሔ በመስጠትና በርካታ ዜጎች በኤክሰፖርት ስራ፣ በተለያየ አቅምና የምርት አቅርቦት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የሚያበረታቱ የብድር፣ የታክስ፣ የቦታ አቅርቦትና ሌሎች የድጋፍና የማበረታቻ መንገዶችን ለአጭር ጊዜ በገደብ ማመቻቸት ሲሆን
ሌላውና መሰረታዊ ጉዳይ፤ እስካሁን 13 ሺ ከሚደርሱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን 3 ሚሊየን ዶላር መሰባሰብ እንደተቻለ ተዘግቧል፡፡ ከአጠቃላይ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አኳያ የፈቃደኞች ቁጥር ጥቂት ቢሆንም በነዚህ ጥቂት በጎ አሳቢ ዜጎች ተነሳሽነት ምክንያት ቀላል የማይባል ሀብት መሰብሰቡን መረዳት ይቻላል፡፡
አንዱ ችግሩ የማያቋርጥ የመዋጮ ጥያቄ መሆኑ ይመስለኛል (Donner Fatigue)። መንግስት ይህንን አሰራር በጊዜ ገደብ ወደ የሚመለስ የቦንድ ሽያጭ በማሳደግ የአንድ ዓመት የአጋዋ ኤክስፖርታችንን ያህል የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ በዘለቄታው የሚሰሩ ስራዎች መፍትሔ እስኪሰጡ ድርስ አንድ ሚሊየን ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በማስተባበር እያንዳንዳቸው በአማካይ 500 ዶላር የሚያወጣና በተለያየ የግዢና የክፍያ ስርዓት የሚሰበሰብና ተመላሽ የሚሆን ቦንድ ቢገዙ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ ከዲያስፖራ በመበደር (Revolving Fund) የእፎይታ ጊዜ ማግኝት ይቻላል፡፡
የእፎይታ ጊዜው በሚሰጠው ትንፋሽ ውስጥ ሆነን ከላይ የቀረቡትን አማራጭ ስራዎች ያለማሰለስና በንቃት ከተሰራ በራስ አቅም የችግሩን ውስብስብነት ከመቀነስ ባሻገር አደጋውን እስከ መቀልበስ የሚሻገር ዘላቂ ውጤት ማግኘት ይቻላል።