Connect with us

የኛ ቄስ፣ የኛ ሼህ፣ የኛ ፓስተር፣ የኛ ሽማግሌ የምንለውን፤

ነፃ ሃሳብ

የኛ ቄስ፣ የኛ ሼህ፣ የኛ ፓስተር፣ የኛ ሽማግሌ የምንለውን፤

የኛ ቄስ፣ የኛ ሼህ፣ የኛ ፓስተር፣ የኛ ሽማግሌ የምንለውን፤
እንደ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ያሉ የጋራ አባቶችን ያብዛልን፡፡

(ስናፍቅሽ አዲስ~ ድሬቲዩብ)
የወልዲያው ሙስሊም የእኛ ቄስ ሲል ሰማሁት፡፡ እውነቱን ነው፤ አቡነ ኤርሚያስ የእኛ ናቸው፡፡ የእኛ ማለት የሁላችን፣ የአንድ ቤተ እምነት አባት ቢሆኑም ለሁሉም ቤተ እምነት እኩል ልብ፣ እኩል ፍቅር፣ እኩል ስስት ያላቸው፡፡

ትህነግ የወሰደችብንን ብንቆጥረው ዘመናት የሰኮንድ ያህል አጥረውን ይቀራሉ፡፡ አካባቢያችንን ብንመለከት የሰፈራችንን ሽማግሌዎች ነጥቃናለች፡፡ እዛኛው ሰፈር ትርጉም እንዳይኖራቸው አድርጋ ሰፈራችንን አውራ አልባ አድርገዋለች፡፡ በተመሳሳይ የቤተ እምነቶችም ጉዳይ እንዲሁ ነው እንኳን የአንዱ ቤተ እምነት አባት ለሌላው ሊተርፍ ይቅርና በራሱ ቤተ እምነት ውስጥ ክብር ፍቅርና ህብረት እንዳይኖረው አድርጋለች፡፡

ቤተ ክህነቱን ፈትፍታበታለች፤ ሀገር እያየና እየሰማ እስልምና አስተማሪ ሆናለች፡፡ ድምጻችን ይሰማ ያለውን ጥይት አሰምተዋለች፡፡ በሃያ ሰባት አመት የስቆቃ ዘመን አባት ብርቅ፣ እሴት እንግዳ ነገር እንዲሆንብን ያደረገች መአት ናት፡፡
ቀዳሚ ሙፍቲ ወደ አደባባዮቹ ብቅ ሲሉ ክርስቲያኑ ሁሉ አባታችን አለ፡፡ እንዲህ ያለ አባት ተርበን የኖርን ነው፤ እንደ መርከቡ፣ ግድቡ፣ ህንጻውና አንድነታችን ሁሉ ወያኔ አባቶቻችን ነጥቃናለች፡፡ አባት የለሽ አድርጋናለች፡፡ አባትና ሽማግሌ የተራብን ህዝቦች ነን፤

ለዚህ ነው ቀዳሚው ሙፍቲ አባታችን የሆኑልን፣ ሲናገሩ ያደመጥነው፣ ድምጻቸው መስጂድ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ጣሪያ ትርጉም ያለው የሆነው፣ አቡነ ኤርሚያስ እንደ ቀዳሚ ሙፍቲ የእኛ የሚባሉ አባት ናቸው፡፡

የወልዲያ ሙስሊሞች የእኛ ቄስ እያሉ የሚጠሯቸው አባት ተግባር ድንቅ ነው፡፡ ቦታቸውን አልለቀቁም፣ ስለ ቤተስኪያኑ እንጂ ስለመስጂዱ አያገባኝም አላሉም፡፡ እኔ የሀገሬው አባት ነኝ ብለው አባትነታቸውን ኖረው አሳዩት፡፡

ምልክቶቻችን እንዲህ ያሉ አባቶች ከሆኑ የማናልፈው መከራ የማንወጣው ችግር የለም፡፡ ምልክቶቻችን የጋራ አባቶች ከሆኑ የጋራ ነገሮቻችን በልጠው ልዩነቶቻችን ይጠፋሉ፡፡ የጋራ አባት የጋራ ሀገር እንዲኖረን ያደርገናል፡፡

ሁላችንም የእኛ የምንላቸውን አባቶች እንመኛለን፡፡ ሙስሊሞች ባንሆንም የእኛ ሼህ የምንለው አባት ያስፈልገናል፡፡ ኦርቶዶክሶች ባንሆንም የእኛ ቄስ የምንለው አባት ያስፈልገናል፡፡ የእምነቱ ተከታዮች ባንሆንም የእኛ ፓስተር የምንለው ፓስተር ያስፈልገናል፡፡ እንዲህ ያሉ ምልክቶች ለጋራ ጥቅማችን፣ ለጋራ ህልውናችን፣ ለጋራ ደህንነታችን የሚቆሙ ናቸው፡፡

እንደ እምነት አባት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው እንዲህ የእኛ በሚባል ያለ ልዩነት ለሰው በሚቆም ሰው መቅናት ጤናማ ነገር ነው፡፡ አቡነ ኤርሚያስ ያስቀናሉ፤ ምነው እንደሳቸው ባደረገኝ የሚያስብሉ ናቸው፡፡

እንደ እሳቸው ያሉ የእኛ አባቶች እዚህም እዚያም ቢበዙ እዚህም እዚያም መልካም ይሆናል፡፡ የእኛ የምንላቸው አባቶች የሀገር ምልክት፣ የእርቅ መንገድ፣ የፍቅር መገለጫዎች ናቸው፡፡ የወል ጥቅሞቻችን በወል አባቶቻችን በኩል የሚገኙ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ የእኛ የሚባል አባት መሆን ክብሩን አይተነዋል፡፡

የወልዲያ ሰዎች የእኛ ያሏቸውን አባት ሲያመሰግኑ እንባ እየተናነቃቸው ነበር፤ እንባ አምጠው የእኛ ያሉትን አባት ምስክርነት ነግረውናል፡፡ ሁላችንም የምንመሰክርላቸው እንዲህ ያሉ የእኛን አባቶች ያብዛልን፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top