Connect with us

ከሊቅ እስከ ደቂቅ የማጥፋት ምኞትና የመንዝ ጓሳ ውድመት፤

ከሊቅ እስከ ደቂቅ የማጥፋት ምኞትና የመንዝ ጓሳ ውድመት፤
ሄኖክ ስዩም

ነፃ ሃሳብ

ከሊቅ እስከ ደቂቅ የማጥፋት ምኞትና የመንዝ ጓሳ ውድመት፤

ከሊቅ እስከ ደቂቅ የማጥፋት ምኞትና የመንዝ ጓሳ ውድመት፤

ከአይጥ ጉሬና ከቀበሮ ሜዳ እስከ ጓሳ ማውደም፡፡

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

ጓሳ ነኝ፡፡ ያ ውብ መልከዓ ምድር ጥቁር ለብሷል፡፡ ከል መስሎ ተንጣሏል፡፡ ጓሳው ነዶ መንዜው በቁጭት ጨሷል፡፡ ይህ በዓለም ፊት በማኅበረሰብ እሴት ተጠቅሞ ሀገር የመጥቀም ላብራቶሪ ነበር፡፡ ቢኖር ከአጋመ እስከ አንደርታ፣ ከአክሱም ጫፍ እስከ አጽቢ ወንበርታ ያለ ገበሬ የሚማርበት ህያው ተቋም ነበር፤

እናንተ ስለ ሰው መኖሪያ ውድመት ሰምታችኋል፡፡ አማራ ምድር ላይ የሚኖሩ ጭላዳዎች አትኖሯትም ይመስል መዋያቸው ወድሞ አየሁ፡፡ መንዝ ጓሳን ለምን? እዚህ እንዲህ ያለውን ተፈጥሮ ከማውደም ጀርባ ምን ቅዠትስ ይሳካ ይሆን?

እንደ ፍራንክፈርት ያሉ ተቋማት፣ እንደ ዶክተር ዘለዓለም ያሉ የማህበረሰብ አካባቢ ጥበቃ ጽንሰ ሀሳብ ተግባሪዎች፣ እንደ ወልዴ ያሉ ደም ተፍተው ሰው ከምድሩ እንዲጠቀም ያደረጉ ብዙዎች የለፉበት ነበር፡፡

የተመለከትኩት ነገር ልቤን ሰብሮታል፡፡ ያ የመጣውን የሚቀበለው ሎጂ እንዳልነበር ሆኗል፡፡ ቁሳቁሱ ሜዳው ላይ ተበትኗል፡፡ የጌራ ምድር ጀግኖች አብሮ ቆሞ አብሮ መጠቀምን ያሳዩበት የክህሎት አምባ ተመዝብሯል፡፡ ወድሟል፡፡

እንደ ክሊኒኩ፣ እንደ ሆስፒታሉ፣ እንደ ዩኒቨርሲቲው ሁሉ የአይጥ ጉሬው ሳይቀር መውደም ተፈርዶበታል፡፡ መንዝ ጓሳ የአይጦች ምድር ነው፡፡ ያ ተፈጥሮ ሲቃጠል ሲወድምና ሲጠፋ ዓላማውን አካባቢውን በማጥፋት የነዋሪውን ተስፋ ደስታና ጥረት ማጥፋት ነው፡፡

አይጡን በጎሬው አቃጥለው፣ ጭላዳውን አሳደው፣ ቀይ ቀበሮው የሚበላውን አሳጥተው፣ ጓሳውን አውድመው ሎጁን አፈራርሰው የአስራ ሰባት ቀበሌ የወዝ ድካም ሜዳ ለማስቀረት ያሰበ፣ አስቦም የቻለውን ያደረገ ጭካኔ ነው፡፡

መንዝ ጓሳ በዘመነ ኮሮና ሳይቀር የጎብኚ እግር ሳይለየው የኢትዮጵያ የማህበረሰብ አቀፍ ጥበቃ ቦታ የልቀት ማሳያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ተፈጥሮ አዋሽን የሚታደግ የተፋሰስ ኮርብታዎች ብዝሃ ህይወት ቅጥር ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የብዙ ሺህዎች ልብስና ጉርስ፤

ትናንት እነኚህ ጎበዝ ገበሬዎች የሶስት መቶ ሃምሳ አመት ክብርና ታሪክ ያለውን የተፈጥሮ ጥበቃ ስፍራ ነፍስ ዘርተውበት የኢትዮጵያ መስህብ አድርገውታል፡፡ ተሸልመውበታል፡፡ ተመስግነውበታል፡፡ ነገም ይሄ ታሪክ እውን ይሆናል፡፡

ገንዘብ የማይተምነው ብዝሃ ህይወት ወድሟል፡፡ የመንዝን አይን ለማጥፋት ጓሳው ላይ ጣትህን ጠንቁል የሚለው ሴራ ተሞክሯል፡፡ የመንዝ ዓይን የበለጠ ቢያይ እንጂ ከሚጓዝበት የብርሃን ህይወት የሚቀለብሰው አይኖርም፡፡

የቱሪዝም ቤተሰቡ፣ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪው፣ የማህበረሰብ ቱሪዝም ጽንሰ ሀሳብ አቀንቃኙ አብሮ ከቆመ ተአምር እንመለከታለን፡፡ ከነበረው የተሻለ ነገር እንሰራለን፡፡ ከሆነው የሚበልጥ ድል እናስመዘግባለን፡፡ ወራሪው ከመንዝ ጓሳ ጥሎ ጠፍቷል፡፡ የወረራውን ዳፋ አብረን ቆመን ታሪኩ ነውር ብቻ ሆኖ እንዲቀር እናደርገዋለን፡፡

ግን ሰው እናድንቅ፣ አድማሱ የጓሳ ጥበቃ ስፍራ ዋርደን ነው፡፡ ምድሩን ጥሎ አልጠፋም፡፡ እንደ ጭላዳው የመድፍና ታንኩ መተራመስ ሳያስፈራው በስፍራው ጸና፣ በመንዝ ኮረብታዎች እንደ ወንድ የጀግንነት ስራ ሰራ፡፡ ለሚወደው ምድር ነፍጡን ይዞ ታገለ፡፡ ይሄ ታሪክ የማይረሳው የመንዝ ገበሬዎች የሚያወድሱት ተግባር ሆኖ ይኖራል፡፡ መንዝ ጓሳን እወድዋለሁ ሲል እስከምን ለሚል ሰው መልስ ሲሰጥ ይኖራል፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top