ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በአፋር ግንባር
(አሳዬ ደርቤ ለድሬ ቲዩብ)
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠላትን አሻግረው የሚመለከቱበትን ባይናኩላር ከአንገቴ ላይ አንጠልጥዬ ከጎናቸው ተሰልፌያለሁ፡፡ ወሳኙን ትዕዛዝ አስተላልፈው የተከበበውን የባንዳ ሠራዊት ወደ መቀመቅ ከማውረዳቸው በፊትም ‹‹የሞት ቀጠና ውስጥ ካስገባኸው ሠራዊትህ ጋር በጓንት የተሸፈነ እጅህን ትሰጣለህ ወይስ አትሰጥም?›› የሚል መልዕክት ለደብረ ጽዮን የላኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹እጄን ቀርቶ ጓንቴን አልሰጥህም›› የሚል መልስ ተቀብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ፡-
‹‹የሊጥ ሐራራ ፥ ያቅበዘበዘው
እናት ኢትዮጵያን ፥ ማፍረስ ካማረው
ቋንጃውን ሰብረህ ፥ እንደ አብሲት ጣለው›› የሚል ትዕዛዝ ለማስተላለፍ ተገደዱ፡፡
በተመሳሳይ ጊዜም ባንድ እጁ መገናኛ፣ በሌለኛው እጁ የሊጥ ሞሃቻ አንጠልጥሎ የጠላትን ጦር የሚመራው አቶ ጌታቸው ረዳ በተጠለፈው መገናኛው አማካኝነት ‹‹ኢትዮጵያውያን እና ድሮን መምጫቸው ስለማይታወቅ ወደ ደቡብና ወደ ሰሜን አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰማይም ተኩሱ›› የሚል ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ተሰማ፡፡
አንገቴ ላይ ያንጠለጠልኩትን የጦር መነጽር ዐይኔ ላይ ሰክቼ የወገን ጦርን እንቅስቃሴ ስቃኘው… የጠቅላይ ሚኒስትሩን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው የዘመቱ ምሁራን፣ አርቲስቶች፣ ፖለቲከኞችና አትሌቶች በግንባር ተሰልፈው የሠራዊቱን ሞራል ይገነባሉ፡፡ ከእነዚህም ታዋቂ ሰዎች አንዱ የሆነው አርቲስት ታማኝ በየነ በጥይት ካፊያ መሀከል ቆሞ እንዲህ በሚል ሽለላ ጦሩን ያበረታታል፡፡
‹‹አቅሙን የማያውቅ፥ የፈርዖን ውሻ
ሰላምን ንቆ ፥ መዋጋት ካሻ
ጠራርገህ ጣለው ፥ እንደ ቆሻሻ››
በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጎን የተሰለፈው አትሌት ሃይሌ ገብረ ሥላሴም ወደ ፊት ከሚራመደው ጦር ጋር እየገሰገሰ፡-
ለቅኝ ገዥዎች- እጅ የማንሰጥ
ቡና ይመስል- አገር የማንሸጥ
ከእግሩ ስር ወድቀን- ስንለምነው
በኮንጎ ጫማ- መርገጥ ካሰኘው
በብርቱ ክንድህ- አቅሙን አሳየው›› እያለ ለሠራዊቱ ሞራልና ጥይት ያቀብላል፡፡
በዚህም ሁኔታ ስሜቱ የተነቃቃው የኢትዮጵያ ጦር የጭፍራን ምሽግ እንደ ገል እየሰባበረ ጠላትን መረፍረፍ ሲጀምር፣ በሞት አፋፍ ላይ ከሚገኘው ሠራዊቱ ‹‹አንገታችሁ ላይ ያደረጋችሁት የሱዳን መተት ጥይት አያስመታም አላልከንም ነበር ወይ›› የሚል ጥያቄ የቀረበለት ኣይተ ጌታቸው ረዳ ‹‹ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በድግምት አክሽፎት እንጂ መተቱ’ስ በሕይወት ያለን ቀርቶ የሞተን የሚቀሰቅስ ነበር›› የሚል መልስ ሲሰጥ ተደመጠ፡፡ ከአፍታ ውጊያ በኋላም ‹‹ወደ ሁሉም አቅጣጫ ተኩሱ›› የሚል ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ የነበረውና ከጦሩ መሃከል የሚተርፍ አለመኖሩን የተረዳው አቶ ጌታቸው ረዳ በተጠለፈው መገናኛው ውስጥ፡-
‹‹ያ ሁሉ ጎረምሳሽ- ያ ሁሉ ኮበሌ
ጭፍራ እረግፏልና- የኔዋ መቀሌ
ወንድ ልጅ የላትም- ብለው እንዳያሙሽ
ለዘር እሆን ዘንዳ- እኔ ልትረፍልሽ›› ብሎ ሲናገር ተሰማ፡፡
ይሄንንም ንግግሩን ያዳመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ፊት እየገሰገሱ ‹‹ያንን ጌታቸው ረዳ የተባለ ባንዳ ከእነ ሕይወቱ እፈልገዋለሁ›› የሚል ትዕዛዝ ለአትሌት ሃይሌና ፈይሳ ሌሊሳ አስተላለፉ፡፡ ሆኖም ግን አትሌት ሃይሌ ‹‹አቶ ጌታቸው እኮ አንገት የለውም›› የሚል አሳማኝ ሎጂክ በማቅረቡ ‹‹አንገት ከሌለው ብልቱንም ቢሆን አንቃችሁ አምጡት›› በማለት ከአጠገባቸው የቆመው ጄኔራል ትዕዛዙን አስተካከለ፡፡
አትሌቶቹም በሩጫ ወደ ፊት በመስፈንጠር ላይ ሳሉ… የጦር መነጽሬን ዐይኔ ላይ ደግኜ ጌታቸው ረዳ ወዳለበት ተራራ ስቃኝ በሚንቀጠቀጥ እጁ እጽ ጠቅልሎ ካጨሰ በኋላ መፈርጠጥ ሲጀምር ዐየሁት፡፡
ይሄንን ማፊያ አንቆ መመለስ በኦሎምፒክ ውድድር ላይ የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቆ ከመመለስ በላይ ዋጋ እንዳለው የተረዱት አትሌቶችም ፍጥነታቸውን ጨምረው ከኋላ ከኋላ ሲከተሉት ከቆዩ በኋላ በአነቃቂ እጽ ተበረታትቶ በድምጽ ፍጥነት በመፈርጠጥ ላይ የሚገኘውን ኣይተ ጌታቸው ረዳን መቆጣጠር በመቶ ሜትር ውድድር ላይ ቦልትን እንደ መፎካከር መሆኑን ተረዱ፡፡
ያን ጊዜም ተስፋ በቆረጠ ድምጽ ‹‹እግርህን ሰብረንህ ከምንጥልህ ብትቆም ይሻልኻል›› በማለት ሲያስጠነቅቁት ጌቾ ምን ብሏቸው ፍጥነቱን ቢጨምር ጥሩ ነው?
‹‹እግሬን ለመስበር ስታስቡ ሪከርዳችሁን ጎማምጄ ጉድ ከምሠራችሁ ብትመለሱ ይሻላችኋል››