ታላላቅ መሪዎች ሕያው ሆነው ባለፉበት የትግል ጎዳና ውስጥ የገባውን መሪ ማነፍነፉን ትታችሁ የሙታን ዋሻችሁን ፈልጉ
(አሳዬ ደርቤ ለድሬ ቲዩብ)
‹‹የማያድግ ልጅ በእናቱ ጀርባ ታዝሎ ጆሮዋ ላይ ያፉጫል›› የሚል አገራዊ አባባል አለ፡፡ ይሄም በሌላ አማርኛ ሲገለጽ ‹‹ጥጋበኛ ባንዳ በአገሩ ጫንቃ ላይ ሆኖ ‘አፈርስሻለሁ’ እያለ ይዝታል›› እንደማለት ነው፡፡ ከሰሞኑን ደግሞ ‹‹ድሮን የሚዞረውና ወደ መቃብር መውረድ ያማረው አሸባሪ ‘ገዳዬ የዘመተበትን ግንባር ለጠቆመኝ ወሮታ እከፍላለሁ’ የሚል የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ያወጣል›› የሚል አባባል ተፈጥሯል፡፡
የሆነው ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ጀርባ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ደሟን ሲመጣትና ‹‹አፈርስሻለሁ›› እያለ ሲዝትባት የኖረው ጁንታ ‹‹ለኔ ያሰብከውን ባንተ ላይ ያድርሰው›› የሚል እርግማኗ ደርሶበት በጀግኖች ልጆቿ ክንድ እንደ ጨው እየተደቆሰ ነው፡፡ ከሚያፍጫጭበት ትከሻዋ ተንሸራትቶ ወደ ከርሰ ምድሯ የሚወርድበት ክስተት አጋጥሞትም እሪታውን እያቀለጠ ነው፡፡
በዚህም የተነሳ ከሳምንት በፊት ባሉት ቀናቶች ‹‹ወደ አዲስ አበባ የምናደርገውን የድል ግስጋሴ ማስቆም የሚችል ምድራዊ ሃይል የለም›› እያለ ሲሸልል የነበረው ኣይተ ጌታቸው ረዳ ትናንት CNN ላይ ቀርቦ ‹‹ያንተን ፕሮፖጋንዳ መስማት ሰልችቶኛል›› በሚል አኳኋን ስትገላምጠው ለነበረችው ጋዜጠኛ ‹‹አዲስ አበባ መግባት ቀላላችን ቢሆንም መንግሥት መንገዱን ከከፈተልን በቦሌ ፈንታ ወደ መቀሌ ለመመለስ ዝግጁ ነን›› የሚል መልስ ሲሰጥ ተሰምቷል፡፡
ልብሱን እንጂ ቃሉን ማጠፍ የማይከብደው አቶ ጌታቸው ረዳ ‹‹ጦርነቱን በድል አጠናቅቀን ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር ካደረግን በኋላ የኢትዮጵያ ሁኔታ ምን መምሰል እንዳለበት የምንወስን ይሆናል›› የሚል አንጀባውን ሰርዞ ‹‹መብራትና ውሃ ከተለቀቀልን መውጫ ያጣውን ሠራዊታችንን ለማስወጣት ዝግጁ ነን›› የሚል የመሠረተ ልማት ጥያቄ ማቅረብ ጀምሯል፡፡
ከወር በፊት በክብር መንፈስ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳች ስትጠይቀው ለነበረችው የ CNNን ጋዜጠኛ የተስፋ ዳቦውን እና ‹‹ላም አለኝ በሰማይ›› የሚል ምኞቱን ሲመግባት የታየው የአሸባሪው ቃለ አቀባይ በሰሞኑን ኢንተርቪው ላይ ጥያቄዋንም ሆነ ግልምጫዋን መቋቋም ተስኖት ሲንተፋተፍ ተስተውሏል፡፡ በፌስቡክና በትዊተር ገጹም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለፍርድ እናቀርባለን›› ወይም ደግሞ ‹‹በቀናት ውስጥ አዲስ አበባ እንገባለን›› የሚል ብሽከታውን ጋብ አድርጎ ‹‹ባላሰብነው ሰዓት በሚፈጸምብን የድሮን ጥቃት መቀሌ ውስጥ መቀመጫ አጥተናል›› የሚል ስሞታውን ይጦምር ይዟል፡፡ ‹‹በክልሉ ውስጥ ያለው ሁሉም ዜጋ ወታደራችን ነው›› ማለቱን እረስቶ በለኮሰው ጦርነት ጓዶቹን ሲነጠቅ ‹‹ሲቪሊያን አለቁብን›› ማለት ጀምሯል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ‹‹ኢትዮጵያን የነካ የለውም በረካ›› እንደሚባለው የህውሓት አመራሮች ፉከራቸው ቀርቶ ቁጥራቸው ቀስ በቀስ መመናመን ጀምሯል፡፡ ሰው ሰራሿ ወፍ የአሸባሪዎቹን መኖሪያ ቤት ማንኳኳት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰለፉበትን ግንባር ለጠቆመን 11 ሚሊዮን ብር እንሸልማለን›› የሚለውን የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ገንጥለው ላብ የሚያመነጭ ግንባራቸውን እያበሱ የማያምኑትን ሰማይ መቃኘት እንደጀመሩ እየተሰማ ነው፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ የአፋልጉኝ ማስታወቂያ የወጣበት ጠቅላይ ሚኒስትር፡-
ጡት ላጠባችን ፥ ሕይወት የምንሰጥ
ቡና ይመስል አገር የማንሸጥ
ኢትዮጵያ እስክንሆን ገብተን ከአፈሯ
ኢትዮጵያዊ ነን- ቋሚ ለክብሯ›› እያለ በአፋር ግንባር መሰለፉን በሚገልጽ ቪዲዮ ሲገለጥ፣ በርካታ የኮርና የጦር አመራሮቻቸውን የገበሩትና በድሮን ፎቢያ የሚሰቃዩት የጁንታው አመራሮች ግን የሚዋጉበትን ግንባር በመምረጥ ፈንታ የሚደበቁበትን ዋሻ የማሰስ ግዴታ ወድቆባቸዋል፡፡
‹‹አገሩን የከዳ- ታሪክ የለሽ ባንዳ››
በሕይወቱ ሳለ- ወገን የሚጎዳ
ሲሞት አልቃሽ የለው- ሕልፈቱ አይረዳ›› እንደሚባለው ትናንት ጭፍራ ላይ ቆሞ ሲሸልል የነበረው ጄኔራል ታደሰ ወረደ አልቃሽ ቀርቶ አስታዋሽ እንዳይኖረው ሆኖ ወደ መቃብር ወርዷል፡፡
በሌላ መልኩ ግን፡-
ለአገር ሕልውና- ለክብሯ የሚዘምት
ልቡ እየነገረው- አርፎም እንደማይሞት
ጥይቱ ሲያካፋ- ሲበረታ ተኩሱ
በእርካታ ተሞልቶ- ፈገግ ይላል ጥርሱ›› እንደሚባለው የኢትዮጵያን ጦር እየመራ ወደ ግንባር ያመራው ጠቅላይ ሚኒስትር ታደሰ ወረደ ከቆመበት ምድር ላይ ቆሞ ሲፈግግ ታይቷል፡፡
እናም እንላለን…
ሕልፈት በሌለበትና ሕያው መሪዎች በዘመቱበት በዘላለማውያን የጦር ግንባር ላይ የተሰለፈውን ጠቅላይ ሚኒስትር መፈለጉን ትታችሁ በሕይወት አልባ የትግል መስመር ውስጥ ገብተው ሲርመሰመሱ የከረሙ ጓዶቻችሁ የገቡበትን መቃብር ፈልጉ፡፡
ከሴቶች ጓዳ ውስጥ ተወሽቃችሁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘመተበትን የወንዶች ስፍራ ማነፍነፉን ተውና ከኢትዮጵያውያን እና ከድሮን እይታ የራቀ የሙታን ዋሻ መርጣችሁ እራሳችሁን ቅበሩ፡፡
ድል ለአገራችን!